Sunday, June 21, 2015

መረጥሁ!!!

ዲቮሽን 284/07 እሁድ፣ ሰኔ 14/07
(በእህት ማርታ ሲሳይነህ)

መረጥሁ!!!

በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ። መዝ 84፡ 10

መቼም በዚህ ምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ አላፊ ነው። ወይ እኛ እናልፋለን፣ ወይም ያ የጓጓንለት ነገር ያልፋል፣ በመጨረሻም ሰማይና እና ምድር እንኳን ያልፋሉ። ብቻ ምናለፋችሁ፣ በዚህ ምድር ላይ ቋሚ የሆነ አንዳችም ነገር የለም።

ስለዚህ፣ ዛሬ፣ ለዚህ ምድር ሆይ ሆይታ እና አጓጓል ድንዛዜ፣ ምኞት እና ግርግር ልዩ የሆነ “እምቢ ለእርኩሰት” የሚያሰኝ የጭካኔ መንፈስ እንዲገባብን እኔ እጸልያለሁ።

ዳዊት በኃጥአን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ፣ ያለው እኮ፣ “ጸሎቴም ባይመለስ፣ የምፈልገውን ዝናና ክብርም ባለገኝ፣ በድህነት በበሽታም ብኖር፣ በማጣት በጉስቁልናም ብመታ፣ በውርደትና በነቀፌታ ብመላለስም፣ የምፈልገውን የአገልግሎት ደረጃና ስልጣን ባላገኝም፣ ያማረኝን ባልለብስና ባልጠጣም፣ አሪፍ መኪናና ቤት ባይኖረኝም፣ ሰዎች የሚገባኝን ከበሬታ ባይሰጡኝም፣ የያዝኩት ሁሉ ከእጄ ቢበተን፣ . . . ሌላ ቦታ ሄጄ፣ ይህን ሁሉ ከማገኝ፣ ከአምላኬ ጋር ተስማምቼ፣ ፈቃዱን ብቻ አድርጌ፣ ደስ የሚያሰኘውን ነገር ብቻ ሆኜለት፣ ህይወቴ ትለፍ” ማለቱ ነው እኮ።

ደግሞስ፣ እውነት እንነጋር ከተባለ ማነው እግዚአብሔርን ተደግፎ፣ አምኖና ተመርኩዞ ከበጎ ነገር ሁሉ የጎደለ! ዳዊት ይህን ሲል እኮ፣ እግዚአብሔርን በደንብ አድርጎ ስለሚያውቀው፣ አንዳችም ነገር እንደማያጣ አውቆም ጭምር ነው።
ወዳጅ መንፈስ ቅዱስ ሆይ፣ ዛሬ አእምሯችንን አይናችንን ልባችንን እጃችንን እግራችንን . . . ሁለንተናችንን ትቆጣጠር ዘንድ በኢየሱስ ስም ጸለይኩ። ሰምተህኛልና ተባረክ። አሜን።

ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እንግዲያውስ እባክዎ ላይክ እና ሼር ኮሜንትም ያድርጉ፤ ጌታ ይባርክዎ።

No comments:

Post a Comment