Friday, November 21, 2014

(ሴት) በመውለድ ትድናለች! (#2)

ዲቮሽን ቁ.72/07     አርብ፣ ሕዳር 12/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

(ሴት) በመውለድ ትድናለች! (#2)

ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፡፡ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥ መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።…ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች (1ጢሞ 2፡1-15)፡፡


ሴቶችና ወንዶች በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም በስብዕና እኩል ደረጃ አላቸው፡፡ በጋብቻ ውስጥ ወንድና ሴቱ ሁለቱ አንድ አካል፣ አንድ ሥጋ ይሆናሉ! በመሆኑም ለመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ‹‹የሴቶች እኩልነት›› የሚባለው ስብከት፣ ‹‹የሴቶች መብት›› የሚባለው ትምህርት አዲስ ወይም እንግዳ አይደለም፡፡

ሆኖም፣ በዚህ ‹‹የሴቶች እኩልነት›› በሚባለው ስብከት፣ ‹‹የሴቶች መብት›› የሚባለው ንፋስ የተወሰዱ ሴቶች በሚያደርጉት በ‹‹መብት›› ንቅናቄ፣ በ‹‹እኩልነት›› ትግል ትዳራቸው ሲፈርስ ቤተሰብ ሲበተን እንመለከታለን፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚደረግ የእኩልነት ትግል፣ የመብት ሽኩቻ ኢ–መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወንድ የሴት ራስ እንዲሆን የደነገገው ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር መሆኑን በግልጽ ያስተምራል፡፡ ይህን ድንጋጌ ለማፍረስ መታገል ስህተት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ እስኪ የወንዶች እና የሴቶችን ሁኔታ ልብ ብላችሁ እዩ! በአብዛኛው በየግሮሰሪው ሲጠጡ የሚያመሹት፣ በየጭፈራ ቤቱ ሲልከሰከሱ የሚያድሩት እነማን ናቸው? ባለትዳር ሴቶች ወይም ልጆች ያሏቸው ሴቶች ናቸው? በጭራሽ! ጤናማ የሆኑ ባለትዳር ሴቶች፣ ልጅ ያላቸው ሴቶች ይህንን አያደርጉም! ባለትዳር ሴቶች ወይም ልጆች ያሏቸው ሴቶች በሥራ ቦታ ላይም ይሁን በፖለቲካ መድረክ፣ አሥሬ ‹‹ቤቴ፣ ቤቴ፣ ልጆቼ፣ ልጆቼ›› ሲሉ ነው የሚደመጡት፡፡

ታውቃላችሁ፣ የፈለገው ፍልስፍና ቢነገር፣ የፈለገው ፖለቲካ ቢደረደር፣ የፈለገው ሥራ ቢኖር ሴቶች እውነተኛ እርካታ የሚያገኙት በፖለቲካ መድረክ፣ ከቤት ውጭ ሳይሆን በቤታቸው ውስጥ ነው፡፡ ሴቶች የፈለጋቸውን ሥልጠና ይውሰዱ፣ በፈለጉት ሙያ ይሰማሩ፣ የፈለጉትን ገቢ ያግኙ እውነተኛ እርካታ ሊያገኙ አይችሉም! ይህ መለኮታዊ አሠራር ነው!

ታውቃላችሁ፣ የሴቶች እውተኛ እርካታ ያለው በቤት ውስጥ ነው! ሴቶች ከፈለጉት የፖለቲካ መሰላል ላይ ይውጡ፣ በፈለገው የሥልጣን እርከን ይቀመጡ፣ የፈለገው የእውቀት ማማ ላይ ይድረሱ እውተኛ እርካታ የሚያገኙት ከቤት ውስጥ ነው! ይህ መለኮታዊ አሠራር ነው!

ታውቃላችሁ፣ ያላገቡ ሴቶች የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ፣ የትዳር አጋር የማጣት ጉዳይ ሆኖ እንጂ እውነተኛ እርካታ የሚያገኙት ከቤት ውስጥ መሆኑን የሚጠቁማቸው አያስፈልጋቸውም!  

ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔር ሴቶችን በቤት እንዲሆኑ የሚፈልገው ያለ ምክንያት አይደለም! ሴቶች የትውልድ ፈጣሪ፣ የትውልዱ ቀራጭ፣ ትውልድ ተኪ ናቸው! የሀገር መሪዎች ተወልደው የሚያድጉት፣ የቤተክርስቲያን ሰዎች ተወልደው የሚያድጉት በቤት ውስጥ ነው! ጥሩ መሪ የሚያድገው በጥሩ እናት ነው! ስለሆነም ሴቶች ትዳር እንዲይዙ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ የወለዱትን ልጅ በሌላ ሰው ሳይሆን ራሳቸው እንዲያሳድጉ መለኮታዊ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸዋል! ይህን የቤት ሥራ ባግባቡ በመወጣት ጤናማ ትውልድ በመቅረጽ ከተጠያቂነት ሊድኑ ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ በመልካም ወይም በክፉ ድርጊታቸው ዝናቸው በዓለም ገንኖ የሚታወቅ መሪዎች ከሞላ ጎደል ከእናቶቻቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ያሳያል፡፡ የሚሊዮችን ሕይወት ያጠፋውን አዶልፍ ሂትለርን አስቡ! በጨቅላ ዕድሜው ላይ የሚወድዳት እናቱን በሞት ሲነጠቅ፣ ከእናቱ ሐዘን በሕይወት ዘመኑ መጽናናት አልቻለም፡፡ የእናቱን ምትክ ፈጽሞ አላገኘም፡፡ በዚህ መልኩ ያደገው ሂትለር ምን ያህል ጨካኝ እንደሆነ አስቡ!

ወገኖች ሆይ፣ በማይታመን ፍጥነት መንግሥታትን በማንበርከክ መላውን ዓለም በግሪክን ሥልጣኔ ሥር ያደረገውን አሌክዛንደር ዘግሬትን አስቡ! በዕድሜው ወጣት ሆኖ ለዚያ ሁሉ ስኬት ለዚያ ሁሉ ድል የበቃው በእናቱ ብርታት ነው! ፈረንሳዊውን ናፖሊዮን ቦናፓርቴን አስቡ! ከምንም ተነስቶ መላውን አውሮፓ ወደ መግዛት የደረሰው በእናቱ ብርታት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የቀድሞው መሪያችን የመለስ ዜናዊን፣ የጠቅላይ ሚኒስትራችን የኃይለማርያም ደሳለኝን፣ የክቡር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖምን፣ የባራክ ኦባማን፣ የርስዎን እናት ያስቡ! ለዛሬው ማንነታችን የእናቶቻችን ድርሻ ከፍተኛ አይደለምን? የእናቶቻችን ስብዕና፣ የማንነታቸው አሻራ በአገልግሎታችን ላይ፣ በባህርያችን ላይ፣ በፖለቲካችን ላይ፣ በአመራራችን ላይ ላቅ ያለ አይደለምን?


ወገኖችን ሆይ፣ ልጆቻችን በቤታቸው ውስጥ የእናታቸውን ፍቅር እያገኙ፣ በእናታቸው ምክር እያደጉ ነውን? ሴቶች ሆይ፣ በቤታችሁ ለልጆቻችሁ በእምነትና በፍቅር በቅድስናና ራስን የመግዛት እየሆናችሁ ትውልድ እንድታሳድጉ ጌታ የሰጣችሁን ኃላፊነት እየተወጣችሁ ነውን? ይህ ከሆነ፣ ከተጠያቂነት ትድናላችሁ! (ተፈጸመ)

No comments:

Post a Comment