Thursday, July 30, 2015

ይጨምርልን !

ዲቮሽን 323/07 ፤ ሓሙስ ሓምሌ 23 /07
( ወንድም ጌታሁን ሓለፎም )


ይጨምርልን !


“ ምህረት እና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ ” ይሁዳ 1፡- 2


አሜን ይብዛልን !


መቼስ ሁላችንም እንደምንመሰክረው እና እንደምንረዳው ፡- ወደ ጌታ ዘውር ካልንበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከእግዚአብሔር ከሆነልን አስደናቂ በረከቶች ውስጥ አንዳንዶቹን እንቁጠር ብለን ብንል ፤ የተትረፈረፉልን ሰላም ምህረትና ፍቅር ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሆነው እናገኛቸዋለን ፡፡



እንደበግ የምንቅበዘበዝ ፤እረፍት አጥተን የምንባዝን ነበርን ፤ ነገር ግን ጌታ ወደ ሂወታችን ሲገባ ታላቅ ሰላም እና ምረጋጋትን ተቀበልን ፤ በነጻነት መግባት መውጣት ሆነልን ፤ መሲሁ ወደ ልባችን እልፍኝ ሰላምን ይዞ መጣ !



በመስቀል ላይ ስለ ሰው ልጆች ኃጢያት እራሱን አሳልፎ በሰጠው በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ታላቅ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር አየን !



ታዲያ ሓዋርያው ያቆብ እንደሚለን እነኝህ ከግዚአብሔር የተሰጡን ስጦታዎች ዋጋቸው ታላቅ ነው እና ፤ በየእለቱ የሚበዙ የሚያድጉ የሚጨምሩ ይሁኑ እንጅ በነገሮች እና በሁኔታዎች የተነሳ የሚከስሙና የሚጫጩ መሆን የለባቸውም ፤ ተመልሰን ወደ ፍርሃት ፤ ተመልሰን ወደድንጋጤ ተመልሰን ወደ ኃጢያት እስራት ፤ ተመልሰን ወደብዝበዛ እና ሽንፈት መግባት አይገባንም ፤ይልቁንም የሚበዙ የሚጨምሩ እና የሚያድጉ ይሁኑ !




እውነት ነው ይህ ከጌታ የተሰጠን በረከት በየእለቱ የሚበዛ እና የሚጨምር መሆን ይገባዋል ፤ በነጻ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ነገር ግን እጅግ ውድ ስጦታ ! የማይከፈልበት ያልተለፋበት ነጻ በረከት! አዎ ብር ወርቅ የማይገዛው ውድ ስጦታ !



ስለዚህም ፡- በወንድሞች መካከል ሰላም ይሁን !

ለቤተክርስቲያን ፤ ለምድራችን ፤ ለአለም ሰላም ይሁን ! 



ለሰው ልጆች በሙሉ ከእግዚአብሔር ምህረት እና ሰላም ፍቅር ይሁን ! መጭው ዘመናችን “ ምህረት፤ሰላም እና ፍቅር ” የሚበዛበት ወደ ጌታ ነፍሳት የሚጨመርበት በነገር ሁሉ የምናድግበት ዘመን ይሁን !


------------
እለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ሊጠናቀቅ 43 ቀናቶች ቀርተውታል !

ማነው የሚለየን?????????????

ዲቮሽን 322/07፥ ረቡዕ፥ ሐምሌ 22/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ማነው የሚለየን?????????????

ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ሮሜ 8፡35

በዚህ ምርጫ እና እድል በበዛበት ዓለም፣ መጀመሪያ የያዝነውን የክርስቶስን ፍቅር ይዞ መቆየት ትግል ሆኖብናል። ያንን፣ በእንባና በልቅሶ የምንወደውን ኢየሱስን፣ አሁን በበርካታ ነገሮች ለውጠነዋል።

በድፍረት እናገራለሁ፡ ኢየሱስን በዓለምና በውስጧ ባሉት ነገሮች ተክተነዋል። በፋሽን ተክተነዋል፣ በምቾት ተክተነዋል፣ በድሎት ተክተነዋል። በዝና፣ በእኔ አውቃለሁ ባይነት ተክተነዋል፣ በእውቀታችንም ተክተነዋል፣ በመኪናችን፣ በቤታችን፣ በትዳራችን፣ በቆንጆ ባሎቻችንና ሚስቶቻችን፣ በዘናጭ ልጆቻችን ተክተነዋል፣ በውጭ ሐገር ጉዞዎቻችን ተክተነዋል፣ በዲግሪና በማስተርሳችን፣ በፒኤችዲያችንንና በፕሮፌሰርነታችን ተክተነዋል።

ደግሜ እላለሁ፡ ያንን የሚወደንን፣ ያንን ምስጢረኛችንን ኢየሱስ፣ ያንን የምድረበዳችን ኢየሱስን፣ ያ በተዘጋው ቤታችን የመጣውን ኢየሱሰን፣ ያ የዘላለም ወዳጃችንን ኢየሱስን፣ በሞራል ትምህርት ለውጠነዋል፣ በሳይኮሎጂ ነክ ትምህርት ለውጠነዋል።

ወገኖቼ፣ እኛ እኮ ከኢየሱስ ጋር ብዙ ምስጢር ያለን ሰዎች ነን። ያልተቻለውን ችሎልን፣ ያ የሚከረፋውን እና የሚሸተውን ቁስላችንን ያጠበልንን ኢየሱስን፣ ያ ክፋታችንን እና ሞታችንን ሁሉ ወደ ህይወት የቀየረልንን ኢየሱስን፣ ያ ማንም ወዳጅ እና ሰው ሲጠላን ያልጠላንን ኢየሱስን ለምን ዛሬ ቸለል ቸለል አልነው?

ጳውሎስ፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ችግር ነው ወይስ ስቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቁትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ? ሮሜ 8፡35 እንደሚላቸው ሳይሆን፣ ዛሬ እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ጥጋብ ወይስ ምቾት፣ ወይስ የተንጣለለ ማረፊያ ቤት፣ ወይስ የሚቀያየሩ ልብሶች፣ ወይስ መንግሥታት ያስጠበቁልን ደህንነታችን?
እላችኋለሁ፤ ማንም አይለየን!!!! ማ----ን-----ም!!!!!!

አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ ላንተ የሚሳንህ ነገር የለምና፣ እለምንሃለሁ ወደ ቀደመው ፍቅራችን እና የዋህነታችን መልሰን። በእርግጥ ታደርገዋለህና ተባረክልኝ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 44 ቀን ቀርቶታል

Tuesday, July 28, 2015

አትምረጡ!!!!!

ዲቮሽን 321/07፥ ማክሰኞ፥ ሐምሌ 21/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


አትምረጡ!!!!!

የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን። ኢያሱ 24፡ 15

ኢያሱ የእሥራኤላውያን ነገር አንዴ ያዝ አንዴ ለቀቅ ያለ ዘይቤ ቢይዝበት ደከመውና፣ ምክሩን ሁሉ ሲፈልጉ ሲቀበሉ፣ ሳይፈልጉ ሲጥሉ፣ ሞቅ ያላቸው እንደሆነ ጣዓት ሲያመልኩ፣ መከራ ሲደርስባቸው ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ፣ እንዲያው ታከተውና፣ ራሴን ባድንስ፣ ሲፈልጉ እግዚአብሔርን ያምልኩ፣ ካለፈለጉ ይተውት በማለት ይመስለኛል፣ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ኢያሱ 24፡ 15 በማለት እግዚአብሔርን የማምለክን ጉዳይ ምርጫ ውስጥ ያስገባላቸው።

ዛሬ ግን እኔ እንዲህ እላችኋለሁ! ግዴላችሁም አትምረጡ!!! በሞትና በሕይወት መካከል ሰፊ ልዩነት አለና ለማን ይድላው ብላችሁ ነው፣ ሞትን የምትመርጡት? በሲኦልና በመንግስተ ሰማያት መካከል ከቃላት በላይ የሆነ ልዩነት አለና፣ ለማን ይመቸው ብላችሁ ነው ሲኦልን የምትመርጡት?

ዘመኑ የምርጫ ነው። ሰፊ አማራጭ አለን። ብንፈልግ ኢየሱስን እንደ ሞራል አስተማሪ ልንቀበለው እንችላለን፣ ብንፈልግ እንደ አሪፍ መሪ ልንቀበለው እንችላለን፣ እንደ ትልቅ ምሁርም ልናየው እንችላለን፣ በየወቅቱ ከተነሱት ፈላስፎችም እንደ አንዱ ማየትም መብታችን ነው። ግን ይህ ሁሉ ከሞት አያድነንም። ከሞት የሚያድነው፣ ኢየሱስን እንደ እግዚአብሔር ልጅ መቀበል ብቻ ነው።

ስለዚህ ግዴላችሁም፣ ኢየሱስን ከስነልቦና ምሁራን ጋር አታወዳድሩት፣ ከፈላስፎችም ጋር አታነጻጽሩት። እንዲህ ያለው እውቀታችን የትም አያደርሰንም፣ ከዘላለም ሞት በቀርም የሚያመጣልን ምንም ነገር የለም። ለዚህም ነው ጳውሎስ፣ “በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፣ ይህ እውቀት አለን ብለው አንዳንዶች ስለእምነት ስተዋልና ያለው።” 2 ጢሞ 6፡20።

ኢየሱስ ያድናል!!!!!

አባትዬ፣ እንዲህ እንድናገር ድፍረቱንም ዓቅሙንም ስሰጠህኝ አመሰግንሃለሁ። የምድረበዳየ ኢየሱስ ሆይ፣ እወድሃለሁ። ወንዶች እና ሴቶች ልጆችህ ሁሉ አንተን በማወቅ እንዲሞሉ አሁን መንፈስህን አፍስስባቸው። ሰምተህኛልና ተባረክኝ።

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 45 ቀን ቀርቶታል

እንጮሃለን፣ እንድናለን!!!!!!

ዲቮሽን 320/07፥ ሰኞ፥ ሐምሌ 20/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


እንጮሃለን፣ እንድናለን!!!!!!

በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። መዝ 107፡ 28

ያው አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ስለሆንን፣ የጠላታችንን ውድቀት ልናይ፣ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ወዳሰበልን ልንገባ የተቃረብንበት ጊዜም ስለሆነ ያለን ብቸኛ አማራጭ በሰልፉ ልክ፣ በመከራችን ልክ፣ ወደ እግዚአብሔር መጮህ ነው።
ዙሩ ከርሯል ወገኖቼ!!!!!!!!

አንዳንዶቻን፣ ጭው ባለ በረሐ እየተቅበዘበዝን፣ የእግዚአብሔርን ክብር እየተራብን፣ እየተጠማን፣ ወደ ሰማይ እየጮህን ያለን ሰዎች አለን አይደል? እርሱ የተጠማችውን ነፍስ ያረካልና፣ የተራበችውንም ነፍስ ከበጎ ነገር ያጠግባልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶቻን፣ በብረት ሰንሰለት የታሰርን ፣ መውጫ መፈናፈኛ ያጣን፣ በጭለማ በጥልማሞት የተቀመጥን፣ የሚደግፈን፣ የሚያነሳን ያጣን፣ ከጉድጓድ ማን ያወጣናል የምንል፣ ከወህኒ ማን ይፈታናል የምንል፣ ወደ ሰማይ እየጮህን ያለን ሰዎች አለን አይደል? እርሱ የናሱን በሮች ይሰብራልና፣ የብረቱንም መቆርቆሪያ ይቆርጣልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶች ደግሞ፣ ከበደላችን የተነሳ ችግር ውስጥ የገባን፣ ሰውነታችን የምግብ አይነት የተጸየፈች፣ ወደ ሞትም ደጃፍ የቀረብን አለን አይደል? ቃሉን ልኮ ይፈውሰናል፣ ከመቃብርም አፋፍ ይመልሰናልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶቻችን ደግሞ፣ ከነፋሱና ከማዕበሉ የተነሳ ሐሞታችን የፈሰሰ፣ እንደ ሰከረ ሰውም የምንንገዳገድ፣ መላው ጠፍቶብን የምናደርገውን ያጣን አለን አይደል? እርሱ ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ ያደርጋል፣ የባሕሩንም ሞገድ ረጭ ያደርጋል፣ ወዳሰብነውም ወደብ እንደርሳለንና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አባት ሆይ፣ እጆቻችንንም ሰልፍ፣ ጣቶቻችንንም ዘመቻ ስላስተማርክልን፣ ወደ ምልጃ ጸሎትም፣ ወደ ጩኸትም ስላስገባህን ተባረክ። ሁሉ ለስምህ ክብር ይሁን፣ ሰምተህኛልና ተባረክ። አሜን!!!!!!

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 46 ቀን ቀርቶታል

እለምንሃለሁ!!!!!!

ዲቮሽን 319/07፥ እሁድ፥ ሐምሌ 19/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)



እለምንሃለሁ!!!!!!

ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ። ዘፍጥረት 13፡9

እንኳን በሰው ሃገር ቀርቶ በትውልድ ሃገራችንም የስጋ ዘመዶቻችንን እንፈልጋለን። አጠገባችን እንዲሆኑ፣ ደስታንም ሆነ ሃዘንን አብረውን እንዲካፈሉን እንሻለን። አብርሃም ግን ሲፈራ ሲቸር ፣ አንድ ቀን ጨከነና፣ ይህንን የማያዛልቅ፣የትም የማያደርስ ዝምድና ሊለየው ፈለገ። ሒድ ብሎ ሎጥን ሊያባርረው አልቻለምና፣ “ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ”። ዘፍጥረት 13፡9 ብሎ ይለማመጠዋል።

እንዲያው ዛሬስ በኛ ዘመን እንደ ሎጥ የሆኑብን ጨክነን ልናርቃቸው ያልቻልናቸው አመሎች ይኖሩብን ይሆን? እግዚአብሔርን እያመለክን ግን ደግሞ ብዙ ጸያፍ የሆኑ ነገሮች፣ አስተሳሰቦች አብረውን ተጣብቀው ይኖሩብን ይሆን?


ለምሳሌ፣ ጫት መቃም እየወደድን፣ መጠጣት እየወደድን፣ ማመንዘር እየወደድን፣ መዋሸት እየወደድን፣ መዝፈን እየወደድን፣ ማማት እየወደድን ..... በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔርን ማምለክ እንፈልግ ይሆን? እንዲያው ምናልባት እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ ያለን ሰዎች እንኖር ይሆን? የምንወዳቸው ክፉ ልምምዶቻችን የእግዚአብሔርን ክብር እንዳናይ ከልክለውንስ ቢሆን? መቼም ለእግዚአብሔር የሚያቅተው ነገር የለምና፣ ለምን ተስማምተን አንጸልይም?

አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ በሕይወታችን ላይ ተጣብቀው ያሉ የተለያዩ የምንወዳቸውን ሐጢያቶች እባክህ እንድንጠላቸው እርዳን? ካለነሱ መኖር የሚያቅተን የሚመስለንን፣ ለስጋችን የሚመቹንን ክፋቶች፣ ወዳጄ ሆይ አንተ ቻልና እባክህ ከእኛ አርቃቸው? እንድንጠላቸው አድርገን? የሚጣፍጡንን ሐጢያቶቻችንን፣ እንደ ማር ወለላ የሆኑብንን ከንቱ ልማዶቻችንን እባክህ አንተ በስልጣንህ ከእኛ አርቃቸው? እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ እንዳለ ዳዊት (መዝ 51፡7)፣ ወዳጄ ሆይ፣ ሥጋችንን ባይፈቅድ እንኳን እንደ ሕጻን ልጅ ገርፈህ ዛሬ እጠበን። አባብየ፣ ታደርገዋለህና ተባረክ።

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 47 ቀን ቀርቶታል፡፡

እንደ መንጋ!!!!

ዲቮሽን 318/07፥ ቅዳሜ፥ ሐምሌ 18/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


እንደ መንጋ!!!!

ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ!!!!! መዝ 80፡ 1

ያ በልጅነቱ እናቱን በማጣት የተጎዳው ዮሴፍ፣ በወንድሞቹ ዘንድ ደግሞ የመግደል ሙከራ ተደርጎበታል። እሱንም ሲያልፍ ደግሞ የቀረበለትን የዝሙት ፈተና እምቢ በማለቱ፣ በእስር ቤት ማቅቋል። ብቻ ታሪኩን ብታጠኑት ከልጅነቱ ጀምሮ በስጋ ዘመዶቹም ሆነ በባእድ ሰዎች ዘንድ ብዙ ሸክምን የተቀበለ ሰው ነው-ዮሴፍ። ቢሆንም አልሞተም፣ አልፎ ተርፎም፣ እግዚአብሔርን ያየለትን ነገር ሁሉ አንድም ሳይቀር አየ። ለብዙ ክፉ ነገር ታጭቶ የነበረው ዮሴፍ፣ በመዝ 80፡ 1 ላይ ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ ሆይ ተብሎ፣ በዝቶ ተባዝቶ እናየዋን።

እንግዲህ እናንተ እግዚአብሔር የምትፈሩ ሆይ፣ በከባድ መንገድ እያለፋችሁ ይሆን? በቤተሰብም፣ በሥራ ቦታችሁም፣ በመንደርም፣ በስደትም ያላችሁ፣ በመከራ እያለፋችሁ ይሆን? ምናልባት በወህኒ ቤት፣ ወይም በሆስፒታል ያላችሁ ትኖሩ ይሆን? ወይም ደግሞ ሁሉም ሰው ተስፋ ቆርጦባችሁ ይሆን?

ታዲያ ለምን ተስማምተን አንጸልይም፣ እንዲህ በማለት፣

እግዚአብሔር ሆይ፣ ዳዊት (143) ሲናገር ህያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባርያህ ጋር ወደፍርድ አትግባ እንዳለ፣ ከዚህ ከደካማ ሥጋችን የተነሳ ሥፍር ቁጥር የሌለበት ሐጢያት ውስጥ እየገባን ልብህን ባሳዘንንበት ነገር ሁሉ፣ ኤልሻዳዩ ሆይ፣ በእንባ እለምንሀለሁ፣ አሁን ይቅር በለን። ጠላት ላልተገባ ነገር እና ባልተገባ ቦታ እንደ ዮሴፍ ሸጦን ቢሆን እንኳን፣ እባክህ ዛሬ አንተ በኢየሱስ ደም መልሰህ ግዛን። ከወህኒም አውጣን። ከዚያም ወደ አየህልን ነገር አንድም ሳይቀር አስገባን፣ እንደ መንጋም አድርገን። ወዳጄ ሆይ፣ ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 48 ቀን ቀርቶታል፡፡

ካላየሁ አላምንም!!!!!

