ዲቮሽን ቁ.79/07
አርብ፣ ሕዳር 19/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን
ሐጢያ)
አማካሪ ሰይጣን!
ጴጥሮስ
ኢየሱስን ወደ ጎን ሳብ አድርጎ፣ ‹‹ጌታ ሆይ፣ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ›› እያለ ይገስጸው ጀመር፡፡ ኢየሱስም
ወደ ጴጥሮስ ዘወር ብሎ፣ ‹‹አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለሌለ መሰናክል ሆነህብኛል››
አለው (ማቴ 16፡22-23)፡፡
ጴጥሮስ
ለኢየሱስ እየሰጠ ያለው ምክር ምርጥ ምክር ነው! ከደቀመዛሙርቱ ነጥሎ አውጥቶ፣ መከራ እንዳያይ፣ መስቀል እንዳይሸከም፣ ተሰቅሎ እንዳይሞት፣ ሞቶ
እንዳይቀበር ልባዊ ምክሩን፣ ከምክርም ያለፈ ተግሳጹን እየሰጠ ነው! ይህ የወዳጅ ምክር፣ የወዳጅ ተግሳጽ ነውና ምርጥ ምክር፣
ምርጥ ተግሳጽ ነው!
ታውቃላችሁ፣
ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው! ይኼ ምርጥ ምክር፣ ይኼ ምርጥ ተግሳጽ ከወዳጅ ወይም ከሰማይ ሳይሆን ከወደቀ መልዐክ ከአናካዩ ሰይጣን
ነው!
ታውቃላችሁ፣
በወዳጅ–ጓደኛ ተተግኖ፣ በደቀመዝሙር–ዘማሪ ተሸፍኖ፣ በተማሪ–አስተማሪ ተከልሎ፣ በአገልጋይ–በመሪ ተሰውሮ ሰይጣን ከመስመር
ሊያወጣን ይችላል!
ታውቃላችሁ፣
በመንፈሳዊ ትምህርት፣ በስነ ፍልስፍና፣ በስነ አፈታት፣ በስነ ስብከት፣ በስነ አስተምህሮ፣ በስነቃላት ቁፋሮ፣ ሰይጣን ከመስመር
ሊያወጣን ይችላል!
ወዳጄ
ሆይ፣ ‹‹ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል፤ መካሮች በበዙበት ዘንድ ግን ይጸናል (ምሳ 15፡21)። በምክር መጓደል
እቅድ እንዳይፋለስ መማከር ይገባል፡፡ ነገር ግን በስ ምክክራችን፣ በስነ ስብሰባችን፣ በስነ ውሳኔያች፣ በስነዲፕሎማሲያችን፣ በስነ
ዴሞክራሲያችን፣ በስነ እቅዳችን፣ በስነ ስትራቴጂያችን፣ በስነ ቴኦሎጂያችን፣ በስነ ‹‹ዶክትሪን››አችን፣ በስነ መተዳደሪያ
ደንባችን ሰይጣን ሊጠቀም ይችላልና መጠንቀቅ ያሻል!
ወገኖች
ሆይ፣ በየጊዜው ብዙ ስብሰባዎች፣ ብዙ ሥልጠናዎች፣ ብዙ ምክክሮች፣ ብዙ ውሳኔዎች ይደረጋሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ስንቶቹ የሰይጣን
መጠቀሚያ ሆነው አልፈው ይሆን! ከእነዚህ መካከል ስንቶቹ የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ሐሳብ ስለሌለባቸው ይሆኑ? ከእነዚህ
መካከል ስንቶቹ ፍልስፍና ብቻ፣ የሰው ሐሳብ ብቻ፣ የአእምሮ ነገር ብቻ፣ የቃላት ነገር ብቻ…ይሆኑ?
ወገኖች
ሆይ፣ ከሥልጠናዎቻችንና ከምክክሮቻችን ስንቶቹ አሰናክለውንና አደናቅፈውን ይሆን? ከሥልጠናዎቻችንና ከምክክሮቻችን ስንቶቹ ከመስመር
አውጥተውን፣ ከእውነት አስተውን፣ ከእምነት አስጥለውን ይሆን?
ወገኖች
ሆይ፣ የወዳጅን ካባ ለብሶ፣ የወዳጅ ቋንቋ ተውሶ፣ በሚጣፍጥ ምላስ ተቅለስልሶ ነድፎ ከሚገድል አማካሪ ሰይጣን ጌታ ይሰውረን!
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment