Tuesday, July 28, 2015

እንጮሃለን፣ እንድናለን!!!!!!

ዲቮሽን 320/07፥ ሰኞ፥ ሐምሌ 20/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)


እንጮሃለን፣ እንድናለን!!!!!!

በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው። መዝ 107፡ 28

ያው አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ስለሆንን፣ የጠላታችንን ውድቀት ልናይ፣ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ወዳሰበልን ልንገባ የተቃረብንበት ጊዜም ስለሆነ ያለን ብቸኛ አማራጭ በሰልፉ ልክ፣ በመከራችን ልክ፣ ወደ እግዚአብሔር መጮህ ነው።
ዙሩ ከርሯል ወገኖቼ!!!!!!!!

አንዳንዶቻን፣ ጭው ባለ በረሐ እየተቅበዘበዝን፣ የእግዚአብሔርን ክብር እየተራብን፣ እየተጠማን፣ ወደ ሰማይ እየጮህን ያለን ሰዎች አለን አይደል? እርሱ የተጠማችውን ነፍስ ያረካልና፣ የተራበችውንም ነፍስ ከበጎ ነገር ያጠግባልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶቻን፣ በብረት ሰንሰለት የታሰርን ፣ መውጫ መፈናፈኛ ያጣን፣ በጭለማ በጥልማሞት የተቀመጥን፣ የሚደግፈን፣ የሚያነሳን ያጣን፣ ከጉድጓድ ማን ያወጣናል የምንል፣ ከወህኒ ማን ይፈታናል የምንል፣ ወደ ሰማይ እየጮህን ያለን ሰዎች አለን አይደል? እርሱ የናሱን በሮች ይሰብራልና፣ የብረቱንም መቆርቆሪያ ይቆርጣልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶች ደግሞ፣ ከበደላችን የተነሳ ችግር ውስጥ የገባን፣ ሰውነታችን የምግብ አይነት የተጸየፈች፣ ወደ ሞትም ደጃፍ የቀረብን አለን አይደል? ቃሉን ልኮ ይፈውሰናል፣ ከመቃብርም አፋፍ ይመልሰናልና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አንዳንዶቻችን ደግሞ፣ ከነፋሱና ከማዕበሉ የተነሳ ሐሞታችን የፈሰሰ፣ እንደ ሰከረ ሰውም የምንንገዳገድ፣ መላው ጠፍቶብን የምናደርገውን ያጣን አለን አይደል? እርሱ ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ ያደርጋል፣ የባሕሩንም ሞገድ ረጭ ያደርጋል፣ ወዳሰብነውም ወደብ እንደርሳለንና፣ ወደ እግዚአብሔር እንጮሃለን!!!!!!

አባት ሆይ፣ እጆቻችንንም ሰልፍ፣ ጣቶቻችንንም ዘመቻ ስላስተማርክልን፣ ወደ ምልጃ ጸሎትም፣ ወደ ጩኸትም ስላስገባህን ተባረክ። ሁሉ ለስምህ ክብር ይሁን፣ ሰምተህኛልና ተባረክ። አሜን!!!!!!

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 46 ቀን ቀርቶታል

No comments:

Post a Comment