Sunday, November 30, 2014

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#1) – የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት!


ዲቮሽን ቁ.81/07     እሁድ፣ ሕዳር 21/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#1) – የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት!

በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው (የሐዋ 2፡1-2)፡፡

ለጴንጠቆስጤነት ማንነት መሠረቱ፣ መፈተሻና መለኪያው የበዓለ ኀምሳ ቀን ነው፡፡ በዕለቱ የተከሰቱ ሁነቶችና ድርጊቶች፣ ስብከቶችና አስተምህሮዎች እንዲሁም ማናቸውም የዕለቱ አስተሳሰቦች ለጴንጠቆስጤነት ማንነት መለኪያና ማናጻጸሪያ ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ጴንጠቆስጤነት የሚጀምረው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው! ይህ ጥምቀት ጌታን እንደግል አዳኛቸው አድርገው በተቀበሉ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ክስተት ነው፡፡ ይህ ክስተት ሰዎች ጌታን በተቀበሉ ዕለት ወይንም በኋላ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መቀበል እና ጌታን መቀበል ሁለቱም የተለያዩ ልምምዶች ናቸው፡፡ በበዓለ ኀምሳ ቀን የሆነው ክስተትም ይህንን እውነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከአብ የተሰጠ የተስፋ ቃል ነው፡፡ ይህን የተስፋ ቃል መቀበል ውስብስብ ነገር አይጠይቅም፡፡ የሚያስፈልገው የተስፋ ቃሉን በጸሎት መጠበቅ ነው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጥቁርና ነጭ መገለጫው ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት›› ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ለአርባ ቀናት አብሮአቸው ቆይቶ ነበር፡፡ ጌታችን የምድር ቆይታውን ጨርሶ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ የነገራቸው ‹‹ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ›› ብሏቸው ነበር(የሐዋ 1፡4-5)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ከማረጉ በፊት የነገራቸውን ይህን ትምህርት ደቀመዛሙርቱ ተቀብለው ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ይጠብቁት የነበረው መንፈስ ቅዱስ በድንገት መጣ፡፡

ታውቃላችሁ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አቅጣጫው ከላይ ከሰማይ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ድንገተኛ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ድምጻዊ ነው፡፡ የሚደመጥ፣ የሚሰማ፣ ድምጽ አለው፡፡ ስለሆነም በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁ ድምጽ አውጥተው ሊጮኹ፣ ሊያጨበጭቡ …ይችላሉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እንደ አውሎ ንፋስ ነው –ነቅናቂ፣ አነቃናቂ፣ ቀስቃሽ፣ አንቀሳቃሽ፣ ወዝዋዥ አወዛዋዥ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ወንበራቸው ሊነቃነቅ፣ ሰውነታቸው ሊርገፈገፍ፣ ሊንዘፈዘፍና ሊንቀጠቀጠቀጥ ይችላል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ከሹም ፊት፣ ከሕዝብ ፊት፣ ከምናከብራቸውና ከምንፈራቸው ሰዎች ፊት ስንቆም ሰውነታችን በፍርሃት ይንቀጠቀጥ የለ? ስሜታችንን የሚነካ ደስታ ስንሰማ ድምጻችንን አውጥተን እልልታችንን ይሁን ጭብጨባችንን ወይንም ጩኸታችንን እንገልጽ የለ? ጥልቅ ሐዘን ሲያጋጥመን ድምጻችንን አውጥተን እናለቅስ የለ? ታዲያ፣ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ስሜታቸውን ቢገልጹ፣ ድምጻቸውን ቢያሰሙ ለምን እንደነቃለን?

ወገኖች ሆይ፣ የሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ድንገት ሲመጣ ክራባቱን አስተካክሎ፣ እግሮቹን አነባብሮ ተረጋግቶ የሚቀመጥ ሰው ይኖራል? ታዲያ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ድንገት ሲመጣ ሰዎች ቢንቀሳቀሱ፣ ቢወዛወዙ፣ ቢጮኹ ምን ያስገርማል? የበዓለ ኀምሳው ክስተት ይህን ያስተምራል!

          --------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Saturday, November 29, 2014

ክብር ከሕዝቡ ሲለቅቅ!

ዲቮሽን ቁ.80/07     ቅዳሜ፣ ሕዳር 20/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ክብር ከሕዝቡ ሲለቅቅ!


የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች። ወደሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች። ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም። እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው።(1ሳሙ 4፡19-21)፡፡

እህል ውሃቸው ካልጎደለ፣ እንቅልፍ መኝታቸው ከተደላደለ ለሌላው ነገር የማይጨነቁ ብዙሰዎች አሉ፡፡ ከምግብ ያለፈ ራዕይ፣ ከትዳር ያለፈ ጉዳይ፣ ከምድር ያለፈ ሰማይ የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የሕይወት ዓላማቸው፣ የመኖር ሕልማቸው በምድራዊ ነገር ላይ የተንጠላጠለ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡

በቤተክርስቲያን ውስጥም ብዙዎቹ ለአባልነቱ እንጂ፣ ለአስራት መባቸው እንጂ፣ እሁዱን ጠብቀው ለመመላለሳቸው እንጂ ለሌላው ነገር ደንታ የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ እንደ አሕዛብ ሁሉ ምኞታቸው መማር ሥራ መያዝ፣ ማግባትና መውለድ፣ መክበድና መክበር የሆነ ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች አሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተመቸው አልተመቸው፣ ደላው አልደላው፣ አሸነፈም ተሸነፈ፣ ከሰረም አተረፈ ደንታ የማይሰጣቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ አደገም አላደገ፣ ተነሳም ወደቀ፣ ግድ የማይላቸው አሉ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የፊንሐስን ሚስት እናስብ! ዙሪያዋን የሞሉ አጽናኞች ቢኖሩም፣ ወንድ ልጅ ብትወልድም፣ ታቦት ተማርኳልና፣ የእግዚአብሔር ክብር ከሕዝቡ ለቅቋልና መጽናናት አልቻለችም፡፡ ከወሊድ የምጥ ስቃይ፣ ከባሏ ሞት በላይ፣ ከአማቷም ሞት በላይ ነፍሷን ያስጨነቀው የእግዚአብሔር ክብር ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ክብሩ ከለቀቀ መጽናናት አይኖርም፡፡ ክብሩ የሌለበት ልጆች ቢወለዱም፣ አጃቢዎች ቢኖሩም፣ አባላት ቢበዙም መጽናናት ግን የለም፡፡ ክብሩ የሌለበት ፕሮግራም ቢበዛ፣ አምልኮ ቢንዛዛ መጽናናት አይመጣም፡፡ ክብሩ የሌለበት ሰባኪ–ዘማሪ፣ ወንጌል–አስተማሪ፣ እረኛ–መጋቢ፣ ወይንም ማናቸውም አገልጋይ ቢበዛ፣ ጎመን ቢጠነዛ እንጂ መጽናናት አይመጣም!  

