Sunday, November 30, 2014

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#1) – የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት!


ዲቮሽን ቁ.81/07     እሁድ፣ ሕዳር 21/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)

የጴንጠቆስጤነት አቡጊዳ(#1) – የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት!

በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው (የሐዋ 2፡1-2)፡፡

ለጴንጠቆስጤነት ማንነት መሠረቱ፣ መፈተሻና መለኪያው የበዓለ ኀምሳ ቀን ነው፡፡ በዕለቱ የተከሰቱ ሁነቶችና ድርጊቶች፣ ስብከቶችና አስተምህሮዎች እንዲሁም ማናቸውም የዕለቱ አስተሳሰቦች ለጴንጠቆስጤነት ማንነት መለኪያና ማናጻጸሪያ ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ጴንጠቆስጤነት የሚጀምረው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነው! ይህ ጥምቀት ጌታን እንደግል አዳኛቸው አድርገው በተቀበሉ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ክስተት ነው፡፡ ይህ ክስተት ሰዎች ጌታን በተቀበሉ ዕለት ወይንም በኋላ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ነገር ግን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መቀበል እና ጌታን መቀበል ሁለቱም የተለያዩ ልምምዶች ናቸው፡፡ በበዓለ ኀምሳ ቀን የሆነው ክስተትም ይህንን እውነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከአብ የተሰጠ የተስፋ ቃል ነው፡፡ ይህን የተስፋ ቃል መቀበል ውስብስብ ነገር አይጠይቅም፡፡ የሚያስፈልገው የተስፋ ቃሉን በጸሎት መጠበቅ ነው፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጥቁርና ነጭ መገለጫው ‹‹የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት›› ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ ከደቀመዛሙርቱ ጋር ለአርባ ቀናት አብሮአቸው ቆይቶ ነበር፡፡ ጌታችን የምድር ቆይታውን ጨርሶ ከማረጉ በፊት ለደቀመዛሙርቱ የነገራቸው ‹‹ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ›› ብሏቸው ነበር(የሐዋ 1፡4-5)።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ከማረጉ በፊት የነገራቸውን ይህን ትምህርት ደቀመዛሙርቱ ተቀብለው ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ይጠብቁት የነበረው መንፈስ ቅዱስ በድንገት መጣ፡፡

ታውቃላችሁ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አቅጣጫው ከላይ ከሰማይ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ድንገተኛ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ድምጻዊ ነው፡፡ የሚደመጥ፣ የሚሰማ፣ ድምጽ አለው፡፡ ስለሆነም በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁ ድምጽ አውጥተው ሊጮኹ፣ ሊያጨበጭቡ …ይችላሉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት እንደ አውሎ ንፋስ ነው –ነቅናቂ፣ አነቃናቂ፣ ቀስቃሽ፣ አንቀሳቃሽ፣ ወዝዋዥ አወዛዋዥ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ወንበራቸው ሊነቃነቅ፣ ሰውነታቸው ሊርገፈገፍ፣ ሊንዘፈዘፍና ሊንቀጠቀጠቀጥ ይችላል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ከሹም ፊት፣ ከሕዝብ ፊት፣ ከምናከብራቸውና ከምንፈራቸው ሰዎች ፊት ስንቆም ሰውነታችን በፍርሃት ይንቀጠቀጥ የለ? ስሜታችንን የሚነካ ደስታ ስንሰማ ድምጻችንን አውጥተን እልልታችንን ይሁን ጭብጨባችንን ወይንም ጩኸታችንን እንገልጽ የለ? ጥልቅ ሐዘን ሲያጋጥመን ድምጻችንን አውጥተን እናለቅስ የለ? ታዲያ፣ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ስሜታቸውን ቢገልጹ፣ ድምጻቸውን ቢያሰሙ ለምን እንደነቃለን?

ወገኖች ሆይ፣ የሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ድንገት ሲመጣ ክራባቱን አስተካክሎ፣ እግሮቹን አነባብሮ ተረጋግቶ የሚቀመጥ ሰው ይኖራል? ታዲያ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ድንገት ሲመጣ ሰዎች ቢንቀሳቀሱ፣ ቢወዛወዙ፣ ቢጮኹ ምን ያስገርማል? የበዓለ ኀምሳው ክስተት ይህን ያስተምራል!

          --------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ወዳጅ ጓደኞችም እንዲያገኙ ያግዙ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!)

No comments:

Post a Comment