ዲቮሽን 317/07፥ አርብ፥ ሐምሌ 17/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


ካላየሁ አላምንም!!!!!


የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ..... እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው። ዮሐንስ 20፡ 25


እንግዲህ ክርስትና የመጠማት፣ የመፈለግ፣ እና ከኢየሱስ ጋር የሚኖረን የግል ልምምድ ነው። አንዱ ጋር የሚኖር ልምምድ ሌላው ዘንድ ላይኖር ይችላል። ኢየሱስ የግል አዳኛችን ነው። በግላችን እሱን እንፈልጋለን፣ በደረስንበት እንመላለሳለን። መቼም እመን/ እመኚ ስለተባልን ማመን አንችልም። መሆን የምንችለው ራሳችንን ነው።


ስለዚህ ዛሬ በጌታ ፊት በፍጹም ቅንነትና እውነተኛነት ብንቀርበስ? ቶማስ ያደረገው እንደዚህ ነው። ተጠራጣሪ ልብ እያለው ራሱን አማኝ አስመስሎ በጌታ ፊት አልተመጻደቀም፤ በወንድሞቹም መካከል አልዋሸም። ይልቅስ በይፋ በግልጽ “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ፣ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላስገባሁ፣ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው። ዮሐንስ 20፡ 25። የልቡን ቅንነት ያየው ኢየሱስም አላሰፈረውም። የቶማስንም የልብ ጭንቅ እና ጥርጣሬ መፍትሔ አበጀለት።


እንግዲህ ምናልባት እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ካላችሁ ለምን ተስማምተን አንጸልይም፣ ኢየሱስ ሆይ ከስጋ ድካማችን የተነሳ፣ ከዘገየ ተስፋችንም የተነሳ፣ በጥርጣሬ ውስጥ ላለን ሁሉ እባክህ ዛሬ ተገለጥ። እባክህ ወዳጄ ሆይ፣ እኛም በዓይኖቻችን እንይህ፣ በእጆቻችንም እንዳስህ፣ እንደ ቶማስም ጌታየ አምላኬ እንበልህ። ዘመዴ ሆይ ተባረክ።


--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 49 ቀን ቀርቶታል፡፡

Thursday, July 23, 2015

እንባዎትን አስታዋሽ – አለን?



ዲቮሽን 316/07 ሐሙስ ሐምሌ 16/07 /
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


እንባዎትን አስታዋሽ – አለን?

እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ (2 ጢሞ 1፡4)።

ወዳጄ ሆይ፣ በአካል በዓይነ ሥጋ ሊያይዎት የሚናፍቅ፣ ወዳጅ ይሁን ዘመድ አሊያም የቅርብ ጓደኛ ወይም የአገልግሎት ባልደረባ አለዎት? ስለርስዎ የሚያስብ፣ ስለጤንነትዎ ስለደህንነትዎ፣ ስለሁለንተናዎ ስለሳቅ ደስታዎ የሚገደውና ትዝታ ያለው ሰው አለዎት?  ዓይንዎትን ለማየት ጉጉት ያደረበት፣ ፊትዎትን ለማየት ናፍቆት ያደረበት፣ ሲስቁ ሲያለቅሱ ከርስዎ ጋር ለመሆን ፍላጎት ያለበት ሰው በእውነት አለዎትን?  

ወዳጄ ሆይ፣ ሐዋርያ ጳውሎስንና ጢሞቴዎስን ያስቡ! የግንኙነታቸውንና የፍቅራቸውን መጠን፣ የመቀራረባቸውንና የመተሳሰባቸውንም ልክ ያስቡ! የሁለቱም ወዳጆች ፍቅር ስንመለከት ሲገናኙም በእንባ ሲለያዩም በእንባ ነው! ግንኙነታቸው ከሰላም ጊዜ እስከ መከራና ብሎም እስከ ስደት፣ እንዲሁም ከነጻነት እስከ ወኅኒ ቤት ይዘልቃል፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ በሰላም ጊዜ፣ ሁሉ ምቹ በሆነ ጊዜ፣ ወዳጆቻችን ብዙ ናቸው፡፡ በደስታችን ጊዜ አብረው የሚበሉና አብረውን የሚጠጡ፣ ወዳጆቻችን ብዙ ናቸው፡፡ በሳቃችን ጊዜ አብረውን የሚስቁ ብዙ ብዙ ብዙ ናቸው፡፡ በደስታችን ጊዜ፣ ዙሪያችንን ሞልተው የሚያሳስቁንና የሚያጨበጭቡ እጅ ብዙ ናቸው! ባማረብን ጊዜ የሚያዳንቁን፣ ባለፈልን ጊዜ የሚያሞካሹን፣ እጅ ብዙ ናቸው

ወዳጄ ሆይ፣ ከከፍታው ኋላ ዝቅታ አለና፣ ከሳቁ በኋላ ለቅሶውም አለና ለዚህ ወቅት የሚሆን አብሮት የሚቆም ወዳጅ ማፍራትዎን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ ከአድማስ ባሻገር፣ አሁን ከሚያውቁት ዓለም ገና ያላዩት ሌላ ሌላ ዓለም አለና፣ ለዚያ ጊዜ የሚሆን እውነተኛ ወዳጅ ማፍራት መቻልዎትን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ ሲመች ብቻ ሳይሆን፣ ባልተመቸም ጊዜ ስለርስዎ የሚያስብ፣ የእርስዎን ትዝታ የአንገት ማተቡ፣ የጣት ቀለበቱ አድርጎ የሚዞር እውነተኛ ወዳጅ ማፍራት መቻልዎትን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ለአሕዛብ ለማድረስና ብዙዎችንም ለማዳን፣ ብዙ አብያተክርስቲያናትንም በእንባ በመከራ በመትከል እጅግ ከፍ ያለ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡  ነገር ግን ችግር ባጋጠመው ጊዜ፣ በመከራውና በስደቱ ጊዜ እንዲሁም በእስራቱ ጊዜ፣ ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም ትተውት ሄደዋል፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ምን በላ – ምን ጠጣ? ምን ደላው – ምን ከፋው? ያለው አልነበረም!
 
