Wednesday, December 31, 2014

የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 4

  
ዲቮሽን .112/07     ረቡዕ ታህሳስ 22/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 4


ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)

አትጠገብ በጭንቀት ስሜት፣ የየውብዳር አምሳለን እጅ ጭምድድ አድርጋ ይዛ በደረቅ ፈገግታ፣ አስፈሪውን ጨዋታ የማመጥ ፍላጎቷን በግንባሯ አረጋገጠችላት፡፡ ዘርፉ ይህችን ፈገግታ እንዳገኘ ጨዋታውን ቀጠለ፡፡

<<ሐዋሪያ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 4፡10፣15 ለፊልጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍላቸው፣ <እንደገና እኔን ለመርዳት በማሰባችሁ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ጌታንም በጣም አመሰግነዋለሁ .... እንደምታስታውሱት ለወንጌል ሥራ ከመቄዶኒያ በተነሳሁ ጊዜ ከእናንተ በቀር በጉዞዬ የረዳኝ ሌላ ቤተክርስቲያን አልነበረም፡፡ እናንተ ለጉዞዬ የሚያስፈልገኝን ነገር በመስጠትም ሆነ በማስተናገድ ብዙ ረድታችሁኛል> ይላል፡፡>> 

<<አያችሁልኝ? የፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን ለአገልጋዮች አሳቢ ነች ማለት ነው፡፡ የመቀዶኒያ አማኞች አገልጋዮችን ተቀብለው በማስተናገድና በገንዘብ በመደገፍ የተመሰገኑ ናቸው! የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስለአገልጋዮች ማሰብ የምትጀምረውስ መቼ ነው? በአገልጋዮቹ በኩል ጌታ ብዙ ያደረገላቸው ምዕመናንስ ስለአገልጋዮች ማሰብ የሚጀምሩት መቼ ነው? ሕዝባችን በመስጠትና በመቀበል ስሌት አብሮን የሚቆመስ መቼ ነው? እኛ ስንራብና ስንጠማ፣ ስንጎድልና ስናጣ  ሕዝቡ ከጎናችን መቆም የሚጀምረው መቼ ነው!>>

<<ሐዋሪያ ጳውሎስ በኤፌሶን 6፡21 ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍላቸው፣ <እንዴት እንዳለሁ ኑሮዬን እንድታውቁ በጌታ የተወደደው ወንድማችንና ወንጌልን በማስተማር ታማኝ ረዳታችን የሆነው ቲኪቆስ ስለእኔ ሁኔታ በሰፊው ያጫውታችኋል> ይላል፡፡ ሐዋሪያው ራቅ ያለ ቦታ ላይ ላሉ ሰዎች ነው የኑሮውን ሁኔታ ሪፖርት የሚያደርግ አገልጋይ እየላከ ያለው፡፡>>

<<የኛ ደግሞ ይለያል! የኛ ሕይወት ምስክር ወይም ሪፖርተር አያሻውም፡፡ እንዴት እንዳለን ሰው ሁሉ ያውቀዋል! መጋደላችን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፣ ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር፣ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር መሆኑ ቀርቶ ከደምና ከሥጋ ጋር ሆኗል፡፡ ከአጋንንት፣ ከጨለማ ሠራዊት ጋር መታገል ሲገባን፣ ስንታገል የምንውለውና ስንታገል የምናድረው ከእህልና ውሃ፣ ከቤት ኪራይና ከመሳሰሉት ጋር መሆኑን ሰው ሁሉ እያወቀ ዝም ይለናል!  ወይ ነዶ!>>

<<ጌታችን ኢየሱስ በሉቃስ 10 ሰባውን ሁለት ሁለት አድርጎ ሲልክ፣ የደረሱበት ቤት ሁሉ እየበሉና እየጠጡ እንዲቀመጡ ነበር ያዘዛቸው፡፡ ምክንያቱም የወንጌል ሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና ነው! ባይቀበሏቸው ከከተማው የተጣበቀባቸውን ትቢያ እያራገፉ እንዲወጡ ነው የታዘዙት፡፡>>

<<ብዙዎቹ የሙሉጊዜ አገልጋዮች በመሪዎቻቸው ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድም ግርማ ሞገስ የላቸውም! በርካቶቹ አገልጋዮች ጊዜ ሰጥተው እያገለገሉ ምንም ደመወዝ አይከፈላቸውም፡፡ ይህ ሁሉ እንኳ ሆኖ ከሉቃስ 10 ትምህርት አይቀስሙም! ረሀብና ጥጋብ፣ በረዶና ዝናብ፣ ሐሩርና ውርጭ፣ መከራና ችግር እየተፈራረቀባቸው፣ አራግፈው አይወጡም!>>

ዘርፉ የቀኝ እጁን ቡጢ ጨብጦ፣ <<አዎ፣ የሐሩርና ውርጭ መፈራረቅ አልፈናል፣ መራብና መጥገብን ተምረናል፣ መብዛት መጉደሉን አውቀናል፡፡ ነገር ግን አንዲት ያላወቅናት ነገር፣ አንዳች ያልተረዳናት ትምህርት አለች፡፡ እርስዋም፣ ጌታ ያሳየንን ራዕይ ተከትሎ መውጣት፣ ወደሚልከን ሄዶ ማገልገል! ከተልዕኳችን ጋር የማይስማሙና አብረው የማይሄዱ አሠራሮችን ከራሳችን አራግፈን መጣል! በጸጋው ተደግፈን ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር፣ ወደ አዲስ ሥራ መግባት! በቃ ይኸው ነው መፍትሔው፡፡>>

