ዲቮሽን 316/07፥ ሐሙስ፥ ሐምሌ 16/07
ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
እንባዎትን አስታዋሽ – አለን?
እንባህን እያሰብሁ በደስታ እሞላ ዘንድ ላይህ እናፍቃለሁ (2 ጢሞ 1፡4)።
ወዳጄ ሆይ፣
በአካል በዓይነ ሥጋ ሊያይዎት የሚናፍቅ፣ ወዳጅ ይሁን ዘመድ አሊያም የቅርብ ጓደኛ ወይም የአገልግሎት ባልደረባ አለዎት? ስለርስዎ
የሚያስብ፣ ስለጤንነትዎ ስለደህንነትዎ፣ ስለሁለንተናዎ ስለሳቅ ደስታዎ የሚገደውና ትዝታ ያለው ሰው አለዎት? ዓይንዎትን ለማየት ጉጉት ያደረበት፣ ፊትዎትን ለማየት ናፍቆት ያደረበት፣ ሲስቁ
ሲያለቅሱ ከርስዎ ጋር ለመሆን ፍላጎት ያለበት ሰው በእውነት አለዎትን?
ወዳጄ ሆይ፣
ሐዋርያ ጳውሎስንና ጢሞቴዎስን ያስቡ! የግንኙነታቸውንና የፍቅራቸውን መጠን፣ የመቀራረባቸውንና የመተሳሰባቸውንም
ልክ ያስቡ! የሁለቱም
ወዳጆች ፍቅር ስንመለከት ሲገናኙም በእንባ ሲለያዩም በእንባ ነው! ግንኙነታቸው ከሰላም ጊዜ እስከ መከራና ብሎም እስከ ስደት፣ እንዲሁም ከነጻነት
እስከ ወኅኒ ቤት ይዘልቃል፡፡
ወዳጄ ሆይ፣ በሰላም ጊዜ፣ ሁሉ ምቹ በሆነ ጊዜ፣ ወዳጆቻችን ብዙ ናቸው፡፡
በደስታችን ጊዜ አብረው የሚበሉና አብረውን የሚጠጡ፣ ወዳጆቻችን ብዙ ናቸው፡፡ በሳቃችን ጊዜ አብረውን የሚስቁ ብዙ ብዙ ብዙ ናቸው፡፡
በደስታችን ጊዜ፣ ዙሪያችንን ሞልተው የሚያሳስቁንና የሚያጨበጭቡ እጅ ብዙ ናቸው! ባማረብን ጊዜ የሚያዳንቁን፣ ባለፈልን ጊዜ የሚያሞካሹን፣ እጅ ብዙ ናቸው!
ወዳጄ ሆይ፣ ከከፍታው ኋላ ዝቅታ አለና፣ ከሳቁ በኋላ ለቅሶውም አለና ለዚህ
ወቅት የሚሆን አብሮት የሚቆም ወዳጅ ማፍራትዎን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ ከአድማስ ባሻገር፣ አሁን ከሚያውቁት ዓለም ገና ያላዩት ሌላ
ሌላ ዓለም አለና፣ ለዚያ ጊዜ የሚሆን እውነተኛ ወዳጅ ማፍራት መቻልዎትን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡
ወዳጄ ሆይ፣ ሲመች ብቻ ሳይሆን፣ ባልተመቸም ጊዜ ስለርስዎ የሚያስብ፣ የእርስዎን
ትዝታ የአንገት ማተቡ፣ የጣት ቀለበቱ አድርጎ የሚዞር እውነተኛ ወዳጅ ማፍራት መቻልዎትን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ለአሕዛብ ለማድረስና ብዙዎችንም ለማዳን፣ ብዙ
አብያተክርስቲያናትንም በእንባ በመከራ በመትከል እጅግ ከፍ ያለ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ነገር ግን ችግር ባጋጠመው ጊዜ፣ በመከራውና በስደቱ ጊዜ እንዲሁም በእስራቱ
ጊዜ፣ ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም ትተውት ሄደዋል፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር ምን በላ – ምን ጠጣ? ምን ደላው – ምን ከፋው? ያለው
አልነበረም!
ወዳጄ ሆይ፣ የሰው ልጅ ነንና፣ ከጸሐይ በታች የሚኖር እንደ እኛው ሁሉ ሥጋና
ደም የለበሰ አይዞህ ባይ፣ አይዞሽ ባይ ሊኖረን ያስፈልጋል! በሐዘናችን ወቅት ሊያጽናናን የሚችል፣ በደስታችንም ወራት አብሮን የሚደሰት፣
ሲከፋን ተከፍቶ፣ ስናለቅስ አልቅሶ የሚያስተዛዝነን ሰው ያስፈልገናል፡፡ ስለሆነም፣ ከከበቡዎትና አብረዎት ከሚገኙ ባልደረቦች መሀል፣ ከእልልታቸውና
ከጭብጨባቸው መሀል፣ እውነተኛ ወዳጅ ማፍራት መቻልዎትን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡ ከነዴማስ መሀል(4፡9)፣ ከነፊሎጎስና ከነሄርዋጌኔስ
መሀል (1፡15)፣ ከነሄሜኔዎስና ፊሊጦስ መሀል(2፡17)፣ ከነእስክንድሮስ መሀል (2፡17)፣ ከነኢያኔስና ኢያንበሬስ መሀል(3፡8)፣
ከነአስቆሮቱ ይሁዳ መሀል፣ እንደነ ጢሞቴዎስ ያሉ፣ እንደነ ቄርቂስ፣ እንደነ ቲቶ፣ እንደነ ቲኪቆስ (4፡10-12) እንደነ ኤሪስጦስ፣
እንደነ ጥሮፊሞስ፣ የመሳሰሉ ግለሰቦች መኖራቸውን፣ ከቤተሰብም ደግሞ እንደነ ጵሪስቅላና አቂላ፣ እንደነ ሄኔሲፎሩ፣ እንደነ ኤውግሎስና
ጱዴስ፣ እንደነ ሊኖስ ቅላውዲያም(1፡16፣ 4፡19፣ 21) መኖራቸውን እርግጠኛ ይሁኑ፡፡
No comments:
Post a Comment