Sunday, June 21, 2015

አትፍራ!

ዲቮሽን 281/07 ሓሙስ ሰኔ 11/07
( ወንድም ጌታሁን ሓለፎም )

አትፍራ!

ዘፍ 15፡1 “ከዚህ ነገር በሗላ የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብርሃም መጣ እንዲህ ሲል አብርሃም ሆይ አትፍራ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው ፡፡”

አባት ለልጁ ሁል ግዜ “አይዞህ እኔ አባትህ በህይወት እስካለሁ ድረስ ምንም ነገር አይገጥምህም ፤ ሁል ጊዜ ከጎንህ ነኝ ፤ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን አትፍራ አትታወክ አትደንግጥ ካንተ ፈጽሞ አልለይህም ” ይለው ነበር ፡፡
ልጅም ከህጻንነቱ ጀምሮ “አይዞህ” የሚለውን እና የሚያበረታውን የአባቱን ድምጽ እየሰማ ስላደገ ፤ በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢያልፍ ሳይፈራ እና ሳይደነግጥ በነጻነት ይወጣ እና ይገባ ነበር ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ለሚገጥመው አስቸጋሪ ሁኔታ ቃል የገባለት አባቱ አጠገቡ እየተገኘ ይረዳው እና ለችግሩ ይደርስለት ስለነበረ ይበልጥ አባቱ ላይ መደገፍ
ሆነለት ፡፡

ከእለታት ባንዱ ቀን ግን እንዲህ ሆነ ፤ ለወትሮው ከአባቱ ጋር አንድ ላይ ያቁዋርጠው በነበረ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ በኩል ብቻውን ማለፍ ግድ ሆነበት ፡፡ ጥቂትም እንደተጓዘ ከሩቅ አንድ የአንበሳ ደጎል እያገሳ ወደ እሱ ሲገሰግስ አየ፥ ብላቴናውም አካባቢውን ሲመለከት ከእሱ በቀር ሌላ ማንም ሰው የለም ፡፡ በልቡ ውስጥ ድንጋጤ እና ፍርሃት ሲሰማው ታውቀው ፡፡

ያንበሳውም ደጎል ይበልጥ እየገሰገሰ ወደሱ መቅረብ ጀመረ ፡፡ ብላቴናውም በፍርሃት ውስጥ እንዳለ በውስጡ የአባቱ ድምጽ አቃጨለበት “አይዞህ እኔ ከአንተ አልለይም ” ብላተናው ግን በዚህች ቅስበት ብዙ ጥያቄ ይመላለስበት ነበር “

ዛሬ ግን አባቴ ለምን ተለየኝ ፤ ለምን እንዲህ ባለ አስፈሪ ወቅት ያውም በዚህ በጫካ ለምን አባቴ ከኔ ተለየ አይዞህ አልለይህም ይለኝ አልነበረም ወይ ? ” እያለ የበለጠ ፍርሃት እና ድንጋጤ ውስጥ ገብቶ ያሰላስል ነበር፡፡

በዚህ መሃል እየገሰገሰ የመጣው አንበሳ ዘሎ እላዩ ላይ ሊከመርበት ሲል ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ ሲሰማ እና አንበሳው መሬት ላይ ሲደፋ አንድ ሆነ፡፡ የተከሰተው ነገር ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ ታላቅ ፍንዳታ ወደተሰማበት ስፍራ ዘውር ብሎ ሲመለከት አባቱን ከነ ጠበንጃው በታላቅ ፈገግታ ሆኖ ቆሞ ሲመለከተው አየ ፡፡

ብላቴናውም እየሮጠ አባቱ ላይ ተጠመጠመ ፡፡ እንዲህም አለው አባቴ አመሰግንህ አለሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ፍርሃት ተሰምቶኝ ነበር አንበሳው ይበላኛል ብየ ተስፋም ቆርጨ ነበር እውነት
ነው እንደ ቃልህ ታምነህልኛል አለው ፡፡

ይገርማል በቃሉ የምንፈተንበት ቀን ለካ ይመጣል?

ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ከገጠምን ችግር እና መከራ የተነሳ ፤ የነገራችን ፍጻሜ የመጨረሻው መራፍ ላይ የደረስን የመሰለን ? እግዚአብሔር ላንበሳና ለተኩላ አሳልፎ እስኪሰጠን ድረስ ዝም ብሎናል ትቶናል እረስቶናል ያልን ?

ስንቶቻችን ነን ጌታ በተለያየ ወቅት እና ጊዜ በቃሉ በነበያቱና ባገልጋዮቹ ተናግሮን ፤ አልጥላችሁም አልተዋችሁም ብሎን አሁን ግን ከምናልፍበት እና ከተጋረጠብን ፤ፈቀቅ አልል ካለን መከራ የተነሳ ተስፋ የቆረጥን ? እግዚአብሔር ተናግሮን ሲያበቃ ፊቱን ከኔ መልሶአል በአጠገቤ የለም የምንል ስንቶቻችን ነን ?

ወገኖቼ እሱ እግዚአብሔር ነው እና ፤ በሰማይ እና በምድር በባህሩና በጥልቁ የወደደውን የሚያደርግ አምላክ ነው እና፤ እርሱ የትንሳኤ አምላክ እና አባት ነው እና በውነት ጊዜው ይርዘም እንጅ ነገሮች አፍጥጠው ሊወርሱን ፤ ሊያሸንፉን አጠገባችን የተጋረጡ ይምሰለን እንጅ እግዚአብሔር እንደተናገረን እንዲሁ ይሆናል ፡፡

አብርሃም ስለ ልጅ መውለድ ጉዳይ ብዙ ዘመን ጠብቆ ጠብቆ 25 አመት በዘገየበት የተስፋ ቃል ምክኒያት በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ አለ“ የቤቴ መጋቢ ደማስቆአዊው ኤሌዘር ሊወርሰኝ ነው ” አብርሃምን ድንገት
ድንጋጤ ጋረደው ፤ ፍርሃት ወረረው ፤ ለካስ ለዚህ ነበር ገና ከጅምሩ ከጧቱ እግዚአብሔር“አይዞህ” ብሎ የተናገረው መጽሓፍ ቅዱሳችን ላይ ወደ 365 ጊዜ የሚሆን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ አትፍራ የሚል ቃል ተጽፎ እናያለን ፡፡
እግዚአብሔር ለምንድን ነው ይህን ያህል አጠንክሮ “አትፍሩ” እያለ የሚናገረን ?“ በራሴ ጊዜ እመጣለሁ ፤ በራሴ ፈቃድ እና እቅድ እሰራለሁ ስለዚህ ነገር የዘገየ ቢመስልም ቃሌን እፈጽማለሁ እና እስከዚያው አይዟችሁ አትፍሩ ጠብቁ ” እያለን እኮ ነው ፡፡

እኔና እናንተ በተለያየ ችግር እና መከራ ውስጥ ስናልፍ ቀለል ባሉ ጉዳዮች ላይ እየታመነው ብዙ የሆነውን እርዳታ እየተቀበልን ብዙ ዘመን አልፈናል ፡፡ ነገር ግን የጠነከረ ወይም ካሰብነው በላይ ያገጠጠ ችግር ሲገጥመን ፍጹም መታመናችን ይጠፋል ፡፡ ነገር ግን ዛሬም ጌታ አትፍሩ አትደንግጡ እመጣለሁ እያለን ነው ፡፡

አሜን እግዚአብሔር ጋሻችን ነው እና አንፈራም !!!!

ይህንን መልእክት ሼር እና ላይክ በማድረግ ጌታን ያገልግሉ ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ

No comments:

Post a Comment