ዲቮሽን
ቁ.112/07 ረቡዕ፣ ታህሳስ 22/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 4
ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ
ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ
ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች
እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)
አትጠገብ በጭንቀት ስሜት፣ የየውብዳር አምሳለን
እጅ ጭምድድ አድርጋ ይዛ በደረቅ ፈገግታ፣ አስፈሪውን ጨዋታ የማዳመጥ ፍላጎቷን በግንባሯ አረጋገጠችላት፡፡ ዘርፉ
ይህችን ፈገግታ እንዳገኘ ጨዋታውን ቀጠለ፡፡
<<ሐዋሪያ ጳውሎስ
በፊልጵስዩስ 4፡10፣15 ለፊልጵስዩስ ሰዎች ሲጽፍላቸው፣ <እንደገና እኔን ለመርዳት በማሰባችሁ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ጌታንም በጣም አመሰግነዋለሁ .... እንደምታስታውሱት ለወንጌል ሥራ ከመቄዶኒያ በተነሳሁ ጊዜ ከእናንተ በቀር በጉዞዬ የረዳኝ ሌላ
ቤተክርስቲያን አልነበረም፡፡ እናንተ ለጉዞዬ የሚያስፈልገኝን ነገር በመስጠትም ሆነ በማስተናገድ ብዙ ረድታችሁኛል> ይላል፡፡>>
<<አያችሁልኝ? የፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን ለአገልጋዮች አሳቢ ነች ማለት ነው፡፡ የመቀዶኒያ
አማኞች አገልጋዮችን ተቀብለው በማስተናገድና በገንዘብ በመደገፍ የተመሰገኑ ናቸው! የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስለአገልጋዮች ማሰብ የምትጀምረውስ መቼ ነው? በአገልጋዮቹ በኩል ጌታ ብዙ ያደረገላቸው
ምዕመናንስ ስለአገልጋዮች ማሰብ የሚጀምሩት መቼ ነው? ሕዝባችን በመስጠትና በመቀበል ስሌት አብሮን የሚቆመውስ መቼ ነው? እኛ ስንራብና ስንጠማ፣ ስንጎድልና ስናጣ ሕዝቡ ከጎናችን መቆም የሚጀምረው መቼ ነው!>>
<<ሐዋሪያ ጳውሎስ
በኤፌሶን 6፡21 ለኤፌሶን ሰዎች ሲጽፍላቸው፣ <እንዴት እንዳለሁ ኑሮዬን እንድታውቁ በጌታ የተወደደው
ወንድማችንና ወንጌልን በማስተማር ታማኝ ረዳታችን የሆነው ቲኪቆስ ስለእኔ ሁኔታ በሰፊው ያጫውታችኋል> ይላል፡፡ ሐዋሪያው ራቅ ያለ ቦታ ላይ ላሉ ሰዎች ነው የኑሮውን ሁኔታ ሪፖርት የሚያደርግ አገልጋይ
እየላከ ያለው፡፡>>
<<የኛ ደግሞ ይለያል! የኛ ሕይወት ምስክር ወይም ሪፖርተር አያሻውም፡፡ እንዴት እንዳለን ሰው ሁሉ
ያውቀዋል! መጋደላችን ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር፣ ከዚህም ከጨለማ
ዓለም ገዦች ጋር፣ በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር መሆኑ ቀርቶ ከደምና ከሥጋ ጋር ሆኗል፡፡ ከአጋንንት፣
ከጨለማ ሠራዊት ጋር መታገል ሲገባን፣ ስንታገል የምንውለውና ስንታገል የምናድረው ከእህልና ውሃ፣ ከቤት ኪራይና ከመሳሰሉት ጋር
መሆኑን ሰው ሁሉ እያወቀ ዝም ይለናል! ወይ ነዶ!>>
<<ጌታችን ኢየሱስ
በሉቃስ 10 ሰባውን ሁለት ሁለት አድርጎ ሲልክ፣ የደረሱበት ቤት ሁሉ እየበሉና እየጠጡ እንዲቀመጡ ነበር ያዘዛቸው፡፡ ምክንያቱም
የወንጌል ሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና ነው! ባይቀበሏቸው ከከተማው የተጣበቀባቸውን ትቢያ እያራገፉ እንዲወጡ ነው የታዘዙት፡፡>>
<<ብዙዎቹ የሙሉጊዜ
አገልጋዮች በመሪዎቻቸው ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድም ግርማ ሞገስ የላቸውም! በርካቶቹ አገልጋዮች ጊዜ ሰጥተው እያገለገሉ ምንም ደመወዝ አይከፈላቸውም፡፡
ይህ ሁሉ እንኳ ሆኖ ከሉቃስ 10 ትምህርት አይቀስሙም! ረሀብና ጥጋብ፣
በረዶና ዝናብ፣ ሐሩርና ውርጭ፣ መከራና ችግር እየተፈራረቀባቸው፣ አራግፈው አይወጡም!>>
ዘርፉ የቀኝ እጁን ቡጢ ጨብጦ፣ <<አዎ፣ የሐሩርና ውርጭ መፈራረቅ አልፈናል፣ መራብና መጥገብን ተምረናል፣ መብዛት መጉደሉን አውቀናል፡፡
ነገር ግን አንዲት ያላወቅናት ነገር፣ አንዳች ያልተረዳናት ትምህርት አለች፡፡ እርስዋም፣ ጌታ ያሳየንን ራዕይ ተከትሎ መውጣት፣
ወደሚልከን ሄዶ ማገልገል! ከተልዕኳችን ጋር የማይስማሙና አብረው የማይሄዱ አሠራሮችን ከራሳችን አራግፈን መጣል! በጸጋው ተደግፈን ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር፣ ወደ አዲስ ሥራ መግባት!
