Tuesday, November 25, 2014

ድንግልና ሲያሳፍር !

ዲቮሽን ቁ.765/07     ማክሰኞ፣ ሕዳር 16/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

ድንግልና ሲያሳፍር !  

ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ (1 ቆሮ 7፡36)

አንዳንድ እጮኛሞች ጋብቻ ሳይፈጽሙ ለረዥም ዓመታት አብረው ይቆያሉ፡፡ ከጋብቻ በፊት እንዲሆንላቸው አጥብቀው የሚሹት ነገሮች አሏቸው! ኢኮኖሚና ሀብት፣ መኪና እና ቤት፣ ትምህርትና ስኬት ወይንም ሌላ ምኞት አላቸው! ምኞታቸው ሳይሞላ ለዓመታት ያህል ሳይጋቡ ቢቆዩ ማፈር ይጀምራሉ!

ከጋብቻ ሀብትን፣ ከትዳር እውቀትን ለማስቀደም ስንሞክር ዓመታት ያልፋሉ፡፡ በዚህም ሒደት ውስጥ እንደ አበባ ፈክቶ የሚጠወልገው የሴት ልጆች ውበት መክሰም ይጀምራል!

ታውቃላችሁ፣ በኢኮኖሚ ምክንያት እጮኛሞች ሳይጋቡ ሲቆዩ ያሳፍራል! እንደ ፈካ አበባ የምታምረው ወጣት እጮኛ አግኝታ ሳታገባ ብትቆይ በጣም ያሳፍራል! በእጮኝነት ሰበብ፣ በኢኮኖሚ ሰበብጋብቻ ዘግይቶ፣ የቆንጂቷ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ፣ የፊቷ አበባ መጠውለግ ሲጀምር ለሴት ያሳፍራል!   

ታውቃላችሁ፣ የንቦቹ አጀብ ዙሪያው የሚከበብ ያ ውብ አበባ፣ ከቆይታ ብዛት  ፈላጊው ሲጠፋ ለሴት ያሳፍራል! ማግባት በሚገባት ዕድሜ ሴት ቶሎ ካላገባች፣ የፊቷ አበባ እስከነፈላጊው አብሮ ይጠወልጋል! ይህም ያሳፍራል!

ታውቃላችሁ፣ ሲወዱት ጠልቶ–ሲጠሉት መውደድ፣ ሲጠጉት ሸሽቶ–ሲርቁት ማባረር፣ ሲፈልጉት ተደብቆ–ሲደበቁት መገኘት ያሳፍራል!

ወገኖች ሆይ፣ ዕድሜያችን ለጋብቻ ሲደርስ፣ ሀብት ኖረም አልኖረ፣ ሰርግ ተደረገም ቀረ፣ ድግስ ተዘጋጀም ቀረ ዋናው መጋባት ነው! ጋብቻ ክቡር ነው፡፡ ጋብቻ አያሳፍርም! በጋብቻችን ቀን ድግስ ሳንደግስ፣ ጮማ ሳይቆረጥ፣ ቅልጥም ሳይገሸለጥ፣ ከበሮ ሳይደለቅ ማግባት ከፈለግን የወደድነውን እናድርግ! ኃጢአት የለብንም!

ወገኖች ሆይ፣ ማግባት ወደሚገባን ዕድሜ ደርሰን እንደሆነ በጊዜ ለማግባት በጭራሽ አንፈር!  የወደድነውን እናድርግ! ያለ አጃቢና ያለ አጨብጫቢ፣ ያለ ፈረሰኛ ያለ ጋላቢና ያለ አሸብሻቢ መጋባት ብንፈልግ የወደድነውን እናድርግ!

ወገኖች ሆይ፣ ጋብቻ በክርስቲያናዊ ሥርዓት ይፈጸም እንጂ፣ በመኖሪያ ቤትም ተከናወነ በሕዝብ አደባባይ ልዩነት የለውም! ይህንን ብናደርግ–ኃጢአት የለብንም!
ኃጢአቱ ሳይጋቡ መዳራት፣ ሳይዳሩ መዘሞት፣ የዘሞቱን መጥላት፣ የጠሉትን መፍታት ነው!
--------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያደርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment