Saturday, October 4, 2014

የጋብቻ አቀበት …የፈረሰ ይሁን!

ዲቮሽን .22/2007 ሐሙስ፣ መስከረም 22/2007 ..
(
በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


የጋብቻ አቀበትየፈረሰ ይሁን!


እርሱም፦ እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ ወደ ጌታዬ እሄድ ዘንድ አሰናብቱኝ አላቸው።ርብቃንም ጠርተው፦ ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን? አሉአት። እርስዋም፦ እሄዳለሁ አለች። እኅታቸውንምመረቁአትና፦ አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ ዘርሽም የጠላቶችን ደጅ ይውረስ አሉአት። ርብቃም ተነሣች ደንገጥሮችዋም፥ በግመሎች ላይ ተቀምጠው ያንን ሰው ተከተሉት …(ዘፍ 2456-61)

ከብዙ ዓመታት በፊት The Dirty Dozens በተሰኘ ፊልም ውስጥ የተመለከትሁትን ነገር ባስታወስኩ ቁጥር ልቤ ይነካል! በፊልሙ ውስጥ አንድ ከፍተኛ ደረጃ ያለው የጦር መኮንን፣ ለከፍተኛ ደረጃ ውትድርና የሚሰለጥኑ ሰዎችን ሲመለምል ያሳያል፡፡

አንድ ቀን ሰልጣኞቹ በገመድ እየተንጠላጠሉ ረዥም ከፍታ ወዳለው ማማ እንዲወጡ ታዘዙ፡፡ ጥቂቶቹ በስቃይ ማማው ላይ መውጣት ሲችሉ፣ አንዱ ግን መሃሉ ላይ ደርሶ ደከመውና መውጣት አቃተው፡፡ ለአለቃውም፣ ‹‹አልችልም›› ሲል ይነግረዋል፡፡ አሰልጣኙ ተኮሳትሮ ‹‹ትችላለህ›› ብሎ መለሰለት፡፡ ሰልጣኙ በደከመ ድምጽ በድጋሚ ‹‹አልችልም›› አለ፡፡

ሰልጣኙና አሰልጣኙ ‹‹ትችላለህ፣ አልችልም፣ ትችላለህ፣ አልችልም›› እየተባባሉ ሲጨቃጨቁ ጥቂት ሰኮንዶች አለፉ፡፡ በዚህም ምክንያት የተናደደው አለቃ፣ ከረዳቱ እጅ መሳሪያ በመንጠቅ ወደ ሰልጣኙ አቅጣጫ የጥይት እሩምታ ይተኩሳል፡፡ በዚህ ቅጽበት፣ ገመድ ላይ ደክሞትና እንደዚያ ዝሎና ተንጠላጥሎ የነበረው ሰልጣኝ፣ እንደ ጦጣ እየተስፈነጠረ ከማማው አናት ላይ ባንዴ ወጥቶ ጉብ አለና አማተበ፡፡

ታውቃላችሁ፣ በውስጣችን የታመቀ ኃይል አለ! በውስጣችን ያልታወቀ ብቃት፣ ያልተነካ ጉልበት አለ! አውጥተን ያልተጠቀምነው ስጦታ፣ ያልተገለገልንበት ችሎታ በውስጣችን አለ! ይህንን እውነታ ደግሞ ካመንን፣ በጋብቻ ላይ በአገራችን ያለውን ኋላቀር ባህል መድፈር እንችላለን፡፡ ወግና ልማዳችንን መስበር እንችላለን፡፡ እንደ ርብቃ፣ የሰርግና ድግስ ይሉኝታን አሽቀንጥረን መጣል እንችላለን፡፡ ማግባት እየፈለግን የሚያዘገየንን፣ ዕድል እያለን የሚያጨናግፈንን፣ ክብር እያለን የሚያዋርደንን፣ ሁሉ ማሸነፍ እንችላለን፡፡ ቤተሰብ ባይፈቅድ ቤተክርስቲያን አለን፣ የስጋ ዘመድ ባይቀበል መንፈሳዊ ዘመድ አለን፡፡

የአባይን ልጅ ውሃ ከጠማው፣ የላጭን ልጅ ቅማል ከበላው፣ ችግር አለ ማለት ነው! ግራና ቀኛችን በሚወድዱን ታጅቦ፣ ዙሪያ ገባችን በሰው ተከብቦ፣ ነገር ግን ለትዳር የሚሆን ሰው ከጠፋ እኛ ችግር አለ ማለት ነው!

