ዲቮሽን ቁ.77/07
ረቡዕ፣ ሕዳር 17/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን
ሐጢያ)
መንፈስ ቅዱስ ሲያስመልጥ!
ጳውሎስና
የሥራ ጓደኞቹ በእስያ የጌታን ቃል እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው፣ በፍርግያና በገላትያ በኩል አድርገው ሽቅብ
አለፉ፡፡ ከሚስያ ድንበር ሲደርሱም በስተሰሜን በኩል አድርገው ወደ ቢታንያ ለመሄድ አስበው ነበር፡፡ የጌታ መንፈስ ግን ወደዚያ
እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም(የሐዋ 16፡6-7)፡፡
መንፈሳዊ ሰው እንደማንኛውም ሌላ ሰው በእቅድ ሊመራ ይችላል፡፡ መንፈሳዊ ሰው
እንደማንኛውም ሌላ ሰው የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ ሊነድፍም ይችላል፡፡ ለሥራም ሆነ ለኑሮ፣ ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው
አገር፣ ከአንዱ ሥፍራ ወደ ሌላው ስፍራ ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ፣ መንፈሳዊ ሰው እንደማንኛውም ሌላ ሰው አይደለምና ለኑሮውም ሆነ
ለሥራው እንዲሁም ለማንኛውም ነገሩ በመንፈስ ቅዱስ ይመራል፡፡ መንፈስ ቅዱስን በመስማት ከድካም–ከልፋት፣ ከክስረት–ከክህደት፣ ከውርደት–ከውድቀት፣
ከአደጋና–ከሞት ያመልጣል!
ወዳጄ ሆይ፣ የተጠረገ መንገድ፣ የተመቻቸ ጉዞ ቢያጋጥም መንፈስ ቅዱስን ይስሙት! የተከፈተ
በር፣ የተፈለገ መንደር፣ የተሻለ ሀገር፣ ተዘልሎ መኖር ቢያጋጥም መንፈስ ቅዱስን ስማው! ወደ አየልዎ ቦታ፣ ወደ አዘጋጀልዎ ይዞታ፣ ወደ አሰበልዎ ከፍታ እንዲወጡ መንፈስ
ቅዱስን ይስሙ!
ወዳጄ ሆይ፣ የሚፈልጉት ነገር አገልግሎት ቢሆን ወይንም አስተምህሮት፣ መቀበል
ቢሆን ወይንም መስጠት፣ ምክር ቢሆን ወይንም ምሪት መንፈስ ቅዱስን ይስሙ! የሚመኙት ነገር መጋቢነት ይሁን እረኝነት፣ ሰባኪነት ይሁን አስተማሪነት፣
ሐዋሪያነት ይሁን ነቢይነት መንፈስ ቅዱስን ይስሙ!
ወዳጄ ሆይ፣ መንፈስ ቅዱስን መስማት ከድካም፣ ከልፋት፣ ከክስረት ያድናል!
መንፈስ ቅዱስን መስማት ከውርደት፣ ከውድቀት፣ ከአደጋና ጥፋት ያስመልጣል! ከእርሱ ያልሆነ ጎዳና–መንገዱ፣ ዕድልና–በሩ፣ ምርጫውና–ምንጩ
እንዲዘጋ መንፈስ ቅዱስን እንስማ!
ከእግዚአብሔር ያልሆነ ቪዛም ሆነ ቪላው፣ አቻና ጋብቻው አደጋው ብዙ ነው! ስለሆነም
መንፈስ ቅዱስን በመስማት ከድካም፣ ከልፋት እንዲሁም ከክስረት ማምለጥ ይሁንልን!
--------------------------------
(ትምህርቱ
ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር
ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)
No comments:
Post a Comment