ታውቃላችሁ፣ ክብሩ ሌለበት የሚቀርብ እልልታ፣ የጨረባ ሰርግ፣ የጨረባ ተስካር ነው! ክብሩ ሌለበት የሚደረግ ሽብሸባ ባዶ ዝማሜና ማዶና ማዶ ነው!  የእግዚአብሔር ክብር ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሲለቅ ዝማሬ እሮሮ፣ እልልታ መርዶ ነው!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Friday, November 28, 2014

አማካሪ ሰይጣን!

ዲቮሽን ቁ.79/07     አርብ፣ ሕዳር 19/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

አማካሪ ሰይጣን!

ጴጥሮስ ኢየሱስን ወደ ጎን ሳብ አድርጎ፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ›› እያለ ይገስጸው ጀመር፡፡ ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ዘወር ብሎ፣ ‹‹አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለሌለ መሰናክል ሆነህብኛል›› አለው (ማቴ 16፡22-23)፡፡

ጴጥሮስ ለኢየሱስ እየሰጠ ያለው ምክር ምርጥ ምክር ነው! ከደቀመዛሙርቱ ነጥሎ አውጥቶ፣  መከራ እንዳያይ፣ መስቀል እንዳይሸከም፣ ተሰቅሎ እንዳይሞት፣ ሞቶ እንዳይቀበር ልባዊ ምክሩን፣ ከምክርም ያለፈ ተግሳጹን እየሰጠ ነው! ይህ የወዳጅ ምክር፣ የወዳጅ ተግሳጽ ነውና ምርጥ ምክር፣ ምርጥ ተግሳጽ ነው!

ታውቃላችሁ፣ ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው! ይኼ ምርጥ ምክር፣ ይኼ ምርጥ ተግሳጽ ከወዳጅ ወይም ከሰማይ ሳይሆን ከወደቀ መልዐክ ከአናካዩ ሰይጣን ነው!

ታውቃላችሁ፣ በወዳጅ–ጓደኛ ተተግኖ፣ በደቀመዝሙር–ዘማሪ ተሸፍኖ፣ በተማሪ–አስተማሪ ተከልሎ፣ በአገልጋይ–በመሪ ተሰውሮ ሰይጣን ከመስመር ሊያወጣን ይችላል!

ታውቃላችሁ፣ በመንፈሳዊ ትምህርት፣ በስነ ፍልስፍና፣ በስነ አፈታት፣ በስነ ስብከት፣ በስነ አስተምህሮ፣ በስነቃላት ቁፋሮ፣ ሰይጣን ከመስመር ሊያወጣን ይችላል!

ወዳጄ ሆይ፣ ‹‹ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል (ምሳ 15፡21)። በምክር መጓደል እቅድ እንዳይፋለስ መማከር ይገባል፡፡ ነገር ግን በስ ምክክራችን፣ በስነ ስብሰባችን፣ በስነ ውሳኔያች፣ በስነዲፕሎማሲያችን፣ በስነ ዴሞክራሲያችን፣ በስነ እቅዳችን፣ በስነ ስትራቴጂያችን፣ በስነ ቴኦሎጂያችን፣ በስነ ‹‹ዶክትሪን››አችን፣ በስነ መተዳደሪያ ደንባችን ሰይጣን ሊጠቀም ይችላልና መጠንቀቅ ያሻል!

ወገኖች ሆይ፣ በየጊዜው ብዙ ስብሰባዎች፣ ብዙ ሥልጠናዎች፣ ብዙ ምክክሮች፣ ብዙ ውሳኔዎች ይደረጋሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ስንቶቹ የሰይጣን መጠቀሚያ ሆነው አልፈው ይሆን! ከእነዚህ መካከል ስንቶቹ የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ሐሳብ ስለሌለባቸው ይሆኑ? ከእነዚህ መካከል ስንቶቹ ፍልስፍና ብቻ፣ የሰው ሐሳብ ብቻ፣ የአእምሮ ነገር ብቻ፣ የቃላት ነገር ብቻ…ይሆኑ?

ወገኖች ሆይ፣ ከሥልጠናቻችንና ከምክክሮቻችን ስንቶቹ አሰናክለውንና አደናቅፈውን ይሆን? ከሥልጠናቻችንና ከምክክሮቻችን ስንቶቹ ከመስመር አውጥተውን፣ ከእውነት አስተውን፣ ከእምነት አስጥለውን ይሆን?

ወገኖች ሆይ፣ የወዳጅን ካባ ለብሶ፣ የወዳጅ ቋንቋ ተውሶ፣ በሚጣፍጥ ምላስ ተቅለስልሶ ነድፎ ከሚገድል አማካሪ ሰይጣን ጌታ ይሰውረን!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Thursday, November 27, 2014

ከሥጋና ከደም ጋር መማከር!

ዲቮሽን ቁ.78/07     ሐሙስ፣ ሕዳር 18/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ከሥጋና ከደም ጋር መማከር!

ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም(ገላ 1፡15-16)

ወደዚህ ምድር ከመምጣታችን አስቀድሞ፣ ገና በእናታችን ማህጸን ሳለን፣ ጌታ ያውቀናል፡፡ ከዚህ እውቀቱም የተነሳ ጸጋ ይሰጠናል፡፡ በዚህ ጸጋ እንድናገለግለውም ይጠራናል፡፡ በሚጠራን ጸጋና አገልግሎት ደግሞ ልጁ ኢየሱስ እንዲገለጥ ይፈልጋል፡፡ ኢየሱስ በሕይወታችን እንዲገለጥ ወድዶ ጌታ ከጠራን፣ እንግዲያውስ ከሥጋና ደም (ራዕይ አጨንጋፊ ሰዎች) ጋር መማከር አይገባም!

ወገኖች ሆይ፣ በኢትዮጵያ አብያተክርቲያናት ውስጥ ራዕይ አጨንጋፊ ሰዎች በዝተዋል! የተቀቡ ሲነሱ ተጋግዘው የሚደቁሱ፣ ነቢያት ሲነሱ ተረዳድተው የሚያጨነግፉ በዝተዋል!  ሐዋሪያት ሲወለዱ ተረባርበው የሚያወግዙ፣ ሰባኪዎች ሲነሱ ተባብረው የሚነቅፉ ሞልተዋል!