ከዚያ ዝምታ ሰፈነ፡፡ ግን በሁሉም ሰው ፊት ቁጣና እልህ ይነበብበታል፡፡ ፍሬውም ከንፈሩን ነክሷል፡፡ የሆነ ነገር በእልህ ሲያስብ እንደዚህ ያደርገዋል፡፡ ለረዥም ደቂቃዎች ዝምታ ሆነ፡፡

የውብዳር አምሳለ ዝምታውን ሰብራ ገባች፡፡ በአገልጋይ ቤተሰቦች ላይ ሰፊ ጥናት አድርጋለች፡፡ የአገልጋዮቹ ሚስቶች ስለባሎቻቸው የሚናገሩትን ታውቃለች፡፡ የአገልጋዮቹ ልጆች ስለአባታቸውና ስለአገልግሎቱ የሚሰጡትን ብዙ ምስክርነቶች ሰብስባለች፡፡ የሰማችውንና ያየችውን ለመናገር ጉሮሮዋን ጠራረገችና ተመቻችታ ተቀመጠች፡፡

የውብዳር አምሳለ መናገር ጀመረች፡፡ <<በአንዳንድ ቦታዎች ሲታይ፣ የሙሉጊዜ አገልጋዮች ከቤተክርስቲያን አቅም በላይ መብዛታቸው ሁሉም ተያይዘው ችግር ውስጥ እንዲወድቁ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ጊዜያቸውን ሲሰጡ አቅሟን ሳታመዛዝን ዝም ብላ ከምትሰበስብ ጸጋ ያላቸውን አገልጋዮች በትክክል ፈትና ብትቀበል የተሻለ ነው፡፡ የተቀበለቻቸውን ደግሞ ልትንከባከባቸው ይገባል፡፡>>

<<ቤተክርስቲያን ጸጋቸውን ፈትና፣ አቅሟን አመዛዝና የተቀበለቻቸውን አገልጋዮች ልታንገላታና ልታሰቃይ አይገባም፡፡ ቤተክርስቲያን የአገልጋዮችን ደመወዝ ከቻለች በበቂ ሁኔታ ብትከፍል፣ የማትችል ከሆነ ደግሞ ድንኳን እየሰፉ እንዲያገለግሉ ብታበረታታ መልካም ነው፡፡ አገልጋዮች ስለኑሮና ስለቤተሰባቸው በማሰብ ጭንቀት ውስጥ ባይገቡ መልካም ነው፡፡ አብያተክርስቲያናት በየቦታው ሲያደርጉ የሚታየው ከአቅም በላይ የሆኑ ግዟዙፍ ሕንጻዎች የመገንባትና ሳውንድ ሲስተሞች የመሰብሰቡ ነገር ቢቆም ጥሩ ነው፡፡>> … (ምንጭ፣ የወንጌላዊው እጮኛ፣ ገጽ 76-78 የተቀነጨበ)

--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ትናንት፣ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ተመርቋል፡፡ መጽሐፉን ፒያሳ ከሚገኘው በእምነት መጻሕፍት መደብር ፒያሳ፣ በራዕይ መጻሕፍት መደብሮች፣ መካነየሱስ መጻሕፍት መደብር፣ የምሥራች ድምጽ መጻሕፍት መደብሮች፣ መሠረተክረስቶስ መዝሙር ቤት ስቴዲዮም ያገኛሉ፡፡

Tuesday, December 30, 2014

የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 3

ዲቮሽን .111/07     ማክሰኞ ታህሳስ 21/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 3


ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)

<<የአገልጋይ ሚስቶች ስለባሎቻቸው የሚሰጡት አስተያየትና ልጆቻቸው ስለአባቶቻቸው ሕይወት የሚሰጡት አስተያየት ደግሞ ሌላው የሚገርም ነው፡፡ ብዙዎቹ አገልጋይ ባሎች የአደባባይ እንጂ የቤት ሰዎች አይደሉም፡፡ ብዙ አገልጋዮች የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው <የፍቅር ረሃብተኞች ሆነናል፣ ጊዜ ይስጡን> ሲሉ ነው የሚደመጡት፡፡ የአንዳንድ አገልጋይ ሚስቶች ደግሞ ደፍረው <አገልጋይ ማግባት እንዲህ መሆኑን ባውቀው ኖሮ አላገባም ነበር፡፡ በጋብቻ ምርጫዬ ቀድሞ ትክክል የነበርኩ ይመስለኝ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ሳየው ግን መሳሳቴን በማወቄ አዝናለሁ> ሲሉ ይደመጣሉ፡፡>>

<<የአገልጋይ ሚስቶች ሲናገሩ ብዙዎቹ የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደማይጎበኟቸውና እንደማያገለግሏቸው ሲናገሩ፣ አንዳንዶች እንደውም ፈጽሞ እንደማያውቋቸውም ሁሉ ይናገራሉ፡፡ ባሎች የሚስቶቻቸውንና የልጆቻቸውን ፍቅር ማስታገስ ካልቻሉ በትዳራቸው ላይ ትልቅ አደጋ ይደቀናል፡፡ ትዳሩ እየተንገራገጨ ከመፍረስ ቢድን እንኳ ከትውልድ ፍሬ ቢስነት ግን አያመልጥም፡፡>>

<<አንዲት ሚስት ልጇ ታምሞባት፣ ባሏ ከአገልግሎት ቀርቶ የገዛ ልጁን እንዲያስታምመው ስትጠይቀው <ጥሪዬ ወንጌል መስበክ እንጂ ልጅ ማስታመም አይደለም> ብሎ እምቢ ብሏታል፡፡ ሌላው አገልጋይ ደግሞ ለጋብቻ የደረሱ ሴቶች ልጆቹ የጽዳት መጠበቂያ ወርሃዊ ወጪ አስቦ እንዲሰጣቸው አባታቸውን ሲጠይቁት፣ <ገንዘብ የለኝም> ብሎ በግልጽ እንደመናገር እንዴት እንደዘላበደባቸው እንደ አርቲስቶች ለሁለት እየተቀባበሉ በንዴት ሲናገሩ፡-

<<አባታችን <እኛ በእዚህ ምድር ላይ ስንኖር እንግዶችና ምጻተኞች ነን፣ ይለናል፡፡ መደላደልን መመኘት የለብንም፡፡ ያለፉ አባቶቻችን ታሪክ የተጻፈልን ለትምህርታችን ነው፡፡ ዓለም አልተገባቸውምና የዓለም ነገር ሳይመቻቸው አልፈዋል> ይለናል፡፡ ለራሱ ሳይማር ቀርቶ እኛን ችግር ላይ መጣሉ ሳያንስ፣ ብዙ ጊዜ እኛም የእርሱን መንገድ እንድንከተልለት በመፈለግ ከእኛ ጥያቄ ጋር ምንም የማይገናኝ ነገር እየነገረን ያመናፍስብናል፡፡>>

<<አይ አባቢ!>> ስለእምነታቸው መከራ የተቀበሉ አባቶችን ከመጽሐፍ ቅዱሱ ሲያነብብ፣ በእምነት ደግሞ መንግሥታትን ድል ስለነሡ አባቶች ደግሞ አያነብብም እንዴ? ሁሌ ስለመከራ ብቻ ከሚያወራልን፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ስላገኙ አባቶች ለምን አያወራልንም? የአንበሶችን አፍ ስለዘጉ አባቶች ለምን አይተርክልንም? የእሳትን ኃይል ስላጠፉት አባቶች፥ ከሰይፍ ስለት ስላመለጡ ጀግኖች፥ በጦርነት ኃይለኞች ስለሆኑት ለምን አይነግረንም? የባዕድ ጭፍሮችን ስላባረሩ አባቶችስ ለምን አይሰብከንም?>>

<<አባቢ የእምነት አባቶችን ታሪክ እየዘለለ፣ እስከ ሞት ስለተደበደቡት ብቻ፣ ስለተገረፉት ብቻ፣ በእስራትና በወኅኒ ስለተፈተኑት ብቻ፣ በድንጋይ ተወግረው ስለሞቱት ብቻ፣ በመጋዝ ስለተሰነጠቁት ብቻ፣ በሰይፍ ተገድለው ስለሞቱት ብቻ ይሰብከናል፡፡ አንዳንዴ ስናስበው የአባቢ እምነት የሆነ ቦታ ላይ ችግር ያለበት ይመስለናል፡፡ ስለዚህ መስተካከል አለበት፡፡>>

<<ጌታ ለአገልግሎት የጠራው እርሱን ከሆነ እኛን ለምን ያስርበናል?  እኛ ልጆች ነን፡፡ ምን ስላጠፋን ነው የምንራበው? የአባቢ አምላክ መከራ አሸካሚ ብቻ እንጂ ስለ ልጆቹ የማይጨነቅ ደንታ ቢስ ይመስለናል፡፡ ከአባቢ የተነሳ ጌታን ልንጠላው ደርሰናል፡፡>>

<<እኛ ትምህርታችንን ጨርሰን ሥራ ስንይዝ፣ እንኳን ከአባታችን ቤት፣ አባታችን የሚገባበት ቤተክርስቲያን እንኳን ድርሽ ማለት አንፈልግም፡፡ አባቢ በውበቷ ስንትና ስንት ባለጠጋ ወንዶች የሚፈልጓትን እናታችንን አጎሳቁሎብናል፡፡ ፊቷ ማድያት በማድያት ሆኖ የተበላሸው ለእርሷ ካለው የወረደ አመለካከት ነው፡፡ ትምህርታችንን ጨርሰን ሥራ ስንይዝ እናታችንን ከእርሱ እጅ ነጥቀን ከእኛ ጋ እንወስዳታለን፡፡ እየተንከባከብናት በደስታ እናኖራታለን፡፡ ከእርሱ ያጣችውን ፍቅር እኛ እንሰጣታለን፡፡>>

