Tuesday, June 23, 2015

በሕንጻ ግንባታ ለተጠመዱ አብያተክርስቲያናት!

ዲቮሽን 286/07 ማክሰኞ ሰኔ 16/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

በሕንጻ ግንባታ ለተጠመዱ አብያተክርስቲያናት!

የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፥ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር። ( ነህምያ 8 : 8)

የነህምያ መጽሐፍ በምናነብበት ጊዜ ከምርኮ ተመላሽና ሳይማረኩ የቀሩ እስራኤላውያን የቃልኪዳን ምድራቸውና የገዛ ርስታቸው በሆነች ግዛታቸው ላይ አጋጥሟቸው የነበረውን የስነልቦና፥ የመንፈስና የሞራል ውድቀት፥ እንዲሁም ማኅበራዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክስረት ለመለወጥ ያደረጉትን የሕዳሴና መልሶ ግንባታ ተጋድሎ ያሳያል፡፡

በነህምያ አመራር የፈራረሰችውን የእስራኤልን ቅጥር መልሶ የመገንባቱ ራዕይ በተሳካ ሁኔታ ፈር እንደያዘ፥ ወዲያው ደግሞ እዝራ የሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት መልሶ ግንባታ ቦታ እንዲይዝ ሲሰራ እንመለከታለን፡፡

እዝራ በሕንጻ ግንባታ ለተጠመዱ እስራኤላዊያን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ እያነበበ፤ እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፡፡ ሕዝቡም ደግሞ እዝራ የሚያነብበውን ቃል ያስተውሉ ነበር። ይህም በመሆኑ፥ በምድሪቱ ላይ ከጫፍ ጫፍ የሚደርስ ሪቫይቫል ተቀጣጠለ፡፡

ወገኖች ሆይ፥ በሀገሪቱ ሪቫይቫል ሲመጣ፥ ቀደም ሲል ወድቆ የነበረው የሕዝቡ ስነልቦና፥ የመንፈስና የሞራል ውድቀት፥ እንዲሁም ማኅበራዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክስረት በመለኮታዊ ኃይል ተቀየረ! በመላ ሀገሪቱ ከዳር እስከዳር የምስጋናና የድል ዜማ ይደመጥ ጀመረ!

ወገኖች ሆይ፥ በሀገራችን በኢትዮጵያ ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ መላው የኢትዮጵያ አብያተክርስቲያናት ከከተማ እስከ ገጠር በሕንጻ ግንባታ ስራዎች ላይ ተጠምደው፥ በተቃራኒው ደግሞ የሕዝቡ መንፈሳዊ ግንባታ ተስተጓጉሎ ወይንም ችላ ተብሎ እናያለን፡፡ ለሕንጻ ስራ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ፥ መንፈሳዊ ግንባታው ግን ተዘንግቶ እንታዘባለን፡፡

በሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ተጠምደው የሚገኙ የኢትዮጵያ አብያተክርስቲያናትና የሕዝቡን መንፈሳዊ ግንባታ ቸል ያሉ መሪዎች፥ ከእዝራና ከነሀምያ ይማሩ!

መሪዎች ሆይ፥ ከሕንጻ ግንባታችሁ ጎን ለጎን፥ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል የማስተማሩን ስራ አትዘንጉ፥ ለቁሳቁስ በምትሰጡት ትኩረት መጠን፥ ወይንም ከሕንጻ ፕሮጀክቶች ይልቅ ለእግዚአብሔር ሕዝብ መንፈሳዊ ዕድገት ትልቅ ትኩረት ስጡ፡፡

መሪዎች ሆይ፥ መንፈሳዊ ፕሮጀክቶችን ችላ አትበሉ! ሕዝቡ እግዚአብሔርንና ቅዱስ ቃሉን እንዲያውቅ ትጋትን ጨምሩ፡፡ ከእዝራ ከነህምያ፥ ይህንን ተማሩ!

No comments:

Post a Comment