ታውቃላችሁ፣ የሥነመለኮት ተቋማት የብዙዎቹን ጸጋ ላጭተዋል! ሐይማኖታዊ ፍልስፍናዎች የእምነት ኃያላንን ቀርጥፈው በልተዋል! ክብሩን እንዲገልጡ የተጠሩ ብዙዎች ከኮሌጅ ሲገቡ ከሰው ይማራሉ! ክህደት፣ ጥርጣሬ፣ ጥያቄና ፍርሃት ለብሰው ይወጣሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ከሐዋሪያ ጳውሎስ እንማር! እግዚአብሔር ሲጠራው፣ ጠርቶም ሲቀባው፣ ከቴኦሎጂ ተቋም ለመማር አልገባም! የተቀበለውን ራዕይ ወደጎን አድርጎ፣ ከሥጋና ደም ጋር አልተመካከረም!  ትምህርት ቤቶቻችን ይላጩ እንደሁ እንጂ ጸጋን አይጨምሩም፡፡ ፈተና ሲሰጡን፣ አሳይመንት ሲሰጡን ጭንቅላትን እንጂ የልብን አያውቁም!

ታውቃላችሁ፣ ትምህርት ቤቶቻችን የመመረቂያ እንጂ የመዳንን ራስ ቁር በእኛ ላይ አይጭኑም!  በጸሎት ሕይወት፣ በጸጋ አገልግሎት፣ በእምነት ትምህርት ውጤት ድካም አሳይተን፣ ‹‹ብቁዎች ተብለን›› እንመረቃን፡፡ ሆኖም በምረቃ ዕለት የምንለብሰው ነገር ጥቁር ጋዋን እንጂ የጽድቅ ጥሩር አይደለም!  

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Wednesday, November 26, 2014

መንፈስ ቅዱስ ሲያስመልጥ!

ዲቮሽን ቁ.77/07     ረቡዕ፣ ሕዳር 17/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


መንፈስ ቅዱስ ሲያስመልጥ!

ጳውሎስና የሥራ ጓደኞቹ በእስያ የጌታን ቃል እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ በኩል አድርገው ሽቅብ አለፉ፡፡ ከሚስያ ድንበር ሲደርሱም በስተሰሜን በኩል አድርገው ወደ ቢታንያ ለመሄድ አስበው ነበር፡፡ የጌታ መንፈስ ግን ወደዚያ እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም(የሐዋ 16፡6-7)፡፡

መንፈሳዊ ሰው እንደማንኛውም ሌላ ሰው በእቅድ ሊመራ ይችላል፡፡ መንፈሳዊ ሰው እንደማንኛውም ሌላ ሰው የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ ሊነድፍም ይችላል፡፡ ለሥራም ሆነ ለኑሮ፣ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው አገር፣ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው ስፍራ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ፣ መንፈሳዊ ሰው እንደማንኛውም ሌላ ሰው አይደለምና ለኑሮውም ሆነ ለሥራው እንዲሁም ለማንኛውም ነገሩ በመንፈስ ቅዱስ ይመራል፡፡ መንፈስ ቅዱስን በመስማት ከድካም–ከልፋት፣ ከክስረት–ከክህደት፣ ከውርደት–ከውድቀት፣ ከአደጋና–ከሞት ያመልጣል!

ወዳጄ ሆይ፣ የተጠረገ መንገድ፣ የተመቻቸ ጉዞ ቢያጋጥም መንፈስ ቅዱስን ይስሙት! የተከፈተ በር፣ የተፈለገ መንደር፣ የተሻለ ሀገር፣ ተዘልሎ መኖር ቢያጋጥም መንፈስ ቅዱስን ስማው!  ወደ አየልዎ ቦታ፣ ወደ አዘጋጀልዎ ይዞታ፣ ወደ አሰበልዎ ከፍታ እንዲወጡ መንፈስ ቅዱስን ይስሙ!  

ወዳጄ ሆይ፣ የሚፈልጉት ነገር አገልግሎት ቢሆን ወይንም አስተምህሮት፣ መቀበል ቢሆን ወይንም መስጠት፣ ምክር ቢሆን ወይንም ምሪት መንፈስ ቅዱስን ይስሙ! የሚመኙት ነገር መጋቢነት ይሁን እረኝነት፣ ሰባኪነት ይሁን አስተማሪነት፣ ሐዋሪያነት ይሁን ነቢይነት መንፈስ ቅዱስን ይስሙ!  

ወዳጄ ሆይ፣ መንፈስ ቅዱስን መስማት ከድካም፣ ከልፋት፣ ከክስረት ያድናል! መንፈስ ቅዱስን መስማት ከውርደት፣ ከውድቀት፣ ከአደጋና ጥፋት ያስመልጣል! ከእርሱ ያልሆነ ጎዳና–መንገዱ፣ ዕድልና–በሩ፣ ምርጫውና–ምንጩ እንዲዘጋ መንፈስ ቅዱስን እንስማ!  

ከእግዚአብሔር ያልሆነ ቪዛም ሆነ ቪላው፣ አቻና ጋብቻው አደጋው ብዙ ነው! ስለሆነም መንፈስ ቅዱስን በመስማት ከድካም፣ ከልፋት እንዲሁም ከክስረት ማምለጥ ይሁንልን!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Tuesday, November 25, 2014

ድንግልና ሲያሳፍር !

ዲቮሽን ቁ.765/07     ማክሰኞ፣ ሕዳር 16/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ድንግልና ሲያሳፍር !  

ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ (1 ቆሮ 7፡36)

አንዳንድ እጮኛሞች ጋብቻ ሳይፈጽሙ ለረዥም ዓመታት አብረው ይቆያሉ፡፡ ከጋብቻ በፊት እንዲሆንላቸው አጥብቀው የሚሹት ነገሮች አሏቸው! ኢኮኖሚና ሀብት፣ መኪና እና ቤት፣ ትምህርትና ስኬት ወይንም ሌላ ምኞት አላቸው! ምኞታቸው ሳይሞላ ለዓመታት ያህል ሳይጋቡ ቢቆዩ ማፈር ይጀምራሉ!

ከጋብቻ ሀብትን፣ ከትዳር እውቀትን ለማስቀደም ስንሞክር ዓመታት ያልፋሉ፡፡ በዚህም ሒደት ውስጥ እንደ አበባ ፈክቶ የሚጠወልገው የሴት ልጆች ውበት መክሰም ይጀምራል!

