Thursday, November 20, 2014

(ሴት) በመውለድ ትድናለች! (#1)

ዲቮሽን ቁ.71/07     ሐሙስ፣ ሕዳር 11/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


(ሴት) በመውለድ ትድናለች!(#1)


ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፡፡ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።…ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች (1ጢሞ 2፡1-15)፡፡

ይህን ክፍል ያለማስተዋል ከተረዳነው ከብዙ ሔዋኖች ጋር ሊያጣላ ይችላል! ከሴቶች መብት ተሟጋቾች ጋርም ሊያጋጭ ይችላል! ድኅነትይ ከመውለድ ጋር የምናያይዝ ከሆነም የወለዱ ሴቶች የዳኑ፣ ያልወለዱ ሴቶች ደግሞ ያልዳኑ ናቸው ወደሚል የተሳሳተ አቅጣጫ ሊወስደን ይችላል፡፡

በአዲስ ኪዳን የድኅነት መንገድ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ ተቀምጧል– በኢየሱስ ክርስቶስን የሚያምን የዘላለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም (ዮሐ 3፡16)! መዳን በሌላ በማንም የለም (የሐዋ 4፡12)! ስለሆነም ክፍሉ በቀጥታ የሚናገረው ስለ ‹‹ድኅነት›› ሳይሆን ስለ‹‹መዳን›› ነው–ከጨዋ ሕይወት ጉድለት ምክንያት ከሚመጣ አደጋ ስለመዳን ነው! ትዳር በመያዝ፣ ልጅ በመውለድ፣ ተገቢ ልብስ በመልበስ ስለሚድኑት መዳን ነው!

ወገኖች ሆይ፣ በአብዛኛው የምናገኛቸውን ያላገቡ ሴቶችን የጸጉር ስታይሎችና የልብስ ፋሽኖች እስኪ ተመልከቱ! የወጣት ሴቶቻችን እርቃነ ልብሶች ፍትወት ቀስቃሽ ናቸው! በዘመናዊነት ስም ነውራቸውን ገላልጠው የሚሄዱት በአብዛኛው ያላገቡ ሴቶች ናቸው! አንዳንዶቹ ጭራሽ ክፍት በራቸውን፣ ስንጥቅ ኋላቸውን፣ ሁለት ጉልቻቸውን ያለምንም ሐፍረት ገልጠው ይሄዳሉ!

ወገኖች ሆይ፣ የጢሞቴዎስ ጸሐፊ በልብስ ላይ ጠንካራ ትምህርት እየሰጠ ነው! እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሴቶች ይህን ከመሰለ ውርደት እንዲወጡ፣ እርቃን ለብሶ መሄድ ከሚያመጣው ውድቀት እንዲያመልጡ፣ ትዳር እንዲይዙ፣ አደብ እንዲገዙ፣ ጨዋ ልብስ በመልበስ ለሌሎች ማሰናከያ ከመሆን እንዲድኑ ይመክራቸዋል!

ወገኖች ሆይ፣ ትዳር የያዙ ሴቶች እርቃነ ሥጋቸውን አጋልጠው አይሄዱም! የወለዱ ሴቶች  እርቃነ ገላቸውን ለሰው እግዚቢሽን ፈጽሞ አያቀርቡም! ትዳር የያዙ ሴቶች፣ ብሎም የወለዱ ጨዋ ይሆናሉ! ያገቡ የወለዱ ከእዩኝ እዩኝ፣ ውደዱኝ ውደዱኝ አደጋ ይድናሉ! አርፈው፣ ጸጥና ዝግ ብለው የተረጋጋ ሕይወት መኖር ይፈልጋሉ!

ወገኖች ሆይ፣ ባለትዳር ሴቶች ብሎም የወለዱ የወጣትነትን እብደት ሒሳብ ይዘጋሉ! ሌሎችን ከመጣል በሌሎችም ከመጣል አደጋ ይድናሉ! ወገኖች ሆይ፣ ያገቡ ሴቶች ብሎም የወለዱ ወዴት ሄድሽ? የት ነበርሽ? የሚል ሰው አላቸው! በሽንገላ ፍቅር በሚያታልል ምላስ ስተው እንዳይወድቁ የሚከለክላቸው ባለቤት አላቸው! ራቁት መሄድ ሳይኖር፣ እዩኝ እዩኝ ሳይኖር፣ በቅዱስ ጋብቻ፣ በቅዱስ መኝታ፣  የጾታን ጥያቄ በፈለጉት ጊዜ የሚመልስላቸው፣ ከጣራቸው በታች ከእጃቸው አላቸው!


ወገኖች ሆይ፣ የሴት ልጅ ትልቅ ኃላፊነት ያለው በቤቷ ውስጥ ነው! የሚያምኑ ልጆችን ወልዶ ለማሳደግ፣ ለወለዱት ልጆች በፍቅር በቅድስና ምሳሌ በመሆን ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነት ያለው በቤት ውስጥ ነው! 

ቅድስት ማርያም በወለደችው ልጅ ምክንያት ለዓለም ሁሉ መዳን ምክንያት ሆናለች! ሴቶቻችን ትውልድ እንዲተኩ፣ ትውልድ እንዲቀርጹ ይፈለጋሉ! በመሆኑም፣ ሴቶቻችን ከቅድስት ማርያም በመማር የትውልድ ተኪነት ሚናን ተግተው ቢጫወቱ፣ የቤት ኃላፊነታቸውን በትጋት ቢወጡ ከተጠያቂነት ይድናሉ!

No comments:

Post a Comment