ዲቮሽን
ቁ.111/07 ማክሰኞ፣ ታህሳስ 21/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ!
3
ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ
ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ
ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች
እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)
<<የአገልጋይ ሚስቶች
ስለባሎቻቸው የሚሰጡት አስተያየትና ልጆቻቸው ስለአባቶቻቸው ሕይወት የሚሰጡት አስተያየት ደግሞ ሌላው የሚገርም ነው፡፡ ብዙዎቹ አገልጋይ
ባሎች የአደባባይ እንጂ የቤት ሰዎች አይደሉም፡፡ ብዙ አገልጋዮች የውጭ አልጋ የቤት ቀጋ ናቸው፡፡ ስለሆነም ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው
<የፍቅር ረሃብተኞች ሆነናል፣ ጊዜ ይስጡን> ሲሉ ነው የሚደመጡት፡፡ የአንዳንድ አገልጋይ ሚስቶች ደግሞ ደፍረው <አገልጋይ ማግባት እንዲህ መሆኑን ባውቀው ኖሮ አላገባም ነበር፡፡ በጋብቻ ምርጫዬ ቀድሞ ትክክል
የነበርኩ ይመስለኝ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ሳየው ግን መሳሳቴን በማወቄ አዝናለሁ> ሲሉ ይደመጣሉ፡፡>>
<<የአገልጋይ ሚስቶች
ሲናገሩ ብዙዎቹ የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደማይጎበኟቸውና እንደማያገለግሏቸው ሲናገሩ፣ አንዳንዶች እንደውም ፈጽሞ እንደማያውቋቸውም
ሁሉ ይናገራሉ፡፡ ባሎች የሚስቶቻቸውንና የልጆቻቸውን ፍቅር ማስታገስ ካልቻሉ በትዳራቸው ላይ ትልቅ አደጋ ይደቀናል፡፡ ትዳሩ እየተንገራገጨ
ከመፍረስ ቢድን እንኳ ከትውልድ ፍሬ ቢስነት ግን አያመልጥም፡፡>>
<<አንዲት ሚስት
ልጇ ታምሞባት፣ ባሏ ከአገልግሎት ቀርቶ የገዛ ልጁን እንዲያስታምመው ስትጠይቀው <ጥሪዬ ወንጌል መስበክ እንጂ ልጅ ማስታመም አይደለም> ብሎ እምቢ ብሏታል፡፡ ሌላው አገልጋይ ደግሞ ለጋብቻ የደረሱ ሴቶች ልጆቹ የጽዳት መጠበቂያ
ወርሃዊ ወጪ አስቦ እንዲሰጣቸው አባታቸውን ሲጠይቁት፣ <ገንዘብ የለኝም> ብሎ በግልጽ እንደመናገር እንዴት እንደዘላበደባቸው እንደ አርቲስቶች ለሁለት እየተቀባበሉ በንዴት
ሲናገሩ፡-
<<አባታችን <እኛ በእዚህ ምድር ላይ ስንኖር እንግዶችና ምጻተኞች ነን፣ ይለናል፡፡ መደላደልን መመኘት የለብንም፡፡
ያለፉ አባቶቻችን ታሪክ የተጻፈልን ለትምህርታችን ነው፡፡ ዓለም አልተገባቸውምና የዓለም ነገር ሳይመቻቸው አልፈዋል> ይለናል፡፡ ለራሱ ሳይማር ቀርቶ እኛን ችግር ላይ መጣሉ ሳያንስ፣ ብዙ ጊዜ እኛም የእርሱን መንገድ
እንድንከተልለት በመፈለግ ከእኛ ጥያቄ ጋር ምንም የማይገናኝ ነገር እየነገረን ያመናፍስብናል፡፡>>
<<አይ አባቢ!>> ስለእምነታቸው መከራ የተቀበሉ
አባቶችን ከመጽሐፍ ቅዱሱ ሲያነብብ፣ በእምነት ደግሞ መንግሥታትን ድል ስለነሡ አባቶች ደግሞ አያነብብም እንዴ? ሁሌ ስለመከራ ብቻ ከሚያወራልን፣ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ስላገኙ አባቶች
ለምን አያወራልንም? የአንበሶችን አፍ ስለዘጉ አባቶች ለምን አይተርክልንም? የእሳትን ኃይል ስላጠፉት አባቶች፥ ከሰይፍ ስለት ስላመለጡ ጀግኖች፥ በጦርነት ኃይለኞች ስለሆኑት ለምን አይነግረንም? የባዕድ ጭፍሮችን ስላባረሩ አባቶችስ ለምን አይሰብከንም?>>
