Wednesday, June 24, 2015

የሚጓጉለትን ሳያዩ - አይሙቱ!

ዲቮሽን 287/07 ረቡዕ ሰኔ 17/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

የሚጓጉለትን ሳያዩ - አይሙቱ!

(ስምዖን) በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር (ሉቃስ 2 : 26)
ወገኖች ሆይ፥ በሕይወታችን ሳናይ ላለመሞት የምንጓጓለት ነገር ምንድነው? በውስጥ ሰውነታችን የተረዳነው፥ በመንፈስ ቅዱስም ያረጋገጥነው፥ በትንቢት የተነገረን፥ ከቃሉ የሰማነው ነገር ምንድነው?

ወዳጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያረጋገጥልዎትን፥ በሕይወት ዘመንዎ በዓይን በብረትዎ እንደሚመለከቱ፥ መውጣትና መውረስ መውሰድ እንደሚችሉ የተናገረዎትን ሳያዩ ሳይመለከቱ፥ ሳይወስዱና ሳይወርሱ መሞት የሚባል ነገር አይመለከቱም! የተነገረዎትን ከመጠበቅ ይልቅ፥ በገዛ ፈቃድዎ ካላበላሹ በቀር፥ ከጥበቃው ማማ ካልወረዱ በቀር፥ ከሕይወት ሩጫው መስመር አቋርጦ ለመውጣት ካልወሰኑ በቀር፥ የተገባልዎትን ቃል ሳይመለከቱ ደግሞም ሳይወርሱ ሊሞቱ አይችሉም!

ወዳጄ ሆይ፥ ከስምዖን ይማሩ! ጻድቁ ስምዖን በጌታ የተቀባውን ሳያይ ሞትን ላለማየት አሻፈረኝ አለ፡፡ የተቀባውን ሳያይ የሞትን እንግዳ አልቀበል አለ፡፡ የተቀባውን ሳያይ ሞት በሩን ሲያንኳኳ እንዳልሰማ ሰምቶ አልከፍትለት አለ፡፡ እስኪያረጅ እስኪገረጅፍም ድረስ የሞትን ጥሪ "አልሰማም-አላይም-አልቀበልም!" አለ፡፡ በመጨረሻም የተመኘውን ጌታ በዓይኑ በብረቱ ሊመለከት ቻለ፡፡ የተቀባውን አቅፎ ሊስመውም ቻለ! ሃሌሉያ!

ወዳጄ ሆይ፥ የኔም ጸሎት ይኼ ነው! የተነገረኝን ተስፋ፥ የተገባልኝን ቃል፥ ሳላይ ሳላገኘው ሳልወርሰው አልሞትም! ሞት በመንገዴ በድንገት አግኝቶኝ እኔን ሊጨብጠኝ እጁን ቢዘረጋ፥ ጠልፎ እንዲጥለኝ ካልታሰበ ቦታ ወጥመድ ቢዘረጋ፥ ቃል ያለኝ ሰው ነኝና ሞትና መልዐኩ ሊያገኘኝ አይችልም! የምጓጓለትን ሳልወርሰው አልሞትም!

ወዳጄ ሆይ፥ ላረጋግጥልዎት፥ የሚጓጉለትን ሳይወርሱ እርስዎም አይሞቱም! እንደ ጻድቁ ስምዖን፥ የተስፋ ቃልዎትን ሙላት፥ የሕዝብዎትን መጽናናት ከተጠባበቁ፥ በጽድቅና ትጋት መቆየት ከበቁ፥ በመንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፍ ከቻሉ፥ የሚጓጉለትን ሳይወርሱ አይሞቱም!

No comments:

Post a Comment