ወዳጄ ሆይ፣ የሰው ልጅ ነንና፣ ከጸሐይ በታች የሚኖር እንደ እኛው ሁሉ ሥጋና ደም የለበሰ አይዞህ ባይ፣ አይዞሽ ባይ ሊኖረን ያስፈልጋል! በሐዘናችን ወቅት ሊያጽናናን የሚችል፣ በደስታችንም ወራት አብሮን የሚደሰት፣ ሲከፋን ተከፍቶ፣ ስናለቅስ አልቅሶ የሚያስተዛዝነን ሰው ያስፈልገናል፡፡ ስለሆነም፣ ከከበቡዎትና አብረዎት ከሚገኙ ባልደረቦች መሀል፣ ከእልልታቸውና ከጭብጨባቸው መሀል፣ እውነተኛ ወዳጅ ማፍራት መቻልዎትን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ ከነዴማስ መሀል(4፡9)፣ ከነፊሎጎስና ከነሄርዋጌኔስ መሀል (1፡15)፣ ከነሄሜኔዎስና ፊሊጦስ መሀል(2፡17)፣ ከነእስክንድሮስ መሀል (2፡17)፣ ከነኢያኔስና ኢያንበሬስ መሀል(3፡8)፣ ከነአስቆሮቱ ይሁዳ መሀል፣ እንደነ ጢሞቴዎስ ያሉ፣ እንደነ ቄርቂስ፣ እንደነ ቲቶ፣ እንደነ ቲኪቆስ (4፡10-12) እንደነ ኤሪስጦስ፣ እንደነ ጥሮፊሞስ፣ የመሳሰሉ ግለሰቦች መኖራቸውን፣ ከቤተሰብም ደግሞ እንደነ ጵሪስቅላና አቂላ፣ እንደነ ሄኔሲፎሩ፣ እንደነ ኤውግሎስና ጱዴስ፣ እንደነ ሊኖስ ቅላውዲያም(1፡16፣ 4፡19፣ 21) መኖራቸውን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡

Wednesday, July 22, 2015

አለማመናችንን እርዳ!!!!!!

ዲቮሽን 315/07፥ ረቡዕ፥ ሐምሌ 15/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አለማመናችንን እርዳ!!!!!!

አምናለሁ፣ አለማመኔን እርዳ። ማርቆስ 9፡ 24

የእምነት ነገር በጣም ከባድና ሐሳባዊ ሆኖባችሁ ያውቅ ይሆን? በተለይም በጣም በሚያስፈልጋችሁ ነገር ላይ፣ በጣም በጉጉት በምትጠብቁት ነገር ላይ፣ ጌታ በተደጋጋሚ እየተናገራችሁ ለእናንተ ግን ርቆባችሁ ይሆን? ጌታ ከተናገራችሁ ነገር በተቃራኒው በሕይወታችሁ እየሆነ ይሆን?

ሕይወታችሁን በቅድስና እየመራችሁ፣ ቃሉ እንደሚላችሁ እየተመላለሳችሁ፣ በሥፍራችሁ ሆናችሁ ሳለ፣ ነገሮች ግን እየተበላሹባችሁ ይሆን? እግዚአብሔርን ከመጠበቅ የተነሳም የመዛልና የስፍና ነገርስ ይሰማችሁ ይሆን? “ስለማታምኝ ነው/ ስለማታምን ነው እግዚአብሔር የተናገረሽን/ የተናገረህን ያልመለሰላችሁ” ተብላችሁስ በወገኖች ተመክራችሁ ይሆን?

እንግዲህ ነገሩ ካለማመናችን ከሆነ ለምን ተስማምተን አንጸልይም? እንዲህ በማለት፣ አብ አባት ሆይ፣ እኔ የማውቀው ማመኔን ነው፣ እኔ የማውቀው አንተን ተስፋ ማድረጌን ነው፣ ነፍሴ የምትመሰክርልኝ ኤልሻዳይነትህን ማመኔን ነው። ደግመህ ደጋግመህ በልዩ ልዩ መንገድ የተናገርኸኝ ነገር ያልሆነው ካለማመኔ ይሆንን? ወደጄ ሆይ፣ እባክህ አለማመኔን እርዳ። በድካሜ ላይ ተገለጥ፣ ጥርጣሬየን የመንፈስህ እሳት ይብላውና፣ ዛሬ በአዲስ እምነትና ኃይል ሙላኝ። ባለፈው ዘመኔ ሁሉ እንዳደረከው፣ እለምንሃለሁ፣ በወደድከው፣ ባከበርከው በልጅህ በኢየሱስ ስም እለምንሃለሁ፣ አለማመኔን እርዳ። ወደ ፈቃድህም አስገባኝ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 51 ቀን ቀርቶታል፡፡

አንድም አልጠፋብኝም!!!!

ዲቮሽን 314/07፥ ማክሰኞ፥ ሐምሌ 14/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አንድም አልጠፋብኝም!!!!

ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም። ዮሐ 18፡9

ጌታን ካገኘን ጀምሮ እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን ያመጣቸው እጅግ ዓይነት በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። የኛ ሕይወት አመቺም በሆነ መንገድ ይለፍም አይለፍም፣ የኛ ጸሎት ይመለስም አይመለስም፣ ክርስቲያን በመሆናችን ብቻ አምነውን ለእርዳታ ወደ እኛ የመጡ ብዙ ወንዶችና ሴቶች፣ ታናናሾች እና ታላላቆች ይኖራሉ።

ምክራችንን፣ ጸሎታችንን፣ ገንዘባችንን፣ እንክብካቤያችንን፣ ጊዜያችንን .... ፈልገው “እሱ አለ/እሷ አለች” ብለው የፈለጉንን ሰዎች የት አድርሰናቸው ይሆን? የክርስትና ሕይወት አቀበት ሲሆንብን መንገድ ላይ ጥለናቸው ይሆን?
ሲርበን፣ ሲጠማን፣ ስንታረዝ፣ በሕይወታችን ላይ ሰልፍ ሲበዛብን የራሳችሁ ጉዳይ ብለን አባረናቸው ይሆን?

እግዚአብሔርስ እነዚያን ሰዎች ያለነገር ወደ ሕይወታችን ዝምብለው ያመጣቸው ይመስላችኋል? ከፍቷቸው፣ ሆድ-ብሷቸው፣ ማልቀስ አምሯቸው እኛን ከሰው ሁሉ መርጠው የተጠጉንን ሰዎች የት አድርሰናቸው ይሆን?