<<የቤተክርስቲያን ወንዶች አጠገባችን እንዲደርሱ አንፈልግም፡፡ እናታችንም የተሸወደችው አባታችን <እህት፣ እህት> እያለ ተጠግቷት፣ አሳምሮ ማውራት ብቻ በሚችለው ምላሱ በፍቅር አጥምዷት ነው፡፡ እንዲህ አይነት አደጋ እንዲያጋጥመን አንፈልግም፡፡ ትዳር መመሥረት አንፈልግም!>>

<<ሌላዋ የአገልጋይ ሚስት በትዳር 30 ዓመት ያህል ቆይታለች፡፡ የትምህርት ደረጃዋ 6ኛ ሲሆን ለባልዋ 8 ልጆች ወልዳለታለች፡፡ የአገልጋዩ የወር ገቢ 1400 ብር ነው፡፡ ነገር ግን በመልካም ጊዜ የወለዱት የመጀመሪያ ልጃቸው ጥሩ ሥራ ስለያዘ ጥሩ ይደጉማቸዋል፡፡ አገልጋዩ በመንፈሳዊ ሕይወቷ ስላሳደጋት ባሏን እንደ አባቷ ነው የምታየው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት አንዳቸው ለሌላቸው ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው፣ የሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ <ፍቅር አያረጅም> የሚል ቅጽል ስም ሰጥተዋቸዋል፡፡>>

<<ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ ሰውዬው ከቤተሰቡ ይልቅ አገልግሎት ያስቀድማል፡፡ በቤተክርስቲያን ሥራ ምክንያት ቤተሰቡን ጥሏል፡፡ የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን ሕይወት አይንከባከብም፡፡ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው፡፡ ልጆቹም ስለእርሱ ሲናገሩ፣ <ለኛ ጊዜ የለውም፣ ሁልጊዜ አምሽቶ ይገባል፡፡ ወደቤት ሲመጣ ደግሞ የሆነ ያልሆነ ሥራ እንድንሠራ ያዝዘናል፡፡ እኛ ደግሞ ስለሚደክመን አንግባባም፡፡ ከዚህም የተነሳ በእኛ ያዝናል፡፡ የማንታዘዝ ልጆች አድርጎ ይቆጥረናል> በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡>>

--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ትናንት፣ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 .. ከቀኑ 900 ተመርቋል፡፡


Monday, December 29, 2014

የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 1

ዲቮሽን .109/07     እሁድ ታህሳስ 19/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ!


ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)

<<በሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ክፍያ ዙሪያ የሚገርሙም፣ የሚያስቁም የሚያስለቅሱም ምስክርነቶችን ሰብስቤያለሁ፡፡ ከመሐል ኢትዮጵያከአዲስ አበባ፣ ከምዕራብ ኢትዮጵያጅማ፣ ከምሥራቅ ኢትዮጵያድረዳዋ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያባህርዳር፣ ከደቡብ ኢትዮጵያሐዋሳ በመምረጥ ሰፊ ጥናት አድርጌያለሁ፡፡>>

<<ባደረግሁት ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ከሚገኙ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች መካከል በሚያገኙት የገቢ መጠን ቤተሰባቸውንና ራሳቸውን በመልካም ሁኔታ መደጎም የሚችሉትን ፈልጎ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡>>

<<ለምሳሌ እንውሰድ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቤተሰብ ይዞ የሚኖር አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለወርሃዊ ቀለቡ ከአጥቢያው የሚከፈለው 800 ብር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ለአሥራትና ለሌሎች ወጭዎች ተቆራርጦ ከእጁ የሚገባው 700ብር አካባቢ ነው፡፡ ሚስቱ ሥራ የላትም፡፡ ከተጋቡ ስድስት አመት ቢሆናቸውም ልጅ አልወለዱም፡፡ አገልጋዩ እንዳጫወተኝ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ራሱን ከሰጠ አስር አመቱ ነው፡፡>>

<<ጊዜውን ከመስጠቱ በፊት የእንጨት ሥራ ድርጅት ነበረው፡፡ በሥሩም ስድስት ሠራተኞችን ቀጥሮ ያስተዳድር ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጠርቶት፣ ሥራውን እርግፍ አድርጎ ሲወጣ፣ በሙሉ እምነት ስለነበር የዛሬው አይነት ችግር ይገጥመኛል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ ጥሪ ሲደርሰው በወቅቱ በእጁ ደህና ገንዘብ ስለነበረው ስለገንዘብ የሚጨነቅ ልብም አልነበረውም፡፡>>

<<ሥራውን ጥሎ ወደ አገልግሎት ሲወጣ ለአገልግሎቱ ክብር ሲል ትዳር መያዝ እንዳለበት ይመከራል፡፡ የጋለ የአገልግሎት መንፈስ የነበረው ይኼው <<ፍሬሽ>> አገልጋይ የተነገረውን ምክር ባጭር ጊዜ ተግባራዊ በማድረግ በካዚናው የቋጠራትን ሳንቲም አራግፎ ሰርግ ደገሰበት፡፡ በሰርጉ ዕለት በርካታ አገልጋዮችንና በመቶ የሚቆጠሩ ወገኖችን በመጥራት ቡፌ ደርድሮ ጮማ አስቆረጠ፡፡>>

