Saturday, November 29, 2014

ክብር ከሕዝቡ ሲለቅቅ!

ዲቮሽን ቁ.80/07     ቅዳሜ፣ ሕዳር 20/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ክብር ከሕዝቡ ሲለቅቅ!


የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበር የእግዚአብሔርም ታቦት እንደ ተማረከች፥ አማትዋና ባልዋም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች። ወደሞትም በቀረበች ጊዜ በዙሪያዋ ያሉት ሴቶች። ወንድ ልጅ ወልደሻልና አትፍሪ አሉአት። እርስዋ ግን አልመለሰችላቸውም፥ በልብዋም አላኖረችውም። እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ስለ ተማረከች ስለአማትዋና ስለ ባልዋም። ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕፃኑን ስም። ኢካቦድ ብላ ጠራችው።(1ሳሙ 4፡19-21)፡፡

እህል ውሃቸው ካልጎደለ፣ እንቅልፍ መኝታቸው ከተደላደለ ለሌላው ነገር የማይጨነቁ ብዙሰዎች አሉ፡፡ ከምግብ ያለፈ ራዕይ፣ ከትዳር ያለፈ ጉዳይ፣ ከምድር ያለፈ ሰማይ የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የሕይወት ዓላማቸው፣ የመኖር ሕልማቸው በምድራዊ ነገር ላይ የተንጠላጠለ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡

በቤተክርስቲያን ውስጥም ብዙዎቹ ለአባልነቱ እንጂ፣ ለአስራት መባቸው እንጂ፣ እሁዱን ጠብቀው ለመመላለሳቸው እንጂ ለሌላው ነገር ደንታ የሌላቸው ሰዎች አሉ፡፡ እንደ አሕዛብ ሁሉ ምኞታቸው መማር ሥራ መያዝ፣ ማግባትና መውለድ፣ መክበድና መክበር የሆነ ብዙ የቤተክርስቲያን ሰዎች አሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተመቸው አልተመቸው፣ ደላው አልደላው፣ አሸነፈም ተሸነፈ፣ ከሰረም አተረፈ ደንታ የማይሰጣቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ አደገም አላደገ፣ ተነሳም ወደቀ፣ ግድ የማይላቸው አሉ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የፊንሐስን ሚስት እናስብ! ዙሪያዋን የሞሉ አጽናኞች ቢኖሩም፣ ወንድ ልጅ ብትወልድም፣ ታቦት ተማርኳልና፣ የእግዚአብሔር ክብር ከሕዝቡ ለቅቋልና መጽናናት አልቻለችም፡፡ ከወሊድ የምጥ ስቃይ፣ ከባሏ ሞት በላይ፣ ከአማቷም ሞት በላይ ነፍሷን ያስጨነቀው የእግዚአብሔር ክብር ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ክብሩ ከለቀቀ መጽናናት አይኖርም፡፡ ክብሩ የሌለበት ልጆች ቢወለዱም፣ አጃቢዎች ቢኖሩም፣ አባላት ቢበዙም መጽናናት ግን የለም፡፡ ክብሩ የሌለበት ፕሮግራም ቢበዛ፣ አምልኮ ቢንዛዛ መጽናናት አይመጣም፡፡ ክብሩ የሌለበት ሰባኪ–ዘማሪ፣ ወንጌል–አስተማሪ፣ እረኛ–መጋቢ፣ ወይንም ማናቸውም አገልጋይ ቢበዛ፣ ጎመን ቢጠነዛ እንጂ መጽናናት አይመጣም!  

ታውቃላችሁ፣ ክብሩ ሌለበት የሚቀርብ እልልታ፣ የጨረባ ሰርግ፣ የጨረባ ተስካር ነው! ክብሩ ሌለበት የሚደረግ ሽብሸባ ባዶ ዝማሜና ማዶና ማዶ ነው!  የእግዚአብሔር ክብር ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሲለቅ ዝማሬ እሮሮ፣ እልልታ መርዶ ነው!

--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment