Sunday, June 21, 2015

ምርኮን ተካፈለች

ዲቮሽን 285/07 ሰኞ፣ ሰኔ 15/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)
ምርኮን ተካፈለች
በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች። መዝ 68፡ 12
ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ሕብረት፡ አንዳንዴ መልካም የምንላቸው ጊዜያት፣ አንዳንዴም ከባድ የምንላቸው ወቅቶች ይኖራሉ። አንዳንዴ በበረከት ላይ በረከት እየተደራረበልን ለመቁጠር ያስቸግረናል፣ አንዳንዴም በፍጹም ማጣት እና መራቆት ውስጥ እናልፋለን። አንዳንዴ በምስጋናና በዝማሬ ስንጥለቀለቅ አንዳንዴም በልቅሶና በፍርሃት፣ እንሰጥማለን።
አንዳንዴ ደግሞ፣ በእምነት ስንሞላ አንዳንዴም ደግሞ በጥርጣሬና በስጋት እንዋጣለን። አንዳንዴ ደግሞ በሞገስ ስንወጣ፣ አንዳንዴ ደግሞ በውርደት አንገታችንን እንደፋለን።
ሞላም ጎደለ ግን ዋናው ነገሩ፣ ስንችል እየዘመርን፣ ሲያቅተን እያለቀስን፣ ሲሆንልን በብርታት፣ ሳይሆንልን በድካም፣ ሲደላን እየበረርን፣ ሳይደላን በእንብርክካችን ሆነን፣ በጌታ ቤት፣ በመንፈሱ አፀድ ውስጥ መገኘትን የመሰለ ትልቅ ቁምነገር የለም።
ምክንያቱም፣ አንድ ቀን፣ ጌታ ልጆቹን ሊያስብ በሚመጣበት ቀን፣ ምርኮ ተካፋዮች መሆናችን የማይቀር እውነት ነው። ጌታ በእርግጥ፣ ወደ እያንዳንዳችን ነገር መምጣቱ አይቀርም። ዛሬ ላይ፣ ይህ ነገር እውነት ባይመስለንም፣ በእርግጥ ጌታ መምጣቱ አይቀሬ ነው። ያኔ ግን፣ በቤቱ መገኘት ይሁንልን።
ጌታ ልጆቹን ሊጎበኝ ሲመጣ እንዳያጣን፣ በቤቱም የተገኙት ምርኮ ሲካፈሉ፣ እኛ በደጅ እንዳንቀር፣ የበረከት ዝናብ መውረዱንም በዝና ብቻ ሰሚዎች ሆነን፣ ተካፋዮች ሳንሆን ግን እንዳንቀር፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፣ በቤቱ ውስጥ እንገኝ።
አባት ሆይ፣ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ ነህና፣ ዛሬ፣ የተፍገመገምነውን ሁሉ፣ በክንፎችህ ጥላ ውስጥ ሸሽገን። ሰምተህኛልና አመሰግንሃለሁ።
ትምሕርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ፣ እባክዎ ላይክ፣ ሼር
እና ኮሜንት ያድርጉ፤ ጌታ ይባርክዎ።

No comments:

Post a Comment