ታውቃላችሁ፣ በኢኮኖሚ ምክንያት እጮኛሞች ሳይጋቡ ሲቆዩ ያሳፍራል! እንደ ፈካ አበባ የምታምረው ወጣት እጮኛ አግኝታ ሳታገባ ብትቆይ በጣም ያሳፍራል! በእጮኝነት ሰበብ፣ በኢኮኖሚ ሰበብጋብቻ ዘግይቶ፣ የቆንጂቷ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ፣ የፊቷ አበባ መጠውለግ ሲጀምር ለሴት ያሳፍራል!   

ታውቃላችሁ፣ የንቦቹ አጀብ ዙሪያው የሚከበብ ያ ውብ አበባ፣ ከቆይታ ብዛት  ፈላጊው ሲጠፋ ለሴት ያሳፍራል! ማግባት በሚገባት ዕድሜ ሴት ቶሎ ካላገባች፣ የፊቷ አበባ እስከነፈላጊው አብሮ ይጠወልጋል! ይህም ያሳፍራል!

ታውቃላችሁ፣ ሲወዱት ጠልቶ–ሲጠሉት መውደድ፣ ሲጠጉት ሸሽቶ–ሲርቁት ማባረር፣ ሲፈልጉት ተደብቆ–ሲደበቁት መገኘት ያሳፍራል!

ወገኖች ሆይ፣ ዕድሜያችን ለጋብቻ ሲደርስ፣ ሀብት ኖረም አልኖረ፣ ሰርግ ተደረገም ቀረ፣ ድግስ ተዘጋጀም ቀረ ዋናው መጋባት ነው! ጋብቻ ክቡር ነው፡፡ ጋብቻ አያሳፍርም! በጋብቻችን ቀን ድግስ ሳንደግስ፣ ጮማ ሳይቆረጥ፣ ቅልጥም ሳይገሸለጥ፣ ከበሮ ሳይደለቅ ማግባት ከፈለግን የወደድነውን እናድርግ! ኃጢአት የለብንም!

ወገኖች ሆይ፣ ማግባት ወደሚገባን ዕድሜ ደርሰን እንደሆነ በጊዜ ለማግባት በጭራሽ አንፈር!  የወደድነውን እናድርግ! ያለ አጃቢና ያለ አጨብጫቢ፣ ያለ ፈረሰኛ ያለ ጋላቢና ያለ አሸብሻቢ መጋባት ብንፈልግ የወደድነውን እናድርግ!

ወገኖች ሆይ፣ ጋብቻ በክርስቲያናዊ ሥርዓት ይፈጸም እንጂ፣ በመኖሪያ ቤትም ተከናወነ በሕዝብ አደባባይ ልዩነት የለውም! ይህንን ብናደርግ–ኃጢአት የለብንም!
ኃጢአቱ ሳይጋቡ መዳራት፣ ሳይዳሩ መዘሞት፣ የዘሞቱን መጥላት፣ የጠሉትን መፍታት ነው!
--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያደርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Monday, November 24, 2014

የምንለምነውን አናውቅም!

ዲቮሽን ቁ.75/07     ሰኞ፣ ሕዳር 15/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የምንለምነውን አናውቅም!

የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው። መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት።… ኢየሱስ ግን፦ የምትለምኑትን አታውቁም (ማር 10፡35-45)።

ብዙ ጊዜ የምንለምነውን አናውቅም፡፡ ከዚህ አላዋቂነታችን የተነሳም ለሥጋችን ጉዳት፣ ለነፍሳችን ጥፋት የሚሆኑ ነገሮች እንዲሰጡን እንለምናለን፡፡ ከሕይወት ይልቅ ሞትን፣ ከበረከት ይልቅ መርገም ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ለማግኘት እንጸልያለን፡፡ ማሩን ትተን እሬቱን፣ ዓሳ ትተን ጊንጡን እንጠይቃለን፡፡ ጉድጓዱን ረስተን ሳሩን፣ መከራውን ረስተን ዙፋኑን እንመኛለን፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት የሆኑት ያዕቆብና ዮሐንስም የሚለምኑትን አላወቁም፡፡ መለመን የሚገባቸው ብዙ መልካም ነገር ሳለ የሞት ጽዋ እንዲሰጣቸው ለመኑ፡፡ የመከራ ጥምቀት፣ የሞትን ጽዋ ስጠን በማለት ጠየቁ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ጌታ ‹‹ተዉ፣ ይቅርባችሁ›› ሲላቸው፣ ‹‹እንቢ አሻፈረን›› አሉ፡፡ ስለሆነም፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የለመኑት ልመና፣ የጠየቁትም ነገር ተሰጣቸው!

ታውቃላችሁ፣ ያዕቆብ ከጌታ ደቀመዛሙርት የመጀመሪያው ሰማዕት (የሐዋ 12፡2)፣ ዮሐንስም ከጌታ ደቀመዛሙርት የመጨረሻው ሰማዕት ሆኑ (ዮሐ 21፡20-23፤ ራዕይ 1፡9)፡፡

ታውቃላችሁ፣ ብዙ ጊዜ ጌታ ‹‹ተዉ፣ ይቅርባችሁ›› ሲለን እንሰማውም! ለሥጋችን ጉዳት፣ ለነፍሳችን ጥፋት የሚሆኑ ነገሮች እንዲሰጡን እንለምናለን፡፡ ከሕይወት ይልቅ ሞት፣ ከበረከት ይልቅ መርገም እንጠይቃለን፡፡ ማሩን ትተን ሬቱን፣ ዓሳ ትተን ጊንጡን እንለምናለን፡፡ ክብሩን ትተን ውርደት፣ ዙፋን ትተን ውድቀት እንለምናለን፡፡ የሚጎዳን ነገር ጌታ ካልሰጠንም በሐዘን በእንባ እንታጠባለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፡፡ ስለዚህ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን በሚረዳን፣ ድካማችንንም የሚያግዝ በመንፈስ ቅዱስ ልንደገፍ፣ ልንመራ ያስፈልገናል፡፡ ልብን በሚመረምረውና የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ በሚያውቀው በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንደገፍ፡፡ 
ወገኖች ሆይ፣ መንፈስ ቅዱስ ራሱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንድልጸልይ፣ በማይነገር መቃተት ስለ እኛ ይማልዳልና በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንደገፍ (ሮሜ 8፡26)፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ያልተጠመቅን ካለን በጽድቅ፣ በቅድስናና በጸሎት ጌታ እንዲሰጠን በርትተ እንጠይቅ!
--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያደርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Sunday, November 23, 2014

እግዚአብሔርን መናቅ!

ዲቮሽን ቁ.74/07     እሁድ፣ ሕዳር 14/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


እግዚአብሔርን መናቅ!


እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚያከብሩኝን አከብራለሁ፤የሚንቁኝም ፈጽሞ ይናቃሉ፡፡ (1 ሳሙ 2፡30)

አንዳንድ አገልጋዮች እግዚአብሔርን በሥራቸው ሲንቁ ይታያል! በጎደፈ ሕይወት እየተመላለሱ፣ ነውረኛ መስዋዕት እያቀረቡ፣ ያለ ፈርሃ እግዚአብሔር እያለገሉ እግዚአብሔርን ይንቃሉ! ምሕረቱን–ትዕግሥቱን፣ ችሎታ–ብቃቱን፣ ኃይልና–ሥልጣኑን ይንቃሉ! የተፈራ ስሙን፣ ጽድቁን–ቅድስናውን፣ ክብሩንና–ፍርዱን ይንቃሉ!

ወገኖች ሆይ መጋቢዎች እግዚአብሔርን ይንቃሉ! ምናምንቴ ቍርባን ፊቱ እያቀረቡ፣ በአጸያፊ ዕጣን ቤቱን እያገሙ፣ ያልተቀደሰ ነገር እየነካኩ፣ አደባባዮቹን በትዕቢት እየረገጡ፣ ጌታን ይንቃሉ!

ወገኖች ሆይ፣ መሪዎች እግዚአብሔርን ይንቃሉ! ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ እያሉ፣ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ እያደረጉ፥ ጣፋጩን መራራ መራራውን ጣፋጭ እያደረጉ ጌታን ይንቃሉ! ያልተቀደሰ ስብሰባ እየተሰባሰቡ፣ ያልተፈወሰ አጀንዳ እየተነጋገሩ፣ የዐመጻ ፊርማ–የክፋት ውሳኔ እያስተላለፉ ጌታን ይንቃሉ!

ወኖች ሆይ፣ ነቢያት እግዚአብሔርን ይንቃሉ! በዓይናቸው እያዩ–ዓይናቸውን ጨፍነው፣ በጆሮ እየሰሙ–ጆሮአቸውን ዘግተው፣ ልባቸው እያወቀ–ልብን አደንድነው እየተመላለሱ ጌታን ይንቃሉ!

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ እግዚአብሔርን ይንቃል! መስማትን እየሰማ ማስተዋል ተስኖት፣ ማየትን እያየ መመልከት አቅቶት ጌታን ይንቃል!

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔርን አንናቅ! እግዚአብሔርን መናቅ አደጋ ያመጣል! እግዚአብሔርን መናቅ ላልታሰበ ስብራት፣ ላልተጠበቀ መዓት ያጋልጣል! ወገኖች ሆይ፣ በቃልና በሥራ እግዚአብሔርን እናክብር! የሚያከብሩትን አክባሪ ነውና፣ እግዚአብሔርን እናክብር!

--------------------------------

(ከመስከረም 1/2007 ጀምሮ ዕለታዊ ዲቮሽን ፖስት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ ሁሉም ወዳጆቼ ትምህርቱ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት፣ ላይክና ሼር እንዲያደርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞቻቸውም መጠቀም እንዲችሉ እንዲያግዙ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ይህ ዲቮሽን የመማማሪያ መድረካችን እንዲሆን ፍላጎት አለኝ፡፡ ስለሆነም፣ ያልተብራራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄ፣ ወይም ማግኘት የምትፈልጉት መንፈሳዊ ምክር ካለ አቅርቡ፣ ጌታ እንደረዳኝ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Saturday, November 22, 2014

መኖርዎም መሞትዎም እንዲጠቅም!

ዲቮሽን ቁ.73/07     ቅዳሜ፣ ሕዳር 13/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


መኖርዎም መሞትዎም እንዲጠቅም!

አንዳንድ ጊዜ በሕይወት ሞኖርን እመርጣለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ እጅግ የሚመረጥ ነውና ሞቼ ከክርስቶስ ጋር አብሮ መሆንን እናፍቃለሁ፡፡ ይሁን እንጂ የማውቀው አንድ ነገር አለ፤ ይህም በሕይወት መኖሬ ለእናንተ ብዙ የሚጠቅም መሆኑን ነው (ፊል 1፡21-24)

ወገኖች ሆይ፣ በዚህች ምድር ላይ እየኖርን ያለነው በዋነኛነት ለራሳችን ጥቅም ከሆነ በሕይወት ከምንኖር ይልቅ ብንሞት የተሻለ ነው! እውነተኛ አማኞች በዚህ ዓለም የሚኖሩት ለራሳቸው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር ነው፡፡ የምንኖረው ሌሎች መልካሙን ሥራችንን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችንን እንዲያከብሩ ብርሃናችንን በሰው ፊት እንድናበራ ነው፡፡ የምንኖረው በቃልና በሥራ ስለጌታ በመመስከር፣ ለእግዚአብሔር ክብር ነው!

ታውቃላችሁ፣ ‹‹አማኞች ነን›› ባይ አንዳንድ ሰዎች ነጻነታቸውንና ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ሰው እንዲያይባቸው፣ ሰው እንዲነካባቸው አይፈልጉም! ‹‹አማኞች ነን›› ባይ ሌሎችም ‹‹ነጻነታችንን ይጋፋል›› በሚል ትዳር መያዝ አይፈልጉም፡፡ እንዲህ ከሚናገሩ ‹‹አማኞች ነን›› ባይ አንዳንዶች፣ በውስልትና ሕይወት ይመላለሳሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ‹‹አማኞች ነን›› ባይ አንዳንዶች ደግሞ ትዳር ቢመሠርቱም፣ ነገር ግን ልጅ መውለድ አይፈልጉም፡፡ ልጅ ወልዶ ማሳደግ የሚያስከፍለውን ዋጋ መሸከም አይሹም፡፡ ስለሆነም ልጅ እንዳይረገዝ ይከላከላሉ፡፡ መከላከያውን ጥሶ ጽንስ ከመጣም ውርጃ ይፈጽማሉ!

ታውቃላችሁ፣ አንዳንዶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት መሳተፍ አይፈልጉም፡፡ ዕውቀት–ችሎታቸውን፣ ክህሎት–ልምዳቸውን ማካፈል አይሹም፡፡ በልዩ ልዩ አገልግሎቶች መሳተፍ የግል ጊዜያቸውንና ነጻነታቸውን ይጋፋባቸዋል፡፡ ገንዘብ–ሀብታቸውን፣ ንብረት–ጥቅማቸውን ይነካባቸዋል!