እግዚአብሔር ሌላ ወገን ሰጣቸው ይሆን? ወይስ የሚያነሳቸው ጠፍቶ ተንከራተው ቀርተው ወይም ሞተው ይሆን? ምናልባት ጌታስ ድንገት ቢጠይቀን፣ እንደ ኢየሱስ፣ “ከሰጠኸኝ ከእነዚህ አንድም አልጠፋብኝም” ዮሐንስ ወንጌል 18፡9 የማለት ኃይል ይኖረን ይሆን? መልሱን ለእያንዳንዳችሁ ልተወው። ዛሬም ሌላ ቀን ነውና፣ ግን ካሁን በኋላ ልብ እንበል።

አባት ሆይ፣ በአንድም በሌላም ምክንያት ወደእኛ ያመጣሀቸውን ሰዎች አባርረናቸው እንደሆነ፣ ወይም በራሳችን ጉዳይ ተጠምደን፣ የነፍሳትን ነገር ችላ ብለን እንደሆነ፣ ወይም ስልካችንን እያጠፋን፣ በመንገድም አይተን እንዳላየን አልፈናቸው እንደሆነ፣ በውጤቱም የእነዚያ ሰዎች ሕይወት ተበላሽቶ እንደሆነ፣ ዛሬ እለምንሀለሁ፣ እኛንም ይቅር በለን፤ እነሱንም ከወደቁበት የሚያነሳውን መንፈስህን ላክላቸው። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 52 ቀን ቀርቶታል፡፡

ባለስልጣን!!!!

ዲቮሽን 313/07፥ ሰኞ፥ ሐምሌ 13/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ባለስልጣን!!!!

ስልጣን ከሰማያት እንደሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል። ዳንኤል 4፡27

የመጨረሻው ዘመን አሠራር እጅግ በረቀቀ እና በተወሳሰበ ስልት ሕይወታችን እያመሰ ያለበት ወቅት ላይ ነን። አማኝ ነን ለምንል ለእኛም ቋንቋችንን እየደበላለቀ፣ እርስ በርሳችን ለእግዚአብሔር ቤት ሥራ እንዳንተጋ ያደረገበት ወቅት ነው።

በሚያልፍና በሚጠፋ ነገር ውስጥ ተተብትበን፣ የክርስቶስን ሰላም እንደ ቀላል ያቃላለንበት ወቅት ነው አሁን። አንዳንዴ ራሳችን ለራሳችን ምን ነክቶኝ ነው እንዲህ የሆንኩት? እስክንል ድረስ በማይገባን ሥፍራ፣ የማይመጥነን ስራና አመል እያሳየን፣ ትእግስት እየጎደለን፣ ስንባዛን ራሳችንን እናገኘዋለን።

በቤተክርስትያንም ያለው አሠራር ደስ የሚያሰኘውንም ያህል፣ ልብን የሚያዝል ነገር አለው። አልፎተርፎም እግዚአብሔር አለ ወይስ የለም? በዚህ ጊዜ ምን እየተከናወነ ነው? ለኔስ ሆነ ለቀሪው ቤተሰቤ፣ ለራእየና ለሀገሬ ምን ተስፋ አላት? እያልን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የምንመላለስበት ሰዓት ነው አሁን። አንድ ነገር እነግራችኋለሁ፣ እግዚአብሔር አለ። እየሆነ ያለውንም ነገር ሁሉ ያውቀዋል። የተበላሸ የቤተክርስትያናችንንም ሆነ የሕይወታችንን ክፍል ያውቀዋል። መፍትሔ ፍለጋም ወደቀኝ እና ወደግራ ስንባክንም ያውቀዋል። የጨለማው ገዢ በመጨረሻው ሰዓት ትንቅንቅ ላይ ስለሆነ ራሳችሁን ባልተገባ ቦታ ላይ ብታገኙት አይግረማችሁ።

ስልጣን ያለው በሰማይ ነው። የሰማይና የምድር ፈጣሪ አንድ እግዚአብሔር ይደርስልናል። እኛ ብቻ በድካምም ውስጥ ብንሆን፣ አባት ሆይ እባክህ ዓይኖቼን ክፈት እያልን እንጸልይ። ወደ ቀኝ ወደ ኋላ ማለታችንንም ትተን ወደሰማይ ብቻ እንመልከት። እጅ እንስጥ። መፍትሔ ያለው ከሰማይ ነው። መላ ያለው ከአብ ዘንድ ነው። ከሌላ ከየትም የለም። እኛ ስልጣን ከሰማይ መሆኑን እንወቅ እንጅ፣ እኛ እግዚአብሔርን እንፈልገው እንጠጋጋው እንጅ፣ እንጠጋጋው እንጅ፣ ያን ጊዜ የተዝረከረከው ነገር ሁሉ ቦታ ቦታውን በራሱ ጊዜ ይይዛል።

አባት ሆይ፣ ግሩም መካሪ ስለሆንክልን ተባረክ። ወዳጅ ሆይ ስምህ ለዘላለም ይባረክ። መንፈስቅዱስ ሆይ፣ ባስጨነቁን ላይ በእሳት ስለምትገለጥ ተባረክ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 53 ቀን ቀርቶታል፡፡

አወሩ!!!!!

ዲቮሽን 312/07፥ እሁድ፥ ሐምሌ 12/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

አወሩ!!!!!

እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ። ሐዋ 15፡ 4

በዘመናችን ጌታ ያደረገልን ነገር ብዙ ነው። ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጅ አድርጎን፣ ውሸተኛ ስንሆን በልጁ በኢየሱስ እውነት ሸፍኖን፣ በሽተኞች ስንሆን በመገረፉ ቁስል ፈውሶን፣ ከርታቶች ስንሆን በእቅፎቹ ይዞን፣ የማንመች ለሆንነው ለኛ፣ የሚመች ሆኖ፣ ለሚቆረቁረው ማንነታችን የማይቆረቁር ስሙን ሰጥቶን፣ ሌቦች፣ ዘማውያን፣ ተሳዳቢዎች ስንሆን... ተሸክሞን ይኼው አለን።

