Tuesday, June 30, 2015

የማይሰማ ጩኸት !

ዲቮሽን 288/07 ሓሙስ ስኔ 18/07
( ጌታሁን ሓለፎም )
የማይሰማ ጩኸት !
“ጌታ ሆይ ማን ምስክርነታችንን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ ?” (ዮሓ 12፡-38)
ወጭ አውጥቶ፥ ለፍቶበት እና ብዙ ተጨንቆ አስቦ አልሞ ሽር ጉድ ብሎ ያዘጋጀውን ግብዣ ታዳሚው በሰአቱ መጥቶ ሲበላ ሲጠጣ ሲያይ ጋባዥ ደስ ይለዋል ፡፡ ከደስታውም ብዛት “ብሉልኝ ጠጡልኝ ” እያለ አደግድጎ ያስተናግዳል፥ በተለይ እማ የምግቡ ጣእም እና መስተንግዶውን መልካም እንደነበረ እያደንቁ “ አቤት አቤት እንዲህ ነው እንጅ ግብዣ ማለት እጅ ይባረክ ብለናል” እያሉ ስለ ግብዣው ሲያመሰግኑ ሲመርቁ
ጋባዥ ጆሮ ውስጥ የገባ እንደሆነማ ፤ ይኮራል ፤ ሓሴት ያደርጋል ደስታው ወሰን ያጣል ፡፡ ልፋቱ ከንቱ እንዳልቀረ ያስባል ፡፡
ሰው የወለደውን ሲስሙለት ፤ ልጆቹ አድገው ለቁም ነገር ሲበቁለት ፤ ስራውን ሲያደንቁለት ፤ በርታ አይዞህ ሲሉት ይወዳል፡፡ ምክሩ ሲደመጥለት ፤በሸንጎ ለመፍትሄ ሲፈለግ ኩራት ይስማዋል
በአንጻሩ ግን ገንዘቡን አቅሙን አሟጦ ጉልበቱን ያፈሰሰበት ግብዣ ላይ ፤ ታዳሚው ሳይመጣ ቢቀር የተዘጋጀው ድግስ በይ ቢያጣ ፤ ሰው የመከረው ምክር በሰዎች ዘንድ ዋጋ ቢስ ቢሆን ፤ ባይደመጥ ፤ የመፍትሔ ሃሳብ እንዳለው ውስጡ እያወቀ ምክሩን ቢያጣጥሉበት ያ ሰው ይከፋል ያዝናል ፡፡
አዎ እንዲሁ ነው ነብዩ ኢሳያስም ስለ ክርስቶስ እየሱስ ያለውን መረዳት ስለ አምላክነቱ ስለ ጌትነቱ ስለሁሉን ቻይነቱ ስለአዳኝ እና ታዳጊነቱ የገባውን እውነት ቢሰብክ ቢመሰክር ሰዎች ስለአልተረዱት አዘነ ውስጡ ተሰበረ ፡፡ አሻግሮ የመሲሁን መምጣት ቢያይ ፤ በውስጡ የበራለትን ብርሃን ለሰዎች ሊያስረዳ ቢፈልግ ሰሚ ቢያጣ እንዲህ አለ “ ጌታ
ሆይ ማን ምስክርነታችንን አመነ የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገለጠ ?”
“ ጌታ ሆይ ለኛ የተገለጠልንን እውነት የዳንበትን ተስፋ በውስጣችን ያፈሰስከውን የማያሳፍር ፍቅር ለሰዎች ብንናገር ብንመሰክር አላመኑንም ምድር እና ሰማይን የፈጠርክበት ጥበብህ ለማን ተገለጠ ማን ተረዳው እኛም ብንናገር ሊሰሙን ፈቃደኞች አይደሉም ” አለ ፡፡
ዛሬም ቢሆን እንዲሁ ነው የነበያት ጩኸት ሰሚ አጥቷል ፤ የውንጌላዊያን ድምጽ አልተደመጠም የሰባኪዎች ምስክርነታቸው ጆሮ አላገኘም ስለ ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሚነገረው የዛሬ 2000 አመት በፊት ጀምሮ የሚሰበከው ወንጌል በውስጡ ህይወት እያለበት ሰወችን ከሞት የሚታደግ ስልጣን ቢኖረውም ዛሬም ድረስ እየተገፋ ይኖራል
በምትኩ የሰው ልጅ ፡ እግዚአብሔር ለተጸየፈው እና ሓጢያት ነው ብሎ ለጠላው ለዘፈን እና ለዳንኪራ ለተለያየ ክፋት እንድሁም ለርክሰት ሲጋፋ እና አዳራሹን ሲሞላ ሲያጣብብ ፤ በየስፍራው የሰዎች ልጆች በጥፋት ወጥመድ ለመያዝ ሲቸኩሉ ህይወት መንገድ እና እውነት የሆነውን ክርስቶስ እየሱስን ሲገፉ ስለ መሲሁ ሲነገር ሳያደምጡ እና ጆሮ
ሳይሰጡ ዛረም ድረስ አሉ ፡፡
ምናለ ጌታ ሆይ ሰው ሁሉ አንተን አምኖ የዘላለምን ህይወት ቢወርስ ?
ምናለ ጌታ ሆይ በተለያየ እስራት ውስጥ ያለ ወደ አንተ መጥቶ ነጻነትን ፤ መፈታትን ቢያገኝ ?
ምናለ ጌታ ሆይ እንዲያው ይሔ ቃል ለሁሉ ሰው ቢበራለት ? “መዳን በሌላ በማንም የለም ልንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና ” ሓዋ 4፡-12
ምናለ ጌታ ሆይ ይህ የርህራሄ ቃልህ ለሁሉ ቢገለጥ ? “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጅ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ አለሙን እንዲሁ ወዷል እና ” ዮሓ 3፡-16

No comments:

Post a Comment