ታውቃላችሁ፣ አንዳንዶች መኖሪያ ቤታቸውን ለመንፈሳዊ ፕሮግራም ለመፍቀድ እንኳን ይጨናነቃሉ! በሳምንት አንድ ጊዜ ለአንድና ሁለት ሰዓት ለሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መስጠት ይቸገራሉ፡፡ አለ አይደል፣ ከቤታቸው አቧራ ይራገፍባቸዋል፣ ጭቃ ይቀባባቸዋል፣ ሶፋቸው ይጎዳባቸዋል!


ወገኖች ሆይ፣ በዚህች ምድር የምንኖረው ለእግዚአብሔር ክብር ነው! ለእውነተኛ አማኝ በሕይወት መኖር ማለት ክርስቶስን ማልገል ነው! በሕይወት መኖራችን ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ነው! የእግዚአብሔር ሰው እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንዲኖር ተጠርቷል፡፡

ታውቃላችሁ፣ ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ስንጀምር ከመሞት ወይም ከመኖር መምረጥ ያስቸግራል! ይህን ሕይወት መኖር ለሌሎችም፣ ለራስም ይጠቅማል! ለእግዚአብሔር ክብር ስንኖር፣ በሕይወት መኖራችን ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ይጠቅማል!

ታውቃላችሁ፣ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር ክብር ስለማይኖሩ፣ በሕይወት መኖራቸው ሳይሆን መሞታቸው ይጠቅማል! ታውቃላችሁ፣ አንዳንዶች እንዲያውም ኖረውም ሞተውም አይጠቅሙም!

ወዳጄ ሆይ፣ በሕይወት ሲኖሩ ለሌሎች ጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ ኑሮዎትን ለእግዚአብሔር ክብር ይኑሩ! በቃልና በሥራ ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ይጀምሩ!

--------------------------------

(ከመስከረም 1/2007 ጀምሮ ዕለታዊ ዲቮሽን ፖስት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ ሁሉም ወዳጆቼ ትምህርቱ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት፣ ላይክና ሼር እንዲያደርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞቻቸውም መጠቀም እንዲችሉ እንዲያግዙ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ይህ ዲቮሽን የመማማሪያ መድረካችን እንዲሆን ፍላጎት አለኝ፡፡ ስለሆነም፣ ያልተብራራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄ፣ ወይም ማግኘት የምትፈልጉት መንፈሳዊ ምክር ካለ አቅርቡ፣ ጌታ እንደረዳኝ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

Friday, November 21, 2014

(ሴት) በመውለድ ትድናለች! (#2)

ዲቮሽን ቁ.72/07     አርብ፣ ሕዳር 12/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

(ሴት) በመውለድ ትድናለች! (#2)

ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፡፡ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።…ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች (1ጢሞ 2፡1-15)፡፡


ሴቶችና ወንዶች በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም በስብዕና እኩል ደረጃ አላቸው፡፡ በጋብቻ ውስጥ ወንድና ሴቱ ሁለቱ አንድ አካል፣ አንድ ሥጋ ይሆናሉ! በመሆኑም ለመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ‹‹የሴቶች እኩልነት›› የሚባለው ስብከት፣ ‹‹የሴቶች መብት›› የሚባለው ትምህርት አዲስ ወይም እንግዳ አይደለም፡፡

ሆኖም፣ በዚህ ‹‹የሴቶች እኩልነት›› በሚባለው ስብከት፣ ‹‹የሴቶች መብት›› የሚባለው ንፋስ የተወሰዱ ሴቶች በሚያደርጉት በ‹‹መብት›› ንቅናቄ፣ በ‹‹እኩልነት›› ትግል ትዳራቸው ሲፈርስ ቤተሰብ ሲበተን እንመለከታለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚደረግ የእኩልነት ትግል፣ የመብት ሽኩቻ ኢ–መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወንድ የሴት ራስ እንዲሆን የደነገገው ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስተምራል፡፡ ይህን ድንጋጌ ለማፍረስ መታገል ስህተት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ እስኪ የወንዶች እና የሴቶችን ሁኔታ ልብ ብላችሁ እዩ! በአብዛኛው በየግሮሰሪው ሲጠጡ የሚያመሹት፣ በየጭፈራ ቤቱ ሲልከሰከሱ የሚያድሩት እነማን ናቸው? ባለትዳር ሴቶች ወይም ልጆች ያሏቸው ሴቶች ናቸው? በጭራሽ! ጤናማ የሆኑ ባለትዳር ሴቶች፣ ልጅ ያላቸው ሴቶች ይህንን አያደርጉም! ባለትዳር ሴቶች ወይም ልጆች ያሏቸው ሴቶች በሥራ ቦታ ላይም ይሁን በፖለቲካ መድረክ፣ አሥሬ ‹‹ቤቴ፣ ቤቴ፣ ልጆቼ፣ ልጆቼ›› ሲሉ ነው የሚደመጡት፡፡

ታውቃላችሁ፣ የፈለገው ፍልስፍና ቢነገር፣ የፈለገው ፖለቲካ ቢደረደር፣ የፈለገው ሥራ ቢኖር ሴቶች እውነተኛ እርካታ የሚያገኙት በፖለቲካ መድረክ፣ ከቤት ውጭ ሳይሆን በቤታቸው ውስጥ ነው፡፡ ሴቶች የፈለጋቸውን ሥልጠና ይውሰዱ፣ በፈለጉት ሙያ ይሰማሩ፣ የፈለጉትን ገቢ ያግኙ እውነተኛ እርካታ ሊያገኙ አይችሉም! ይህ መለኮታዊ አሠራር ነው!

ታውቃላችሁ፣ የሴቶች እውተኛ እርካታ ያለው በቤት ውስጥ ነው! ሴቶች ከፈለጉት የፖለቲካ መሰላል ላይ ይውጡ፣ በፈለገው የሥልጣን እርከን ይቀመጡ፣ የፈለገው የእውቀት ማማ ላይ ይድረሱ እውተኛ እርካታ የሚያገኙት ከቤት ውስጥ ነው! ይህ መለኮታዊ አሠራር ነው!

ታውቃላችሁ፣ ያላገቡ ሴቶች የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ፣ የትዳር አጋር የማጣት ጉዳይ ሆኖ እንጂ እውነተኛ እርካታ የሚያገኙት ከቤት ውስጥ መሆኑን የሚጠቁማቸው አያስፈልጋቸውም!  