በቃ ይኸው ነው መፍትሔው፡፡>>
ከዚያ ዝምታ ሰፈነ፡፡ ግን በሁሉም ሰው ፊት ቁጣና
እልህ ይነበብበታል፡፡ ፍሬውም ከንፈሩን ነክሷል፡፡ የሆነ ነገር በእልህ ሲያስብ እንደዚህ ያደርገዋል፡፡ ለረዥም ደቂቃዎች ዝምታ
ሆነ፡፡
የውብዳር አምሳለ ዝምታውን ሰብራ ገባች፡፡ በአገልጋይ
ቤተሰቦች ላይ ሰፊ ጥናት አድርጋለች፡፡ የአገልጋዮቹ ሚስቶች ስለባሎቻቸው የሚናገሩትን ታውቃለች፡፡ የአገልጋዮቹ ልጆች ስለአባታቸውና
ስለአገልግሎቱ የሚሰጡትን ብዙ ምስክርነቶች ሰብስባለች፡፡ የሰማችውንና ያየችውን ለመናገር ጉሮሮዋን ጠራረገችና ተመቻችታ ተቀመጠች፡፡
የውብዳር አምሳለ መናገር ጀመረች፡፡ <<በአንዳንድ ቦታዎች ሲታይ፣ የሙሉጊዜ አገልጋዮች ከቤተክርስቲያን አቅም በላይ መብዛታቸው ሁሉም
ተያይዘው ችግር ውስጥ እንዲወድቁ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ጊዜያቸውን ሲሰጡ አቅሟን ሳታመዛዝን ዝም ብላ ከምትሰበስብ
ጸጋ ያላቸውን አገልጋዮች በትክክል ፈትና ብትቀበል የተሻለ ነው፡፡ የተቀበለቻቸውን ደግሞ ልትንከባከባቸው ይገባል፡፡>>
<<ቤተክርስቲያን
ጸጋቸውን ፈትና፣ አቅሟን አመዛዝና የተቀበለቻቸውን አገልጋዮች ልታንገላታና ልታሰቃይ አይገባም፡፡ ቤተክርስቲያን የአገልጋዮችን ደመወዝ
ከቻለች በበቂ ሁኔታ ብትከፍል፣ የማትችል ከሆነ ደግሞ ድንኳን እየሰፉ እንዲያገለግሉ ብታበረታታ መልካም ነው፡፡ አገልጋዮች ስለኑሮና
ስለቤተሰባቸው በማሰብ ጭንቀት ውስጥ ባይገቡ መልካም ነው፡፡ አብያተክርስቲያናት በየቦታው ሲያደርጉ የሚታየው ከአቅም በላይ የሆኑ
ግዟዙፍ ሕንጻዎች የመገንባትና ሳውንድ ሲስተሞች የመሰብሰቡ ነገር ቢቆም ጥሩ ነው፡፡>> … (ምንጭ፣ የወንጌላዊው እጮኛ፣ ገጽ 76-78 የተቀነጨበ)
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ትናንት፣ እሁድ፣
ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ተመርቋል፡፡ መጽሐፉን ፒያሳ ከሚገኘው በእምነት መጻሕፍት መደብር ፒያሳ፣
በራዕይ መጻሕፍት መደብሮች፣ መካነየሱስ መጻሕፍት መደብር፣ የምሥራች ድምጽ መጻሕፍት መደብሮች፣ መሠረተክረስቶስ መዝሙር ቤት
ስቴዲዮም ያገኛሉ፡፡
No comments:
Post a Comment