<<የኑሮን የችግር ቡፌ ለመጋፈጥ የተገደደው ግን ወዲያው ነበር፡፡ የወር ወጭዎቻቸውን ለመሸፈን ባለመቻላቸው የድርጅታቸውን ዕቃዎች እየሸጡ ለጥቂት ዓመታት ታገሉ፡፡ ዕቃዎቹ ካለቁ በኋላ ግን በተደራራቢ ችግሮች ውስጥ ለማለፍ ተገደዱ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ለብዙ ጊዜያት ስታጠናው ቆይታ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት በ600 ብር ደመወዝ ተቀበለችው፡፡ በዚህ ገቢ ለ2 አመት ሲያገለግል ቆይቶ ወደ 800 ብር አደገለት፡፡ በዚያም ብር እስከዛሬ እየኖረበት ነው፡፡>>

<<በአጥቢያው ውስጥ ስለደመወዝ ጭማሪ የሚያነሳ አገልጋይም ሆነ መሪ የለም፡፡ በዚህም ስቃያቸውን እያዩ ቆዩ፡፡ ልጅ ለመውለድ ደግሞ አቅማቸው ስላልፈቀደ ልጅ እንዳማራቸው ቀረ፡፡>>

<<በውድ ዋጋ ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት የሚበላ ነገር በማጣት ብዙ ጊዜ በምግብ እጦት ተፈትነዋል፡፡ እዚህ ላይ <ጻድቅ ሲራብ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም> ብለሽ ትጠቅሺልኝ ይሆናል፡፡ በርግጥ ለጥቅስ ለጥቅሱማ እኛን ማን አህሎን! ነገሩ ወዲያ ሆነ እንጂ፡፡>>

<<በፊት በፊት፣ አልፎ አልፎ <ጌታ ተናግሮናል> የሚሉ ወገኖች አገልጋዮችን የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን በዚያ መንገድ ጌታ የሚናገራቸው ቀንሰዋል፡፡ ስለተቸገሩ አገልጋዮች የሚያሳስባቸው ሰዎች እየከሰሙ ነው፡፡ አገልጋይ የተንሻፈፈ ጫማ አድርጎ ሲሄድ ምዕመኑ ይጠቋቆምበታል፡፡>>

<<የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችም ሆኑ አገልግሎታቸው ትኩረት እያጣ ነው፡፡ በፊት ብዙ ወገኖች በቤታቸው እንድንጎበኛቸውና እንድንከታተላቸው ይፈልጉ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ይህ አይነቱ ፍላጎት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ብዙዎቹ ሰዎች በሥራና በትምህርት እያሳበቡ አገልጋዮች ከቤታቸው እንዲመጡባቸው አይፈልጉም፡፡ በዚህም ረገድ የራሴንና የበርካታ አገልጋዮችን ምስክርነት ለማሰባሰብ ሞክሬያለሁ፡፡ በየጊዜው ከማነጋግራቸው አገልጋዮች ዘንድ የምሰማው ምስክርነት ልብ የሚሰብር ነው፡፡>> … (ምንጭ፣ የወንጌላዊው እጮኛ፣ ገጽ 39-40 የተቀነጨበ)

--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ዛሬ፣ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው በፒቲሲ እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡


የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 2

ዲቮሽን .110/07 ሰኞ፣ ታህሳስ 20/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 2

ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር።የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 410-15)

«አንድ ጊዜ አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለወራት ያህል ይታመምና ምንም አይነት የሕክምና ዕርዳታ ሳያገኝ አልጋ ላይ ይወድቃል፡፡ አገልጋዩ ቤተሰብና የቅርብ የሆነ ዘመዱ የማይኖርበት አካባቢ ይኖር ስለነበረ የጤንነት ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መጣ፡፡ በሚያገለግልበት አጥቢያ ውስጥ በወንጌል አገልግሎት ስራ ላይ የተሠማራ ከእርሱ ሌላ ረዳት ባለመኖሩ የቤተክርስቲያን መሪዎችን ያሳስብ ጀመር፡፡ ነገር ግን ስለወንጌላዊው ሕመምና ለወራት በአልጋ ላይ የመውደቁ ነገር ያሳሰበው፣ ቀርቦ የጠየቀውም ሆነ ዕርዳታ ያደረገለት አካል አልነበረም፡፡>>

<<አገልጋዩ ሕክምና ባለማግኘቱ ጤናው እየተቃወሰ ሄደ፡፡ በአጥቢያው ብቸኛ የነበረው አገልጋይ ለወራት ታምሞ አገልግሎት ሳይሰጥ የመቅረቱ ጉዳይ ያሳሰባቸው የቤተክርስቲያን መሪዎችን በቦታው ሌላ አገልጋይ አሰማሩ፡፡ መሪዎቹ ቀደም ሲል ለታማሚው አገልጋይ ይሰፍሩለት የነበረው ቀለብ በከፊል ተቀንሶ ይሰጠው ጀመር፡፡ ይህ ክፍያ ከቤት ኪራዩ ውጭ ለምንም የማይተርፍ ነበር፡፡>>