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር ሴቶችን በቤት እንዲሆኑ የሚፈልገው ያለ ምክንያት አይደለም! ሴቶች የትውልድ ፈጣሪ፣ የትውልዱ ቀራጭ፣ ትውልድ ተኪ ናቸው! የሀገር መሪዎች ተወልደው የሚያድጉት፣ የቤተክርስቲያን ሰዎች ተወልደው የሚያድጉት በቤት ውስጥ ነው! ጥሩ መሪ የሚያድገው በጥሩ እናት ነው! ስለሆነም ሴቶች ትዳር እንዲይዙ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ የወለዱትን ልጅ በሌላ ሰው ሳይሆን ራሳቸው እንዲያሳድጉ መለኮታዊ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸዋል! ይህን የቤት ሥራ ባግባቡ በመወጣት ጤናማ ትውልድ በመቅረጽ ከተጠያቂነት ሊድኑ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ በመልካም ወይም በክፉ ድርጊታቸው ዝናቸው በዓለም ገንኖ የሚታወቅ መሪዎች ከሞላ ጎደል ከእናቶቻቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ያሳያል፡፡ የሚሊዮችን ሕይወት ያጠፋውን አዶልፍ ሂትለርን አስቡ! በጨቅላ ዕድሜው ላይ የሚወድዳት እናቱን በሞት ሲነጠቅ፣ ከእናቱ ሐዘን በሕይወት ዘመኑ መጽናናት አልቻለም፡፡ የእናቱን ምትክ ፈጽሞ አላገኘም፡፡ በዚህ መልኩ ያደገው ሂትለር ምን ያህል ጨካኝ እንደሆነ አስቡ!

ወገኖች ሆይ፣ በማይታመን ፍጥነት መንግሥታትን በማንበርከክ መላውን ዓለም በግሪክን ሥልጣኔ ሥር ያደረገውን አሌክዛንደር ዘግሬትን አስቡ! በዕድሜው ወጣት ሆኖ ለዚያ ሁሉ ስኬት ለዚያ ሁሉ ድል የበቃው በእናቱ ብርታት ነው! ፈረንሳዊውን ናፖሊዮን ቦናፓርቴን አስቡ! ከምንም ተነስቶ መላውን አውሮፓ ወደ መግዛት የደረሰው በእናቱ ብርታት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የቀድሞው መሪያችን የመለስ ዜናዊን፣ የጠቅላይ ሚኒስትራችን የኃይለማርያም ደሳለኝን፣ የክቡር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖምን፣ የባራክ ኦባማን፣ የርስዎን እናት ያስቡ! ለዛሬው ማንነታችን የእናቶቻችን ድርሻ ከፍተኛ አይደለምን? የእናቶቻችን ስብዕና፣ የማንነታቸው አሻራ በአገልግሎታችን ላይ፣ በባህርያችን ላይ፣ በፖለቲካችን ላይ፣ በአመራራችን ላይ ላቅ ያለ አይደለምን?


ወገኖችን ሆይ፣ ልጆቻችን በቤታቸው ውስጥ የእናታቸውን ፍቅር እያገኙ፣ በእናታቸው ምክር እያደጉ ነውን? ሴቶች ሆይ፣ በቤታችሁ ለልጆቻችሁ በእምነትና በፍቅር በቅድስናና ራስን የመግዛት እየሆናችሁ ትውልድ እንድታሳድጉ ጌታ የሰጣችሁን ኃላፊነት እየተወጣችሁ ነውን? ይህ ከሆነ፣ ከተጠያቂነት ትድናላችሁ! (ተፈጸመ)

Thursday, November 20, 2014

(ሴት) በመውለድ ትድናለች! (#1)

ዲቮሽን ቁ.71/07     ሐሙስ፣ ሕዳር 11/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


(ሴት) በመውለድ ትድናለች!(#1)


ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፡፡ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።…ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች (1ጢሞ 2፡1-15)፡፡

ይህን ክፍል ያለማስተዋል ከተረዳነው ከብዙ ሔዋኖች ጋር ሊያጣላ ይችላል! ከሴቶች መብት ተሟጋቾች ጋርም ሊያጋጭ ይችላል! ድኅነትይ ከመውለድ ጋር የምናያይዝ ከሆነም የወለዱ ሴቶች የዳኑ፣ ያልወለዱ ሴቶች ደግሞ ያልዳኑ ናቸው ወደሚል የተሳሳተ አቅጣጫ ሊወስደን ይችላል፡፡

በአዲስ ኪዳን የድኅነት መንገድ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ ተቀምጧል– በኢየሱስ ክርስቶስን የሚያምን የዘላለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም (ዮሐ 3፡16)! መዳን በሌላ በማንም የለም (የሐዋ 4፡12)! ስለሆነም ክፍሉ በቀጥታ የሚናገረው ስለ ‹‹ድኅነት›› ሳይሆን ስለ‹‹መዳን›› ነው–ከጨዋ ሕይወት ጉድለት ምክንያት ከሚመጣ አደጋ ስለመዳን ነው! ትዳር በመያዝ፣ ልጅ በመውለድ፣ ተገቢ ልብስ በመልበስ ስለሚድኑት መዳን ነው!

ወገኖች ሆይ፣ በአብዛኛው የምናገኛቸውን ያላገቡ ሴቶችን የጸጉር ስታይሎችና የልብስ ፋሽኖች እስኪ ተመልከቱ! የወጣት ሴቶቻችን እርቃነ ልብሶች ፍትወት ቀስቃሽ ናቸው! በዘመናዊነት ስም ነውራቸውን ገላልጠው የሚሄዱት በአብዛኛው ያላገቡ ሴቶች ናቸው! አንዳንዶቹ ጭራሽ ክፍት በራቸውን፣ ስንጥቅ ኋላቸውን፣ ሁለት ጉልቻቸውን ያለምንም ሐፍረት ገልጠው ይሄዳሉ!

ወገኖች ሆይ፣ የጢሞቴዎስ ጸሐፊ በልብስ ላይ ጠንካራ ትምህርት እየሰጠ ነው! እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሴቶች ይህን ከመሰለ ውርደት እንዲወጡ፣ እርቃን ለብሶ መሄድ ከሚያመጣው ውድቀት እንዲያመልጡ፣ ትዳር እንዲይዙ፣ አደብ እንዲገዙ፣ ጨዋ ልብስ በመልበስ ለሌሎች ማሰናከያ ከመሆን እንዲድኑ ይመክራቸዋል!