ታውቃላችሁ፣ ስኬት የሚገኘው በፈተና ውስጥ ነው! ውቧ ጽጌረዳ እሾኻም ናት፡፡ ጣፋጭ ማር ሰጭ ንብ መርዝ አላት፡፡ ዓሳም አጥንት አላት፡፡ ብርቅዬ ማዕድናት የሚገኙት ከድንጋይ ውስጥ ነው፡፡ ወርቅና ብረት የሚወጣው ከአፈር ውስጥ ነው፡፡ ትዳር የሚገኘው ከሰው መካከል ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ አለት ተደርምሶ ማዕድን ከወጣ፣ አፈር ተቆፍሮ ብር ወርቁ ከወጣ፣ ከሰው ተፈልጎ እንዴት ትዳር ይታጣል? መፈቀር ሳያንሰን፣ ማፍቀር ሳያቅተን፣ መውደዱ ሳይቸግር መወደዱም ሳለ፣ ትዳር እንዴት ተራራ ይሆናል? ጠባይና ውበት፣ ችሎታና እውቀት ሳያንስ፣ እህልና ውሃ ሳይቸግር፣ ትዳር ምስረታው እንዴት ዳገት ይሆናል? ሰው ትዳር መያዝ እየፈለገ ለምን ያቅተዋል?

ክልላዊነትና ቀበሌያዊ አስተሳሰብ ለበርካታ ወገኖቻችን ትዳር እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በርካታ ምዕመናን ይህንን አስተሳሰብ ጥሰው መውጣት አልቻሉም፡፡ በጌታ አምነው የዳኑ በርካታ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች እንኳ ጋብቻ ለመመስረት በዘር፣ በወንዝና በቁሳቁስ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ተንጠላጥለው ይታያሉ፡፡ ብዙዎቹ የቤተሰቦቻቸውን ፈቃደኝነት ይጠብቃሉ፡፡ በርካታ የአገራችን ቤተሰቦች ደግሞ ጠባብ አስተሳሰብ አላቸው፡፡ ለትዳር ምስረታ ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀምጣሉ፡፡ ሀብትን፣ ዘርን፣ ባህልን መሠረት አድርገው ይሁንታ ይሰጣሉ፣ ወይም ይነፍጋሉ፡፡

በተለይም እህቶች ጋብቻን ለራሳቸው ሳይሆን ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ የሚመሰርቱ ይመስላል፡፡ በአገራችን ስለጋብቻ ሲታሰብ ሰርግ፣ ስለ ሰርግ ሲታሰብ ደግሞ ድግስ፣ ድግስ ሲታሰብ ደግሞ አሸሼ ገዳሜው ይታሰባል! ለብዙዎቻችን ድንኳን ካልተተከለ፣ ቡፌ ካልተደረደረ፣ ጮማ ካልተቆረጠ ቅልጥም ካልተገሸለጠ ጋብቻው ጋብቻ አይመስለንም፡፡ ተጋቢዎች ይህን ለማሟላትም፣ አቅም ስለሚያንስ ለዓመታት መቆየት ይገደዳሉ፡፡ አንዳንዶቹም የማይችሉት ይሆንና ወዳሰቡበት ሳይደርሱ ተሰናክለው ይወድቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ በሰው ምርጫ ሳይሆን በቁሳቁስ ምርጫ ላይ ዘመናቸውን ጨርሰው ወደኋላው ዘመን ይቆጫሉ፡፡

አንዳንድ ጀግና እህቶች ደግሞ አሉ፡፡ እንደ ርብቃ የቆረጡሌሞዚን ካልመጣ፣ መርቼዴስ ካልወጣ የማይሉ! ጋብቻን ለመመስረት፣ ቪላ ካልተሰራ፣ መኪና ካልተገዛ፣ ብለው የማያመቻምቹ! እማዬ፣ አባዬ፣ እህትዬ ጋሼ እያሉ በገዛ ምርጫቸው ላይ የማይልፈሰፈሱ! አጃቢ አነሰ፣ ሰርገኛው ቀነሰ የማይሉ እንደ ርብቃ ያገኙትን ይዘው፣ በቀረበው ነገር ተሳፍረው የሚሄዱ!

የጋብቻ አቀበት፣ የባህልና የይሉኝታ ሰንሰለት በኢየሱስ ስም የተመታ ይሁን! ከሚቀርቡን ፊት የሚያሸሸን፣ ከሚሸሹን ኋላ የሚያሮጠን መንፈስ በጌታ በኢየሱስ ስም የተመታ ይሁን! የትዳር ፈተና፣ የኑሮ ቀንበር፣ የተሰበረ ይሁን! ልብን ትቶ መልክን፣ መንፈስን ጠልቶ ስጋን የሚያስወድድ ባህላዊ የሰው መስፈርት የተሰበረ ይሁን፡፡ ለሰርግና ድግስ፣ ለብር ለቁሳቅስ ጋብቻን የሚያዘገይ መንፈስ የተሰበረ ይሁን! ትዳርን በሀብት ላይ፣ በመልክና ዘር ላይ የሰቀለ መንፈስ የተመታ ይሁን! ጋብቻን የሚያጠብብ ክልላዊ ግድብ፣ ቀበሌያዊ ምድብ የፈረሰ ይሁን! በጌታ በኢየሱስ ስም የጋብቻ አቀበት የተናደ ይሁን! ይህ ዓመት የጋብቻ ዓመት ይሁን!
 

No comments:

Post a Comment