<<አባቢ የእምነት
አባቶችን ታሪክ እየዘለለ፣ እስከ ሞት ስለተደበደቡት ብቻ፣ ስለተገረፉት ብቻ፣ በእስራትና በወኅኒ ስለተፈተኑት ብቻ፣ በድንጋይ ተወግረው
ስለሞቱት ብቻ፣ በመጋዝ ስለተሰነጠቁት ብቻ፣ በሰይፍ ተገድለው ስለሞቱት ብቻ ይሰብከናል፡፡ አንዳንዴ ስናስበው የአባቢ እምነት የሆነ
ቦታ ላይ ችግር ያለበት ይመስለናል፡፡ ስለዚህ መስተካከል አለበት፡፡>>
<<ጌታ ለአገልግሎት
የጠራው እርሱን ከሆነ እኛን ለምን ያስርበናል? እኛ ልጆች ነን፡፡ ምን ስላጠፋን
ነው የምንራበው? የአባቢ አምላክ መከራ አሸካሚ ብቻ እንጂ ስለ ልጆቹ የማይጨነቅ ደንታ ቢስ ይመስለናል፡፡ ከአባቢ
የተነሳ ጌታን ልንጠላው ደርሰናል፡፡>>
<<እኛ ትምህርታችንን
ጨርሰን ሥራ ስንይዝ፣ እንኳን ከአባታችን ቤት፣ አባታችን የሚገባበት ቤተክርስቲያን እንኳን ድርሽ ማለት አንፈልግም፡፡ አባቢ በውበቷ
ስንትና ስንት ባለጠጋ ወንዶች የሚፈልጓትን እናታችንን አጎሳቁሎብናል፡፡ ፊቷ ማድያት በማድያት ሆኖ የተበላሸው ለእርሷ ካለው የወረደ
አመለካከት ነው፡፡ ትምህርታችንን ጨርሰን ሥራ ስንይዝ እናታችንን ከእርሱ እጅ ነጥቀን ከእኛ ጋ እንወስዳታለን፡፡ እየተንከባከብናት
በደስታ እናኖራታለን፡፡ ከእርሱ ያጣችውን ፍቅር እኛ እንሰጣታለን፡፡>>
<<የቤተክርስቲያን
ወንዶች አጠገባችን እንዲደርሱ አንፈልግም፡፡ እናታችንም የተሸወደችው አባታችን <እህት፣ እህት> እያለ ተጠግቷት፣ አሳምሮ ማውራት ብቻ በሚችለው
ምላሱ በፍቅር አጥምዷት ነው፡፡ እንዲህ አይነት አደጋ እንዲያጋጥመን አንፈልግም፡፡ ትዳር መመሥረት አንፈልግም!>>
<<ሌላዋ የአገልጋይ
ሚስት በትዳር 30 ዓመት ያህል ቆይታለች፡፡ የትምህርት ደረጃዋ 6ኛ ሲሆን ለባልዋ 8 ልጆች ወልዳለታለች፡፡ የአገልጋዩ የወር ገቢ
1400 ብር ነው፡፡ ነገር ግን በመልካም ጊዜ የወለዱት የመጀመሪያ ልጃቸው ጥሩ ሥራ ስለያዘ ጥሩ ይደጉማቸዋል፡፡ አገልጋዩ በመንፈሳዊ
ሕይወቷ ስላሳደጋት ባሏን እንደ አባቷ ነው የምታየው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት አንዳቸው ለሌላቸው ጥልቅ ፍቅር ስለነበራቸው፣ የሚያውቋቸው
ሰዎች ሁሉ <ፍቅር አያረጅም> የሚል ቅጽል ስም ሰጥተዋቸዋል፡፡>>
<<ከቅርብ ጊዜ
ወዲህ ግን፣ ሰውዬው ከቤተሰቡ ይልቅ አገልግሎት ያስቀድማል፡፡ በቤተክርስቲያን ሥራ ምክንያት ቤተሰቡን ጥሏል፡፡ የራሱንም ሆነ የቤተሰቡን
ሕይወት አይንከባከብም፡፡ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት ነው፡፡ ልጆቹም ስለእርሱ ሲናገሩ፣ <ለኛ ጊዜ የለውም፣ ሁልጊዜ አምሽቶ ይገባል፡፡ ወደቤት ሲመጣ ደግሞ የሆነ ያልሆነ ሥራ እንድንሠራ
ያዝዘናል፡፡ እኛ ደግሞ ስለሚደክመን አንግባባም፡፡ ከዚህም የተነሳ በእኛ ያዝናል፡፡ የማንታዘዝ ልጆች አድርጎ ይቆጥረናል> በማለት ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡>>
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ››
በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ትናንት፣ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ተመርቋል፡፡
No comments:
Post a Comment