ወገኖች ሆይ፣ ትዳር የያዙ ሴቶች እርቃነ ሥጋቸውን አጋልጠው አይሄዱም! የወለዱ ሴቶች  እርቃነ ገላቸውን ለሰው እግዚቢሽን ፈጽሞ አያቀርቡም! ትዳር የያዙ ሴቶች፣ ብሎም የወለዱ ጨዋ ይሆናሉ! ያገቡ የወለዱ ከእዩኝ እዩኝ፣ ውደዱኝ ውደዱኝ አደጋ ይድናሉ! አርፈው፣ ጸጥና ዝግ ብለው የተረጋጋ ሕይወት መኖር ይፈልጋሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ባለትዳር ሴቶች ብሎም የወለዱ የወጣትነትን እብደት ሒሳብ ይዘጋሉ! ሌሎችን ከመጣል በሌሎችም ከመጣል አደጋ ይድናሉ! ወገኖች ሆይ፣ ያገቡ ሴቶች ብሎም የወለዱ ወዴት ሄድሽ? የት ነበርሽ? የሚል ሰው አላቸው! በሽንገላ ፍቅር በሚያታልል ምላስ ስተው እንዳይወድቁ የሚከለክላቸው ባለቤት አላቸው! ራቁት መሄድ ሳይኖር፣ እዩኝ እዩኝ ሳይኖር፣ በቅዱስ ጋብቻ፣ በቅዱስ መኝታ፣  የጾታን ጥያቄ በፈለጉት ጊዜ የሚመልስላቸው፣ ከጣራቸው በታች ከእጃቸው አላቸው!


ወገኖች ሆይ፣ የሴት ልጅ ትልቅ ኃላፊነት ያለው በቤቷ ውስጥ ነው! የሚያምኑ ልጆችን ወልዶ ለማሳደግ፣ ለወለዱት ልጆች በፍቅር በቅድስና ምሳሌ በመሆን ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነት ያለው በቤት ውስጥ ነው! 

ቅድስት ማርያም በወለደችው ልጅ ምክንያት ለዓለም ሁሉ መዳን ምክንያት ሆናለች! ሴቶቻችን ትውልድ እንዲተኩ፣ ትውልድ እንዲቀርጹ ይፈለጋሉ! በመሆኑም፣ ሴቶቻችን ከቅድስት ማርያም በመማር የትውልድ ተኪነት ሚናን ተግተው ቢጫወቱ፣ የቤት ኃላፊነታቸውን በትጋት ቢወጡ ከተጠያቂነት ይድናሉ!

Wednesday, November 19, 2014

ሁሉን በሚችል– አምናለሁ !

ዲቮሽን ቁ.70/07     ረቡዕ፣ ሕዳር 10/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሁሉን በሚችል– አምናለሁ !

እኔ ሁሉን በሚችል – ምድረበዳን ወደገነት በሚቀይር፣ ከባዶ ነገር(ባራ) ሕይወት በሚፈጥር፣ ድቅድቅ ጨለማ ላይ ብርሃን ይሁን በሚል፣ ምንም በማይሳነው በኤልሻዳይ ጌታ በእግዚአብሔር አምናለሁ፡፡

ደግሞም ከእርሱ ዓይኖች ፊት የሚሰወር ነገር፣ ገበናና ሚስጥር፣ ጨለማና ግርዶሽ ችግር እንቆቅልሽ እንደሌለ አምናለሁ፡፡  

ደግሞም ሁሉን ቻዩ ጌታ አንድን ቤተሰብ ከአንድ ግለሰብ፣ ትልቁን ጉባኤ ከትንሹ አጥቢያ፣ ወንዱን ከሴቱ፣ ወጣቱን ከአዛውንቱ፣ ደካማን ከብርቱ እንደማያበላልጥ፣ እንደማይመርጥ፣ እንደማያዳላና እንደማይጠላ አምናለሁ፡፡

ደግሞም፣ ከባሕል ከደንባችን ውጭ፣ ከወግ ከልማዳችን ውጭ፣ ከእውቀት ከግንዛቤያችን ውጭ፣ ከፍልስፍና ከመላምታችን ውጭ፣ ከበጀት ከፎርሙላችን ውጭ መሥራት እንደሚችል አምናለሁ፡፡

ደግሞም፣ ሐዋርያት ሊያስነሳ፣ ነቢያት ሊቀባ፣ ፈውስና ተአምራት፣ ድንቅና ምልክት፣ ያልተለመደና አነጋጋሪ ነገር ሊያደርግ እንደሚችል

ደግሞም፣ እርሱ እንደወደደ በዘይትና ቅባት፣ በጨርቅና ውሃ አልፎ እንደሚሠራ አምናለሁ፡፡

ደግሞም እርሱ እንደፈቀደ በምሁር በማይም፣ በድንጋይ በአህያ መጠቀም እንደሚችል አምናለሁ፡፡

ደግሞም፣ ከሰማያት መናን፣ ከመካኒቱ ልጅን ከድሃው ብልጥግናን በረከትና ሀብትን ማዝነብ እንደሚችል አምናለሁ፡፡


ደግሞም፣ ሊገድል–ሊያድን፣ ሊያወጣ–ሊያወርድ፣ ሊጥል–ሊያነሳ፣ ሊሰጥ–ሊነሳ፣ ሊያጎድል–ሊያበዛ፣ ሊያሳዝን–ሊያጽናና፣ ሊያከብር–ሊያዋርድ፣ ሊፈውስ–ላይፈውስ፣ ሊያበለጽግ–ሊያደኸይ በሚችል በሁሉን ቻይ አምላክ በእግዚአብሔር አምናለሁ፡፡

Tuesday, November 18, 2014

የእምነቴ መግለጫ

ዲቮሽን ቁ.69/07     ማክሰኞ፣ ሕዳር 9/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የእምነቴ መግለጫ

እኔ፣ ሁሉን በሚችል፣ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ፡፡

ደግምም በአንድ ልጁ፣ በመንፈስ ቅዱስ በተጸነሰ፣ በጴንጠናዊው በጲላጦስ ዘመን መከራን በተቀበለ፣ በተሰቀለ፣ በሞተ፣ በሶስተኛው ቀን ከሙታን በተነሳ፣ ወደ ሰማይ በወጣ፣ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ በተቀመጠ፣ በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ከዚያም በሚመለስ፣ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ፡፡

ደግሞም፣ በአንዲት ቅድስት በሐዋርያት ተክርስቲያን፣ በቅዱሳን አንድነት፣ በሥጋ ትንሳኤ፣ በዘላለም ሕይወት አምናለሁ፡፡

ደግሞም ከድኅነት በኋላ በሚሆን በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት፣ በልሳን መናገር፣ ዛሬም በሚሠራ በጸጋ ስጦታ፣ በሐዋርያት፣ በነቢያት፣ በድንቅና ተአምራት፣ በአጋንንት ማውጣት አምናለሁ፡፡


ደግሞም፣ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በቃሉ መገለጥ፣ በወቅታዊ ምሪት፣ በተቀባ ስብከት፣ በጸሎት፣ በመንፈስ መሞላት፣ አምናለሁ፡፡ አሜን፡፡