Friday, October 3, 2014

"ማማ" ላይ ስትወጣ ተጠንቀቅ!


ዲቮሽን .5/2007 ሰኞ፣ መስከረም 5/2007 ..
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

 

 (ማቴ 48-9) ደግሞ ዲያብሎስ (ኢየሱስን) እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፣ ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።

ሰይጣን ለሰው ልጆች ነጻ ስጦታ የለውም፡፡ ኖሮትም አያውቅም፡፡ ‹‹ስጦታ›› የሚመስል ነገር ካለም ቅድመ ሁኔታ አለው፡፡ ሰዎች ወድቀው ሲሰግዱለት ነው፡፡ ስግደቱን የሚፈልግበትም ዋና ዓላማ ሰዎችን ከእግዚአብሔር እጅ ለማጥፋት ነው፡፡

ለሰው ልጆች ነጻ ስጦታ ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እርሱ ለሚወዱትም ለሚጠሉትም፣ ለሚያውቁትም ለማያውቁትም፣ ለሚሰግዱለትም ሆነ ለማይሰግዱለት በነጻ ይሰጣል፡፡ የምንተነፍሰው አየር፣ የምንሞቀው ጸሐይ፣ የምንጠጣው ውሃ፣ ወቅቱን ጠብቆ የሚዘንበው ዝናብለሰው ልጆች ሁሉ ያለመድልዎ የተሰጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች በሰይጣን እጅ የሚገኙ ቢሆን ኖሮ፣ ወድቀን እንድንሰግድለት ግድ ባለን ነበር፡፡

ሰይጣን ይህም ባይሳካለትም እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም፡፡ ሥልጣንን፣ ሀብትን፣ ክብርን፣ እውቀትንና ሌሎችንም ነገሮች በማሳየት ሰዎችን ከእግዚአብሔር ቤት ሊያወጣቸው ይችላል፡፡ ለዚህም ነው አንዳንዶች ሥልጣን ሲይዙ፣ ሀብት ሲይዙ፣ እውቀት ሲይዙከእግዚአብሔር ቤት ሲጠፉ የሚታዩት፡፡ ሰው ከእግዚአብሔር ቤት ከወጣ መሀል ሰፋሪነት አይኖርምና፣ ቢገባውም ባይገባውም ሰይጣንን ያመልከዋል፡፡

ሁሉ የሞላለትን ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንኳ በነዚህ መንገዶች ከመፈተን ወደኋላ ያለለ ዲያብሎስ በብዙ የኑሮ ፈተናዎች የምንገኘውን እኛንስ ምንኛ የባሰ ይፈትነን ይሆን? ስለሆነም የሆነ ከፍታ ላይ ስንወጣ ልንጠነቀቅ ይገባል! የሥልጣን፣ የክብር፣ የእውቀት፣ የሀብትና የተዋቂነት ማማዎች ላይ ስንወጣ ወድቀን እንዳንሰግድለት እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

(ይህን ዕለታዊ ዲቮሽን ለወዳጅ ጓደኞችዎ ያስተላልፉ)

No comments:

Post a Comment