<<ለአገልጋዩ ቤት ያከራዩ የቤት ባለቤቶች <የዘመኑ በሽታ ሊሆን ይችላል> ብለው በመፍራት ቤታቸውን ለቅቆ እንዲወጣ ጠየቁት፡፡ ወንጌላዊውም ለጊዜው ሕመም ላይ ስላለ ቤት አፈላልጎ እስከሚወጣ ድረስ እንዲታገሱት ለመናቸው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ከቤተክርስቲያን አባላት የጠየቀው የለም፡፡>>

<<በመካከሉ አንድ ነገር ተፈጠረ፡፡ አገልጋዩ እንደ ወትሮው ቤት ሲከፍትና ሲዘጋ ለቀናት ያህል ያላዩት አከራዮቹ፣ የአገልጋዩን ቤት ቢያንኳኩ ከወደ ውስጥ <እነሆኝ> የሚል ድምጽ ይጠፋል፡፡ ጉዳዩ አብከንክኗቸው በሩን ጠጋ ብለው ሲመረምሩት መልካም ያልሆነ ጠረን  ይሸታቸው ይጀምራል፡፡>>

<<በሁኔታው የተደናገጡት የቤቱ አከራዮች ለፖሊስ ቢያመለክቱ ያላሰቡት አደጋ በቤታቸው ውስጥ ተከስቶ ያገኙታል፡፡ በተፋፈነና እጅግ በጣም በቆሸሸ ቤት ውስጥ ይኖር የነበረው አገልጋይ የምድር ሩጫውን አጠናቅቆ በሰላም ሲያገለግለው ወደነበረው አምላኩ ከሄደ ቀናት አልፈዋል፡፡>>

<<አዎ፣ እዚያ ረሀብ የለም፡፡ በሽታና ደዌ አይገኝበትም፡፡ በተፋፈነ ቤት መኖር የለም፡፡ የቤት ኪራይ አይከፈልበትም፡፡ በዚያ የሰው አይን ያላየው፣ ጆሮም ያልሰማው፣ እጅ ያልዳሰሰው፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ለምርጦቹ ያዘጋጀው... >>

--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ትናንት፣ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 .. ከቀኑ 900 ተመርቋል፡፡


Saturday, December 27, 2014

ሰብዓ ሰገል!

ዲቮሽን .108/07     ቅዳሜ ታህሳስ 18/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሰብዓ ሰገል!

ኢየሱስ በቤቴልሔም ከተማ ተወለደ፡፡ የክዋክብት ተመራማሪዎች የምሥራቅ አገር ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ በቅርቡ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የሚገኘው የት ነው? በምሥራቅ አገር ሆነን ኮከቡን ስላየን ልንሰግድለት መጥተናል (ማቴ 2፡1-2)።

ጠቢባኖቹ ከምሥራቅ አገር፣ ራቅ ካለ አካባቢ የመጡ ናቸው፡፡ ምናልባትም ከሜዶ-ፐርዥያ ግዛት አካባቢ የመጡ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ እነዚህ ጠቢባን ስለ መሲሁ መወለድ በሜዶንና ፋርስ  ግዛቶች ከተበታተኑ የእስራኤል ዲያስፖራዎች፣ በተለይም ከቤተመንግሥቱ ቁልፍ ባለሞያሞች ቁንጮ ከሆነው ከነቢዩ ዳንኤል (ዳን 9) ሳይሰሙ አልቀሩም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እዚህ ባዕዳን የኮከብ ተመራማሪዎች የነቢዩን ዳንኤል ትንቢት መርምረውና የአይሁዱን ንጉሥ የልደት ጊዜ አስልተው ሊሰግዱለት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፡፡

ታውቃላችሁ፣ እስራኤላዊያን ያልሆኑ ኮከብ ተመራማሪዎች አዲስ ለተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ሊሰግዱለት ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩ የሥነመለኮቱ ሊቆች፣ ፈሪሳዊያን፣ ሰዱቃዊያን፣ መምህራን፣ ካህናት፣ የሕዝብ አለቆችና ባለሥልጣናት የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ አላወቁም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ለድንግሊቱ ማርያም መልዐኩ ገብርዔል የነገራትን መልዕክት፣ የኤልሳቤጥ ጽንስ ለማርያም ጽንስ የዘለለበትን ሚስጥር፣ በእረኞቹ ዙሪያ መላዕክት ተገልጠው ያቀረቡትን መዝሙር፣ የኢየሩሳሌም የሐይማኖት መሪዎች መረጃ የላቸውም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ሐይማኖተኝነታችን ጌታን አያሳየንም፡፡ የኛ ሊቃውንትነት፣ የኛ ሕግ አዋቂነት፣ መጻሕፍት አዋቂነት፣ ሐይማኖተኝት፣ የሕዝብ መሪነት፣ መምህርት፣ ጌታን አያሳይም፡፡ እነዚህ ሁሉ በኢየሩሳሌም የነበሩ የሥነመለኮት ሰዎች መወለዱን ሳያውቁ፣ ከሩቅ አካባቢ የመጡ ኮከብ ተመራማሪዎች መወለዱን አወቁ፡፡

ታውቃላችሁ፣ ወግና ልማዳችን ጌታን አያሳየንም፡፡ የሐይማኖት ተቆርቋሪነታችን ጌታን አያሳየንም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ጌታን የምናየው በእውነተኛ ልብ ስንፈልገው ነው፡፡ ዋና ዓላማችን ራስን በማዋረድ ጌታን ማምለክ ሲሆን፣ ጌታን እናያለን፡፡ ከከፍታ ወርደን፣ ራሳችንን ክደን እርሱን ማመን ስንችል፣ ጌታን እናያለን፡፡ ሌላ ነገር ትተን፣ የተገለጠልንን ሕይወት፣ የበራልንን እውነት ተከትለን ስንሄድ ጌታን እናያለን፡፡


--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ነገ፣ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡

Friday, December 26, 2014

መናው ሲቀር!

