ማክሰኞ፥ መስከረም 6/2007 ዓ.ም.
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
በዚያም የነበሩት ካህናት ሁሉ ተቀድሰው ነበር…መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው… እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፥ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው፡፡ የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሳ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም(2ዜና 5፡11-14)
ባለፈው ሐምሌ 2006 ዓም በሰዊዘርላንዷ ጄኔዋ የሚገኘውን የሴይንት ማቲው አንግሊካን ካቴድራል ከአንድ ሐበሻ ወዳጄ ጋር ጎብኝተን ነበር፡፡ በዕለቱ የጌታ እራት ይሰጥ ስልነበር የአምልኮ መሪዎቹ ከራሽያ ተጋብዘው የመጡ ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያኑ ውበት ማራኪ ነው፡፡ ገና ከበሩ እንደደረስን አንድ ወንድና አንዲት ሴት አስተናጋጆች ሞቅ ባለ ሰላምታ ተቀበሉንና መቀመጫ ቦታ ሰጡን፡፡ ለደንቡ ያህል ቦታ ሰጡን እንጂ ቤቱ ባዶ ነበር፡፡ እኛን ጨምሮ ባጠቃላይ በቤቱ ውስጥ 14 ነበርን፡፡ የራሽያ መዘምራን ዘማሬያቸውን ካቀረቡ በኋላ መጋቢው ተነስቶ ከሐዋርያት ስራ 16 ሙሉ ምዕራፉን አነበበና ሲጨርስ "This is the Word of God"(ይህ የእግዚአብሔር ቃል ነው) ብሎ ቁጭ አለ፡፡ ከዚያም መዘምራኑ እንደገና ሊዘምሩ ተነሱ፡፡ ዝማሬውም ሆነ የዕለቱ የቃል ንባብ በጽሁፍ አስቀድሞ የተመረጠ በመሆኑ መዘምራኑም ያንኑ መዘመር፥ ሰባኪውም ያንኑ ማቅረብ ስለነበር እስከ ፕሮግራሙ ማብቂያ ድረስ ታግሰን መቀመጥ አልቻልንም፡፡ ስለሆነም ጥለን ወጣን፡፡
ቤተክርስቲያን የልማድ አገልግሎቶች የሚሰጥባት ቦታ መሆን ስትጀምር አደጋ አለው፡፡ ጸሎቱ፥ ቃሉ፥ ዝማሬው…ልማድ ሲሆን አደጋ አለው! ቃሉ ልማድ ሲሆን ለ"ንባብ" ብቻ ሲውል ዝማሬው ደግሞ "ዜማ" ብቻ ይሆናል፡፡ ሰባኪው ሲያነብበው የነበረው ክፍል የሚናገረው የመንፈስ ቅዱስ ምሪት፥ ራዕይ፥ የወንጌል ስርጭት፥ የቤተክርስቲያን ተከላ፥ የሰዎች መዳን፥ አጋንንት ማውጣት፥ ድብደባ፥ እስራት፥ የእስር ቤቱ ዝማሬ፥ ድንገት የእግዚኣአብሔር ክብር መገለጥና የወህኒው መሰረት ተናውጦ ደጆች መከፈት፥ የሁሉም እስራት መፈታት፥ የእስረኞቹ ጠባቂና ቤተሰቡ ወደ ጌታ መምጣት …ሁሉ በቃ "ተረት ተረት" ብቻ ይሆናል!
ሰሎሞን በሰራው ቤተመቅደስ ካህናት ሌዋውያን መዘምራን ሁሉ ተቀድሰው ወደ እግዚአብሔርን ቤት በአንድነት ገብተው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ሲያመልኩ፥ የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው፥ ካህናቱም ከክብሩ ሙላት የተነሳ መቆምና ማገልገል አልቻሉም፡፡
የምናመልከው ይህን አምላክ ነው፡፡ ይህ አምላክ አልተለወጠም፥ አላረጀም፥ ጉልበቱም አልደከመም! ይህ አምላክ ዛሬም ሕያው ነው! በቅድስና ፊቱን ተግተን ብንፈልግው እናገኘዋለን፡፡ በጥንቱ ጊዜ፥ በነሙሴ ጊዜ፥ በነቢያት ዘመን፥ በሐዋርያት ዘመን ሲሰራ የነበረው የእግዚአብሔር ክንድ ዛሬም በእኛ ዘመን በእውነትና በመንፈስ እያመለክን በቅድስናና በጽድቅ ተግተን ብንፈልገው ሊንቀሳቀስ ይችላል፡፡
(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ላይክ ያድርጉ፥ ለወዳጅ ጓደኞችዎም ያስተላልፉ)
No comments:
Post a Comment