እስከዛሬ ድረስ፣ እሳከሁኗ ደቂቃ ድረስ፣ ያለነው ጌታ ተጠንቅቆልን ነው። መንገድ የጠፋን ቅብዝብዞች ሆነን እያለ፣ መንገድ ሆኖልን። በምድረበዳው፣ በሐሩር እና በቁሩ፣ በዳገት እና ቁልቁለቱ፣ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል፣ እዚህ ያረሰን እግዚአብሔር ነው። ጠላት ሊያበራየን ሲመጣ፣ ጌታ ከልክሎልን እስካሁኗ ሰከንድ ድረስ አለን።

ታዲያ ዛሬ ለገጠመን ነገር እንዴት እንዴት ምንም እንዳልተደረገለት ሰው ጨለማ ይውጠናል? ታዲያ ዛሬ ላላንበት ነገር እንዴት ልባችን ይዝላል? በጉልበታችን፣ በእውቀታችን፣ በገንዘባችን አልኖርንም አይደል? ስለዚህ፣ አይዞን፣ አይዟችሁ። ድብርት፣ ተስፋ መቁረጥና፣ አዚም ሲጫጫናችሁ/ ሲጫጫነን እንዲህ አድርጉ። እግዚአብሔር በሕይወታችሁ ላይ ያደረገላችሁን ነገር ተጨዋወቱት።

ብቸኝነት ይዟችሁ፣ የምታካፍሉት ሰው ከሌላችሁ እንኳን፣ ወደ ሰማይ ቀና ብላችሁ አሰላስሉት። አስቡት። ለልቦናችሁ ንገሩት። እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ፣ ያ የምሕረት አምላክ አላረጀም፣ አልደከመም፣ አልሰለቸም። በደጅ ነው። በርቱ።
አባት ሆይ፣ ስለሰማህኝ አመሰግንሀለሁ። በእርግጥ ያደረክልን ነገር ብዙ ነውና እሱኑ እንድንጨዋወተው እንድናሰላስለው ስለመከርከን ተባረክ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 54 ቀን ቀርቶታል፡፡

ሰላምን ያደርጋል!!!!!

ዲቮሽን 311/07፥ ቅዳሜ፥ ሐምሌ 11/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

ሰላምን ያደርጋል!!!!!

የሰው አካሔድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ እንደሆነ፣ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል። ምሳሌ 16፡7
አንዳንድ ጊዜ በሕይወት መንገድ ላይ በብዙ ጉዳዮች ተጠምደን እንውላለን። በዚህ በማሕበራዊ መስተጋብራችን ውስጥም የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ያጋጥሙናል። የሚወዱን፣ የሚጠሉን፣ ሐሳባችንን የሚደግፉ፣ ሐሳባችንን የሚቃወሙ፣ በገንዘም ሆነ በምክር የሚረዱን ወይም ደግሞ ያለንንም ነገር ቢሆን የሚወስዱብን፣ ልባችን የሚያርፋባቸው፣ ወይም በነገር እና በሐሜት ልባችንን የሚያደሙ .... ብቻ እጅግ በርካታ አይነት ሰዎች ይገጥሙናል።

በዚህ ጋጋታ ውስጥም ይህ አመጸኛ ስጋችን አንዳንዴ በስሜታዊነት ጎል ያስገባንና ለሰዎች መጫወቻ እንሆናለን። ጉዳይ ልናስፈጽም ብንል እየተሳደብን፣ መልእክት እናድርስ ብንል እየተቆጣን፣ ብቻ ግራ ያጋባናል-ይህ ስጋችን። ያን ጊዜ፣ ሰዎች እንኳን ሊታገሱን እስከማይችሉ ድረስ ይጸየፉናል፣ ወይም ደግሞ ይጠሙብናል። ክብር ለመንፈስቅዱስ ይሁንና፣ ወጀቡም ማእበሉም ሲያንገላታን አጽናኛችን አይጥለንም፤ ወደ ቃሉ ይመልሰናል።

ከዚያም በሁሉ ሙሉ የሆነው ንጹህ የእግዚአብሔር ቃል ይመክረናል፤ እንዲህ ሲል፣“ የሰው አካሔድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘ እንደሆነ፣ በእርሱና በጠላቶቹ መካከል እንኳን ሰላምን ያደርጋል”። ምሳሌ 16፡7

እንዲህ ያለ ነገር ገጥሟችሁ ያውቅ እንደሆነ ግዴላችሁም ወደ ቃሉ ተመለሱ። ጌታ ለዘላለም ስለማይጥለን ከእሱ ጋ እንስማማ፣ ደስ የሚያሰኘውንም እንፈልግ፣ ያን ጊዜ ብልሽትሽቱ የወጣው ማሕበራዊ ሕይወታችን፣ የሥራ ሁኔታችን፣ የጠሉን ሰዎች ሁሉ በስምምነት ከእኛ ጋር መኖርና መስራትን ይፈቅዳሉ።

ባባዬ፣ ደግ ነህና እወድሀለሁ። ደግ ስለሆነው ቃልህም ተባረክልኝ። ቁጥር ስፍር ስለሌለው ምክርህም አመሰግንሀለሁ። ሰምተህኛልና ተባረክ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 55
ቀን ቀርቶታል፡፡

Friday, July 17, 2015

እናስለምድ!!!!

ዲቮሽን 310/07፥ አርብ፥ ሐምሌ 10/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


እናስለምድ!!!!


እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ። 2 ጢሞ 4፡7

በዚህ በመጨረሻው ዘመን ዓለምን ለመምሰል ደፋ ቀና በማለት ስንደክም እንውላለን። በዓለም ያለው ሁሉ እንዳይቀርብን፣ ራሳችንን እናተጋለን። በዓለም ያሉትን ከመማረክ ይልቅ እኛ ራሳችን በእነሱ ተማርከን፣ በቤተክርስትያናችን፣ በቤተሰባችን፣ በሥራ ቦታችን፣ በአገልግሎታችን፣ በማሕበራዊ ሕይወታችን . . . ያለንን የሞያም ሆነ የገንዘብ ዓቅም አሟጠን ዓለምን ለመምሰል በልዩ ብርታት ስንሠራ እንገኛለን። የዓለም እውቀቶች በቤተክርስትያናችን እና በቤተሰባችን ላይ ሠርገው ገብተው፣ እምነት እና ስነልቦና ተምታቶብን፣ እንደዘመኑ ለመሆን የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም። አሳዛኙ ነገር ደግሞ፣ ለምናደርገው ነገር ሁሉ ተስማሚ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱሳችን ማግኘታችን ነው።