ዲቮሽን .107/07     አርብ ታህሳስ 17/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


መናው ሲቀር!

በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ (ኢያ 5፡12)።

በዓለማዊው ሳይንስ ‹‹ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ ሦስቱ መሠረታዊ ነገሮች፣ ‹‹ምግብ መጠሊያና ልብስ›› ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሠረታዊያን መካከል መካከል እግዚአብሔር የለበትም፡፡

ታውቃላችሁ፣ አሕዛብ እግዚአብሔርን አያውቁትምና፣ እርሱን መሠረታዊ ፍላጎታቸውና ምርጫቸው አላደረጉትም፡፡ ይህም በመሆኑ፣ የእንጀራ ምንጫቸውን ከቀጣሪያቸውና፣ ከመሥሪያ ቤት አለቃቸው ያስተሳስሩታል፡፡ ይህም በመሆኑ፣ ዕለት ዕለት በስጋትና በፍርሃት፣ በጭንቀትና ውጥረት ይመላለሳሉ፡፡ እንጀራ ለማግኘት ክብራቸውን ጥለው፣ ለአሠሪዎቻቸው ባሪያ ይሆናሉ፡፡  

ወገኖች ሆይ፣ በእኛ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር የእስትንፋሳችን ምንጭ፣ የአካላችን ፈጣሪ፣ የሰውነታችን ሠሪ ነው፡፡ የእጀራችን ምንጩ ከላይም ሆነ ከታች፣ ከሰሜን ሆነ ከደቡብ፣ ከምሥራቅም ሆነ ከምዕራብ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ የፍጥረት መጋቢ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ እህል ውሃ አቅራቢ፣ የጠዋትና ማታ እንጀራ ጋጋሪ፣ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በሰው፣ በመሥሪያ ቤት፣ በቦታ የማይገደብ፣ በመዝራት በማጨድ በመውቃት የማይወሰን ሳያርሱ የሚያዘራ፣ ሳይዘሩ ሚያሳጭድ፣ ሳይታጨድ አውድማ፣ ሳይወቃ ጎተራ፣ ሙልት የሚያደርግ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ዝናብ በሌለበት ከምድረበዳ መሀል፣ መናን እንደጤዛ በጠዋት የሚያወርድ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እስራኤላዊያን በምድረበዳ ጉዞ መና እየወረደላቸው ይመገቡ ነበር፡፡ የተስፋዪቱን ምድር ፍሬ ሲበሉ፣ መናው መውረድ ተወ፡፡

ታውቃላችሁ፣ መናው ሲቆም፣ እንጀራው ይቀጥላል፡፡ ከአንዱ አቅጣጫ የምናገኘው እንጀራ ሲቋረጥ፣ የሌላ አቅጣጫው ይከተላል፡፡

ታውቃላችሁ፣ የእንጀራችን ምንጩ፣ ሥራ ቀጣሪያችን፣ የመሥሪያ ቤታችን፣ የሥራ አለቃችን፣ አይደለም፡፡ የእህል ውሃችን ምንጩ፣ ደመወዝ የሚሰጠን፣ ቀለብ የሚሰፍርልን፣ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ስለነፍሳችን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን፣ ምንስ አንለብሳለን ብለን አንጨነቅ! ምክንያቱም እህል ውሃችን ያለው በሰማዩ አምላካችን በእግዚአብሔር እጅ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ የሰማዩ መጋቢያችን ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ጥቂቱን አዝመራ በፍሬ ሊያበዛ፣ በትንሹ ነገር ጎተራ ሊሞላ፣ መናን ከላይ ሊያወርድ፣ ካልጠበቁት ቦታ፣ ካላሰቡት ስፍራ የማይመረመረውንና የማይታሰበውን ማድረግ ለእርሱ ይቻለዋል፡፡ እርሱ ጌታ ነውና፣ ለፍተን ከቀረነው፣ ተስፋ ከቆረጥነው ነገር፣ መረብ እስኪቀደድና ጀልባ እስኪሞላ መባረክ ይችላል!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡

ነፍስን መካድ!


ዲቮሽን .105/07     ረቡዕ ታህሳስ 15/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ነፍስን መካድ!

ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ (የሐዋ 20፡24)።

እውነተኛ አማኞች ከጌታ ከኢየሱስ ወንጌልን የመመስከር አገልግሎት ተቀብለዋል፡፡ ይህ አገልግሎት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ይሁዳ፣ ሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ መሮጥ ይጠይቃል፡፡ ይህን ሩጫ ለማድረግ ስንጥር ግን፣ መከራና ፈተና እንዲሁም እስራት ይጠብቀናል፡፡ የታላቁ ተልዕኮ ሩጫ፣ ራስን መካድን፣ ነፍስን በእኛ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር መቁጠርን ይጨምራል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ነፍሱን የሚወድድ ሰው ታላቁን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት ይቸግረዋል! የሚጠፉ ነፍሳትን ለማዳን የራስን ነፍስ መቁረስ አስፈላጊ ይሆናል! የራስን ነፍስ ስንቆርስ የሌሎች ነፍስ ይድናል፡፡ ሌሎች እንዲኖሩ መሞት ይጠይቃል፡፡ ሌሎች እንዲድኑ ራስን መስጠት የግድ ይላል፡፡ ራስን መስጠት ምርኮ ያበዛል፡፡
--------------------------------

‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡

Wednesday, December 24, 2014

ቅጥሩ እንዲወድቅ!

ዲቮሽን .104/07     ማክሰኞ ታህሳስ 14/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ቅጥሩ እንዲወድቅ!

የኢያሪኮ ቅጥር ሰባት ቀን ከዞሩበት በኋላ በእምነት ወደቀ። (ዕብ 11፡30)።


ኢያሪኮ በተስፋይቱ ምድር በከነአን መግቢያ በር ላይ የነበረች ስትራቴጂክ ምድር ነች፡፡ ምድሪቱ የዮርዳኖስን ወንዝ እንደ ብሔራዊ የደህንነት ድንበር ማድረጓ ሳያንስ፣ ከተማዋ ፈጽማ መታጠረችና የተዘጋች መሆኗ ደግሞ የተስፋዪቱን ምድር የመውረዱን ሒደት የባሰ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፣ የተስፋዪቱ ምድር ወይንም የከነአን ነገሥታት እና ጽኑአን ኃያላን የጦር ኃይሎቿ፣ በምድረበዳ ሲንገላታ የቆየውን ሕዝብ እጅግ የሚያስደነግጥ ገጽታ ነበረው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋዪቱ ምድር ወደ ከነአን እያደረጉ ባለው መንገድ ላይ የታጋረጠው ዮርዳኖስ ደረቀ፡፡ ዜናውን ሲሰሙ ታሪክ ተገልብጦ፣ መላው ከነአናዊያን፣ ነገሥታቶቻቸውና ጽኑአን ኃያላኖቻቸው ልባቸው ቀለጠ፣ ነፍስም አልቀረላቸውም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ሰው ነፍሱ ሲቀልጥ ብርታትና አቅሙ አብሮት ይቀልጣል፡፡ ልቡ የፈሰሰ ሰው የፈለገው የጦር መሳሪያ ቢኖረውም ራሱን ለመከላከል አቅም አይኖረውም፡፡ ልቡ የቀለጠ ሕዝብ የመዋጋት አቅም ሊኖረው አይችልም፡፡ ሰው ነፍሱ ከፈሰሰ በቃ ሬሳ ነው፡፡ በሕይወት ያለም ቢመስል ያው በቁሙ የሞተ አስከሬን ነው፡፡

ታውቃላችሁ፣ ከነአናዊያን ከእስራኤልን ልጆች የተነሣ ልባቸው ቀለጠ፣ ነፍስም አልቀረላቸውም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ጠላትን የሚያሸብረው የእኛ ጦር ዕቃ ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እኛ ሲዋጋ፣ ጠላት ኃይሉ ይቀልጣል፡፡ እግዚአብሔር ስለእኛ ሲዋጋ፣ በአጠገባችን ሺህ፣ በቀኛችን አስር ሺህ ይወድቃል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ከኢያሪኮ በፊት፣ እስራኤላዊያን ወንድ ሁሉ ግርዛት ፈጸሙ፡፡ በምድረበዳው ጉዞ ይዘው የቆዩትን ነውራቸውን ጣሉ፡፡ በዓል አደረጉ፡፡ ቃልኪዳን አደሱ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እስራኤላዊያን ወደ ኢያሪኮ ቅጥር ሲመጡ፣ በእምነት እንዲዞሩ ተነገራቸው፡፡ ስድስት ጊዜ ዞሩ፡፡ በሰባተኛው ቀን፣ ዙሩ ከርሮና መርሮ ሰባት እጥፍ ሆነ፡፡ ቢሆንም፣ የኢያሪኮ ቅጥር በእምነት፣ በእግዚአብሔር ክንድ ወደቀ፡፡

ታውቃችሁ፣ ቅጥራችን ሊወድቅ ሲደርስ፣ የእምነት ዙሩ ይከርራል፣ ይመራራል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ዙሩ ሲከርርና ሲመርር ሪከርድ ይሰበራል፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ ቅጥሩ እንዲወድቅ፣ ተስፋ ቃልዎትን ይዘው የእምነት ዙር ይዙሩ፡፡ በመንገድዎ ያለ ግድግዳ እንዲፈርስ፣ ተራራው ኮረብታው እንዲደረመስ፣ ተግዳሮት መከራው እንዲጠረመስ፣ የእምነት ዙርዎን አክርረው ይዙሩ፡፡ ተስፋ ቃሉን ይዘው፣ የእምነት ዙሩን አክርረው ከዞሩ፣ ሪከርድ ይሰብራሉ!

--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