Tuesday, July 28, 2015

እለምንሃለሁ!!!!!!

ዲቮሽን 319/07፥ እሁድ፥ ሐምሌ 19/07 ዓ/ም
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)



እለምንሃለሁ!!!!!!

ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ። ዘፍጥረት 13፡9

እንኳን በሰው ሃገር ቀርቶ በትውልድ ሃገራችንም የስጋ ዘመዶቻችንን እንፈልጋለን። አጠገባችን እንዲሆኑ፣ ደስታንም ሆነ ሃዘንን አብረውን እንዲካፈሉን እንሻለን። አብርሃም ግን ሲፈራ ሲቸር ፣ አንድ ቀን ጨከነና፣ ይህንን የማያዛልቅ፣የትም የማያደርስ ዝምድና ሊለየው ፈለገ። ሒድ ብሎ ሎጥን ሊያባርረው አልቻለምና፣ “ከእኔ ትለይ ዘንድ እለምንሃለሁ”። ዘፍጥረት 13፡9 ብሎ ይለማመጠዋል።

እንዲያው ዛሬስ በኛ ዘመን እንደ ሎጥ የሆኑብን ጨክነን ልናርቃቸው ያልቻልናቸው አመሎች ይኖሩብን ይሆን? እግዚአብሔርን እያመለክን ግን ደግሞ ብዙ ጸያፍ የሆኑ ነገሮች፣ አስተሳሰቦች አብረውን ተጣብቀው ይኖሩብን ይሆን?


ለምሳሌ፣ ጫት መቃም እየወደድን፣ መጠጣት እየወደድን፣ ማመንዘር እየወደድን፣ መዋሸት እየወደድን፣ መዝፈን እየወደድን፣ ማማት እየወደድን ..... በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔርን ማምለክ እንፈልግ ይሆን? እንዲያው ምናልባት እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ ያለን ሰዎች እንኖር ይሆን? የምንወዳቸው ክፉ ልምምዶቻችን የእግዚአብሔርን ክብር እንዳናይ ከልክለውንስ ቢሆን? መቼም ለእግዚአብሔር የሚያቅተው ነገር የለምና፣ ለምን ተስማምተን አንጸልይም?

አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ በሕይወታችን ላይ ተጣብቀው ያሉ የተለያዩ የምንወዳቸውን ሐጢያቶች እባክህ እንድንጠላቸው እርዳን? ካለነሱ መኖር የሚያቅተን የሚመስለንን፣ ለስጋችን የሚመቹንን ክፋቶች፣ ወዳጄ ሆይ አንተ ቻልና እባክህ ከእኛ አርቃቸው? እንድንጠላቸው አድርገን? የሚጣፍጡንን ሐጢያቶቻችንን፣ እንደ ማር ወለላ የሆኑብንን ከንቱ ልማዶቻችንን እባክህ አንተ በስልጣንህ ከእኛ አርቃቸው? እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ እንዳለ ዳዊት (መዝ 51፡7)፣ ወዳጄ ሆይ፣ ሥጋችንን ባይፈቅድ እንኳን እንደ ሕጻን ልጅ ገርፈህ ዛሬ እጠበን። አባብየ፣ ታደርገዋለህና ተባረክ።

--------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 47 ቀን ቀርቶታል፡፡

No comments:

Post a Comment