መጽሐፍ የሚለን ግን፣ “እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ” ነው። አሁን ያለንበት ይህ የማብቂያው ዘመን፣ ለሁላችንም እጅግ አዳጋች እና ፈታኝ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው። ግን የሚያዋጣው እግዚአብሔርን መምሰል ነው። እግዚአብሔርን መምሰል ማለት ምን ማለት ነው? ለሚለው መጽሐፍ ቅዱስ ምላሽ ስለሚሰጠን፣ ወደ ቀድሞው ፍቅራችን፣ የዋህነታችን፣ ትህትናችን፣ እውነተኛታችን፣ ገራገርነታችን ተመልሰን፣ በፍጹም ንስሐ ወደ ቃሉ እንመለስ።

አባት ሆይ፣ ሁልጊዜም ቢሆን ስለማትሰለቸን ተመስገን። በዓለምና በውስጧ ባሉት ነገሮች መማረካችን፣ መፍዘዛችን፣ መወሰዳችን እውነት ነው፤ ቢሆንም ግን፣ ዋጋ የከፈልክብን ልጆችህ ስንጠፋ ዝም አትበለን። አንተን ለመምሰል፣ እለት እለት እራሳችንን ለማስለመድ እንፈልጋለን። ስለዚህ ዛሬ ጸጋህ ይደግፈን፣ አሁን መንፈስህን ላክልንና እባክህ ወደመገኘትህ አስገባን? ሰምተህኛልን ተባረክ።

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 56 ቀን ቀርቶታል፡፡

Thursday, July 16, 2015

የመጨረሻው እይታ !!



የኢትዮጵያ የሕይወት ብርሃን ቤተ ክርስቲያን
ዲቮሽን 309/07 ሓሙስ ሓምሌ 09/07

ዲቮሽን 309/07 ሓሙስ ሓምሌ 09/07 
( ወንድም ጌታሁን ሓለፎም )


የመጨረሻው እይታ !!

የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ እንዲሁም ነን ፡፡ ” 1 ዮሓ 3-1

ክርስቲያን መባላችን - ጉዳዩ መንግስተ ሰማያትን መውረስ እና የዘላለም ህይወትን ማግኘት የእግዚአብሔር ልጆች ተብሎ የመጠራት እንዲሁም በግዚአብሔር እውቅናን የማግኜት እና ከሀሳቡ ጋር የመስማማት እውነት እስከሆነ ድረስ የመጨረሻውን እና ውድ የሆነውን ስጦታ መቀበልን የመሰለ ሌላ ወሳኝ እና አስፈላጊ አማራጭ አይኖርም ! እሱም ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው !

ለምን ቢባል - ወደ እግዚአብሐር አብ ለምምጣትና ለመጠጋት አባ አባት ብለን በልጅነት ስልጣን እንድንጠራው እና እንድንመላለስ በፊቱም እንደ ልጅ እንድንገባ እና እንድንወጣ የሚያስችለንን ድፍረት ለማግኘት ከመሲሁ በስተቀር ሌላ መንገድ እግዚአብሔር አብ አላዘጋጀልንም እና ነው !

ይህ ደግሞ የራሱ የእግዚአብሔር ምርጫ እና ሃሳብ እንዲሁም የተቀደሰ ቸርነቱ ነው ፡፡

እግዚአብሔር እኛን እንደ ልጆች ሊቀበለን ሊያቀርበን ሲፈልግ እንደ መንገድ እና ድልድይ አድርጎ ሊጠቀም የወደደው አንድያ ልጁን ስጦታ አድርጎ ለኛ በመስጠት ነው ፡፡

ለዚህም ነው ሓዋርያው ዮሃንስ - እንዴት ያለ የላቀ እንዴት ያለ የተመረጠ እንዴት ያለ የተለየ ስጦታ እንደተሰጣችሁ እና እንደተቀበላችሁ እዩ የሚለን ፡፡  ስጦታ ከሌላው ከተመረጠው ከብር ከእንቁ ይበልጣል ! ይህ። ስጦታ ከመላእክት ከቅዱሳን ከፍጥረታት ክብር ይበልጣል !

ስለዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር ምን ያህል የላቀ እንደሆነ አስተውሉ እዩ ተረዱ !

ስጦታው የመጣው በናንተ ልክ እናንተ በምትመጥኑት መለኪያ መጠን ሳይሆን በራሱ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ሚዛን እና ፈቃድ የመጣ ነው ፡፡

ስለዚህ መንፈሳዊ አይንህ ይገለጥ እና የእግዚአብሔርን እቅድ እይ አንተን ስለወደደህ መለኮት የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ሰጠህ ፡፡

ስለዚህ መንፈሳዊ አይንህ ተገልጦ የተሰጠህን ስጦታ አስትውል

እውነት ነው ወገኖቼ ሰው ክርስቶስ እየሱስን ብቼኛ ጌታ እና ብቸኛው አዳኝ አድርጎ በህይወቱ ላይ ለመሾም እና ለመከተል - መንፈሳዊ አይን እና መረዳትን ይጠይቃል ፡፡ በእግዚአብሔር የተወደደ እና የተመረጠው ሃሳብ የትኛው ነው ? ብሎ እራስን መጠየቅን እና እውነቱን የመቀበል ጀግንነትን ይጠይቃል፡፡ ከምንም አይነት ትጽእኖ ነጻ የሆነ እንዲሁም በቃሉ ላይ የተመሰረተ እይታን ድፍረትን ይጠይቃል !

እንግዲህ እኛም ይህ እውነት ገብቶናል ብለን የጌታን መንገድ የምንሮጥ ቅዱሳኖች ይህን የከበረውን ስጦታና የእግዛብሔር ታላቅ ፍቅር የተገለጠበትን እውነት እንደሚገባ እንድንኖር ጸጋው እንዲያግዘን እንድንጸልይ እና በጽድቅ ለመኖር እራሳችንን እንድናዘጋጅ በጌታ ፍቅር እያሳሰብኩ


ሌሎች ደግሞ ይህ እውነት እንዲበራላቸው እና የእግዚአብሔርን ሃሳብ እንዲረዱ ከመናገር እና ከማሳሰብ ቸል አንበል እላለሁ፡፡  እየሱስ ጌታ ነው !