ዲቮሽን 289/07 አርብ፥ ሰኔ 19/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ለጠላት - ፊት አይስጡ!
የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ! ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት (ዳንኤል 3 : 17-18)
ወዳጄ ሆይ፥ የሚያመልኩትን ጌታ ማንነቱን ያውቃሉ? ግርማና ሞገሱን፥ ኃይልና ሥልጣኑን፥ ችሎታ ብቃቱን ጉልበትና ክንዱን ያውቃሉ? እንግዲያውስ ለጠላትዎ ዛቻ፥ ስድብ ማስፈራሪያ አይንቀጠቀጡ! አምላክዎን ካወቁ፥ ለጠላት ፊት አይስጡ!
በባቢሎን አውራጃ በፖለቲካ ሥልጣን ላይ ተሿሚዎች የነበሩ ሲድራቅ ሚሳቅና ሲብደናጎ አምላካቸውን የሚያውቁ፥ አይሁዳዊያን ናቸው፡፡ የመንግሥታቸውን አዋጅ፥ አዋጅ መተላለፍ የሚያመጣውን ቅጣት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ የንጉሡ ቁጣ፥ የባለሥልጣናቱ አድማ በሕይወታቸው ላይ የሚያስከፍላቸውን ዋጋ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን፥ ይህን ሁሉ እያወቁ፥ በነፍሳቸው ተወራርደው ለሐውልቱ ላይሰግዱ፥ ለባለሥልጣናቱ ለንጉሡም ላያጎበድዱ ውሳኔ አደረጉ!
ወገኖች ሆይ፥ ሲድራቅ ሚሳቅ አብደናጎ፥ ለንጉሡ ሐውልት ሰግደው በሕይወትና በምድራዊ ክብር ከመኖር ይልቅ፥ በሚነድደው እሳት መጣልን መረጡ፡፡ ለጣዖት በመስገድ ምድራዊ ሀብትና ሥልጣን ከሚያቆዩ፥ ለሚያመልኩት ጌታ መሰዋት መረጡ!
ወዳጄ ሆይ፥ የሚያመልኩትን ጌታ በእውነት ያውቁታል? ክብርና ሞገሱን፥ ኃይልና ሥልጣኑ ችሎታ ጉልበቱንስ ያውቃሉ? እንግዲያውስ ለጠላት ማስፈራሪያ ወድቀው አይስገዱ! ፈተና ቢነሳ፥ ማዕበል ቢበረታ ለወጀብ ለንውጥውጥታ ፊትዎትን አይስጡ!
ወገኖች ሆይ፥ ዳዊትን ያስቡ! በጎልያድ ፊት ሲቆም ለዛቻ ፉከራው አልተንቀጠቀጠም! ዳንኤልን ያስቡ! በአንበሶች ጉድጓድ ሲጣል የሚያመልከውን ያውቅ ነበርና አልተብረከረከም! ዮሴፍ ለጶጥፋር ሚስት አልተልፈሰፈሰም! ነህምያም ለሰንበላጥ ለጦቢያና ጌሳም የዛቻ፥ የንቀት፥ የመግደል ሙከራ አልተርበደበደም!
ወገኖች ሆይ፥ የሚያመልኩትን አምላክ ያውቃሉ? እንግዲያውስ፥ ለጠላት ፊት አይስጡ!
No comments:
Post a Comment