Sunday, June 21, 2015

እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት

ዲቮሽን 283/07፥ ቅዳሜ፥ ሰኔ 13/07
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)

እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት

የጠለቀ መንፈሳዊ ጉዞ ለመጓዝና እየጨመረ የሚሄድ ርካታና እረፍት እንድናይ ካስፈለገ፣ የክርስትና ሕይወት ትጋትን ይጠይቀናል(ዕብ 4:11)፡፡ ትጋታችን በጨመረ ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ጸጋ በሕይወታችን እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ለመንፈሳዊ ነገር ያለን መሻት እያደገ ይሄዳል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ግሥገሣ ውስጥ ባለማሰለስ ስንገኝ፣ እሱን ለማወቅ ያለን ራብ እየተለቀ ስለሚመጣ፣ እየጨመረ ለሚሄድ ፍለጋ እንጠናከራለን፡፡ ይህንን በእንግሊዝኛው አገላለጽ positive vicious cycle ይሉታል፡፡ ማለትም ትጋቱ የጨመረ መንፈሳዊ ራብን ይወልዳል፤ የጨመረ መንፈሳዊ ራብ ደግሞ ሌላ ከፍ ያለ ትጋትን ይወልዳል - መቸም ኡደቱ ማቆሚያ የለውም እኛ በሥጋዊ አካሄዶች እስካላጠፋነው ድረስ!

እየጨመረ የሚሄድ የክርስትና ሕይወት ብዙ ግብዓቶችን ይፈልጋል፡፡ መልካም የእምነት ውጊያንና ዲያቢሎስን በኃይል ጸንቶ መቃወም ይጠይቃል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ሳይታክቱ ማሰላሰልና በፊቱ ጥሩ የሆኑ ጊዜዎችን ማሳለፍ ግድ ይለናል፡፡ ሁኔታዎችንና ሥጋችንን ሳናዳምጥ የሚከፈሉ ዋጋዎችን እንደ ጌታ ፈቃድ መክፈልን ይጠይቀናል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕይወቴን የቀየረና ብዙ ቦታ ደጋግሜ የምጠቅሰውን መርሕ እዚህ ጋ ልጥቀስ፡፡ ሦስት በተሰናሰለ መንገድ የተቀመጡ ድርጊቶች በውጤት ሂደት እንዲህ ተቀምጠዋል፡-

ድርጊት(Action)------->ልማድ(Habit)------->ጠባይ(character)
ይህንን መርሕ ለመግለጽ ጸሎትን እንደ ምሳሌ ልውሰድ፡፡ ጸሎትን ደጋግመን ስናደርገው ወደ ልማድነት ይቀየራል፡፡ በሕይወታችን ልማድ እየሆነ ያለውን ይህንን ተግባር እየጨመርን ደጋግመን ስናደርገው ጠባያችን ወይም መገለጫ ባሕርያችን ይሆናል፡፡ ከዚያማ ውጤቱ እንዲህ ይሆናል፡- መጸለይ እንጂ አለመጸለይ አንችልም፡፡ በፊቱ መሆን እንጂ አለመሆን ያቅተናል - የሚጓጓለት ድንቅ ለውጥ!

የላይኛውን ሐሳብ የሚደግፉና የክርስትና ሕይወት እየተቀጣጠለ፣ እያደገና እየጨመረ የሚሄድ ሕይወት እንደ ሆነ የሚጠቁሙ ብዙ ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሦስቱን ልጥቀስ፡-እስከ እግዚአብሔር ፍጹም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ (ኤፌሶን 3፡19)፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ (ሮሜ 12፡11)መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና/ብዙ የሚያሰክሩ ነገሮች እንዳሉ ልብ ይሏል/(ኤፌሶን 5፡16-20) የእግዚአብሔር ሰው ስሚዝ ዊግልስዎርዝ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “በዛሬው ቀን ትላንትና የነበርክበት ቦታ ላይ ከተገኘህ የኋሊት እየሄድክ ነው"
በተሰጠ ማንነት፣ ልባችን መሉ በሙሉ በጌታ ላይ ሆኖ ከላይ በተጠቀሰው ዓይነት ፍለጋ(craving) እና ትጋት ስንቀጥል፣ የጌታ አብሮሆት ከመቸው በሚበልጥ ሁኔታ በሕይወታችን ዕውን ይሆናል፡፡ ከዚህም የተነሣ የምናገኘው የመጀመሪያው በረከት በቃላት ልንገልጸው የማንችለው ሰላም፣ መረጋጋትና ደስታ ይሆናል፡፡ መንፈሳዊ መረዳታችንም እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ጌታን በሚገባ እያወቅነው እንመጣለን፡፡ መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በጨመረ ሁኔታ እየተከፈቱ ስለሚመጡ፣ ብዙ ረብ የሌላቸውን ነገሮች የመጣል መነሣሣትና አቅም እያገኘን እንመጣለን፡፡

እንደዚህ በጽናት ሳናሰልስ የጌታን ፊት በጨመረ ሁኔታ በፈለግን ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ኃይል በውስጣችን እየጨመረ ስለሚሄድ፣ ብዙ ቀንበሮች ከሕይወታችን ይሰበራሉ፡፡ ስለዚህም ከበፊቱ ይልቅ በሕልውናው ውስጥ መቆየት አያስቸግረንም፡፡ ብዙ ሰዓት በፊቱ መሆንም ያለ ጥርጥር ፈቃዳችን ይሆናል፡፡

ቃሉ ተግተው የሚሹኝ ምስጉኖች/የተባረኩ ናቸው(ምሳሌ 8፡34) ይላልና፣ ለሚሹት በታማኝነት የሚገለጠው ጌታ ሕይወታችን ሲጎበኝ የሚመጣው ለውጥ ለሌሎች በረከት ያደርገናልና በጨመረ ሁኔታ ተግተን እንፈልገው!
ጌታ ሆይ እርዳን!!

“አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፣ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። ወንድሞች ሆይ፣ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” ፊልጵስዩስ 3፡7-13)

No comments:

Post a Comment