ዲቮሽን ቁ.75/07 ሰኞ፣ ሕዳር
15/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የምንለምነውን
አናውቅም!
የዘብዴዎስ
ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው። መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት።… ኢየሱስ
ግን፦ የምትለምኑትን አታውቁም (ማር 10፡35-45)።
ብዙ
ጊዜ የምንለምነውን አናውቅም፡፡ ከዚህ አላዋቂነታችን የተነሳም ለሥጋችን ጉዳት፣ ለነፍሳችን ጥፋት የሚሆኑ ነገሮች እንዲሰጡን እንለምናለን፡፡
ከሕይወት ይልቅ ሞትን፣ ከበረከት ይልቅ መርገም ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ለማግኘት እንጸልያለን፡፡ ማሩን ትተን እሬቱን፣ ዓሳ
ትተን ጊንጡን እንጠይቃለን፡፡ ጉድጓዱን ረስተን ሳሩን፣ መከራውን ረስተን ዙፋኑን እንመኛለን፡፡
የኢየሱስ
ክርስቶስ ደቀመዛሙርት የሆኑት ያዕቆብና ዮሐንስም የሚለምኑትን አላወቁም፡፡ መለመን የሚገባቸው ብዙ መልካም ነገር ሳለ የሞት
ጽዋ እንዲሰጣቸው ለመኑ፡፡ የመከራ ጥምቀት፣ የሞትን ጽዋ ስጠን በማለት ጠየቁ፡፡
ታውቃላችሁ፣
ጌታ ‹‹ተዉ፣ ይቅርባችሁ›› ሲላቸው፣ ‹‹እንቢ አሻፈረን›› አሉ፡፡ ስለሆነም፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የለመኑት ልመና፣ የጠየቁትም
ነገር ተሰጣቸው!
ታውቃላችሁ፣
ያዕቆብ ከጌታ ደቀመዛሙርት የመጀመሪያው ሰማዕት (የሐዋ 12፡2)፣ ዮሐንስም ከጌታ ደቀመዛሙርት የመጨረሻው ሰማዕት ሆኑ (ዮሐ 21፡20-23፤
ራዕይ 1፡9)፡፡
ታውቃላችሁ፣
ብዙ ጊዜ ጌታ ‹‹ተዉ፣ ይቅርባችሁ›› ሲለን እንሰማውም! ለሥጋችን ጉዳት፣ ለነፍሳችን ጥፋት የሚሆኑ ነገሮች እንዲሰጡን እንለምናለን፡፡
ከሕይወት ይልቅ ሞት፣ ከበረከት ይልቅ መርገም እንጠይቃለን፡፡ ማሩን ትተን ሬቱን፣ ዓሳ ትተን ጊንጡን እንለምናለን፡፡ ክብሩን
ትተን ውርደት፣ ዙፋን ትተን ውድቀት እንለምናለን፡፡ የሚጎዳን ነገር ጌታ ካልሰጠንም በሐዘን በእንባ እንታጠባለን፡፡
ወገኖች
ሆይ፣ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፡፡ ስለዚህ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን በሚረዳን፣ ድካማችንንም የሚያግዝ በመንፈስ
ቅዱስ ልንደገፍ፣ ልንመራ ያስፈልገናል፡፡ ልብን በሚመረምረውና የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ በሚያውቀው በመንፈስ ቅዱስ ላይ
እንደገፍ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ መንፈስ ቅዱስ ራሱ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንድልጸልይ፣ በማይነገር መቃተት ስለ እኛ ይማልዳልና በመንፈስ ቅዱስ
ላይ እንደገፍ (ሮሜ 8፡26)፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ያልተጠመቅን ካለን በጽድቅ፣ በቅድስናና በጸሎት ጌታ እንዲሰጠን በርትተ እንጠይቅ!
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያደርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment