ዲቮሽን 322/07፥ ረቡዕ፥ ሐምሌ 22/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ማነው የሚለየን?????????????
ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ሮሜ 8፡35
በዚህ ምርጫ እና እድል በበዛበት ዓለም፣ መጀመሪያ የያዝነውን የክርስቶስን ፍቅር ይዞ መቆየት ትግል ሆኖብናል። ያንን፣ በእንባና በልቅሶ የምንወደውን ኢየሱስን፣ አሁን በበርካታ ነገሮች ለውጠነዋል።
በድፍረት እናገራለሁ፡ ኢየሱስን በዓለምና በውስጧ ባሉት ነገሮች ተክተነዋል። በፋሽን ተክተነዋል፣ በምቾት ተክተነዋል፣ በድሎት ተክተነዋል። በዝና፣ በእኔ አውቃለሁ ባይነት ተክተነዋል፣ በእውቀታችንም ተክተነዋል፣ በመኪናችን፣ በቤታችን፣ በትዳራችን፣ በቆንጆ ባሎቻችንና ሚስቶቻችን፣ በዘናጭ ልጆቻችን ተክተነዋል፣ በውጭ ሐገር ጉዞዎቻችን ተክተነዋል፣ በዲግሪና በማስተርሳችን፣ በፒኤችዲያችንንና በፕሮፌሰርነታችን ተክተነዋል።
ደግሜ እላለሁ፡ ያንን የሚወደንን፣ ያንን ምስጢረኛችንን ኢየሱስ፣ ያንን የምድረበዳችን ኢየሱስን፣ ያ በተዘጋው ቤታችን የመጣውን ኢየሱሰን፣ ያ የዘላለም ወዳጃችንን ኢየሱስን፣ በሞራል ትምህርት ለውጠነዋል፣ በሳይኮሎጂ ነክ ትምህርት ለውጠነዋል።
ወገኖቼ፣ እኛ እኮ ከኢየሱስ ጋር ብዙ ምስጢር ያለን ሰዎች ነን። ያልተቻለውን ችሎልን፣ ያ የሚከረፋውን እና የሚሸተውን ቁስላችንን ያጠበልንን ኢየሱስን፣ ያ ክፋታችንን እና ሞታችንን ሁሉ ወደ ህይወት የቀየረልንን ኢየሱስን፣ ያ ማንም ወዳጅ እና ሰው ሲጠላን ያልጠላንን ኢየሱስን ለምን ዛሬ ቸለል ቸለል አልነው?
ጳውሎስ፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ችግር ነው ወይስ ስቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ረሀብ፣ ወይስ ዕራቁትነት፣ ወይስ አደጋ ወይስ ሰይፍ? ሮሜ 8፡35 እንደሚላቸው ሳይሆን፣ ዛሬ እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፡ ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማነው? ጥጋብ ወይስ ምቾት፣ ወይስ የተንጣለለ ማረፊያ ቤት፣ ወይስ የሚቀያየሩ ልብሶች፣ ወይስ መንግሥታት ያስጠበቁልን ደህንነታችን?
እላችኋለሁ፤ ማንም አይለየን!!!! ማ----ን-----ም!!!!!!
አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ ላንተ የሚሳንህ ነገር የለምና፣ እለምንሃለሁ ወደ ቀደመው ፍቅራችን እና የዋህነታችን መልሰን። በእርግጥ ታደርገዋለህና ተባረክልኝ።
--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 44 ቀን ቀርቶታል
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 44 ቀን ቀርቶታል
No comments:
Post a Comment