Sunday, June 21, 2015

'የውሸት እየኖርን' -- የእውነት እንሞታለን!

ዲቮሽን 280/07፥ ረቡዕ ሰኔ 11/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

'የውሸት እየኖርን' -- የእውነት እንሞታለን!

ለዛሬው ዲቮሽን ርዕሴ ያደረግሁት አባባል፥ ታክሲ ውስጥ ተለጥፎ ያየሁት ነው! ይህን አባባል ማን እንደተናገረው የሚገልጽ ምንጭ ባላገኝም፥ ትልቅ አባባል መሆኑን ግን ደፍሬ እናገራለሁ፡፡

አዎ፥ የአንዳንዶቻችን ኑሮ የውሸት፥ የሽንገላ፥ የለበጣና የማስመሰል ኑሮ ነው፡፡ ነገረ ሥራችን ሲታይ፥ ከቤታችን ሌላ፥ ከቤት ውጭ ሌላ ነው፡፡ ከሰው ጋር ስንሆን ሌላ ለብቻችን ስንሆን ሌላ፡፡ የምናስበው ሌላ የምንናገረው ሌላ፡፡ የልባችን ሌላ፥ የከንፈራችን ሌላ! የሆዳችን ሌላ፥ የጥርሳችን ሌላ!

አዎይ የኛ ነገር፥ የኛ ነገርና እኛ ግራ ግብትኛ ነው! እየራበን እንግደረደራለን፥ አያማረን እንገፋለን፡፡ እየወደድን እየፈለግን የሆድ የአንጀታችንን እንሸሽጋለን፡፡ ከውስጥ እያለቀስን ከውጭ እንስቃለን፥ ከውስጥ እየሳቅን ከውጭ እናለቅሳለን፡፡ ውስጣችን ጮቤ እየረገጠ፥ በውጫችን ደረት እንደቃለን፡፡

አቤት የኛ ነገር፥ የኛ ነገርና እኛ፥ ግራ ግብትኛ! ንግግራችን ውስጠ ወይራ፥ ላይ-ላያችን ሌላ፥ ታህ-ታያችን ሌላ! አይጧ በበላች ደዋ፥ አህያ ፈርቶ ዳውላ፡፡ ፍየላችን ወዲህ፥ ቅምዝምዛችን ወዲያ፡፡

የአንዳንዶቻችን ሕይወት 'ፌክ' ይበዛበታል፡፡ ወዳጅ ከወዳጁ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ፌክ፥ አንዱ ከሌላው ጋራ በሚኖረው ኅብረት ፌክ፥ በንግድ በገበያው ፌክ፥ በሱቅ በፋብሪካው ፌክ፥ በፖለቲካው መድረክ ፌክ፥ በየሐይማኖት ተቋሙ ፌክ፥ በየትምህርት ተቋሙ፥ በየቤተክርስቲያኑም ሆነ በየቤተክሲያኑ ፌክ፥ በየቦታው ሁሉ ፌክ ሞልቷል፡፡
ይህን ይህን ስናይ፥ "እውነትም "የውሸት እየኖርን" ያለ ይመስላል፡፡ እርግጥ ነው፥ የውሸት እየኖርን የውሸት አይሞትምና፥ የውሸት ብንኖርም የእውነት መሞታችን አይቀሬ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፥ የውሸት መኖር ይቅርብን! የእውነት ኑሮ መኖር ዛሬውኑ እንጀምር!

… ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ (ኤፌ 4፡25)

No comments:

Post a Comment