ዲቮሽን
ቁ.107/07 አርብ፣ ታህሳስ 17/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
መናው
ሲቀር!
በነጋውም ከምድሪቱ ፍሬ ከበሉ በኋላ መናው ቀረ፤ ከዚያም በኋላ
ለእስራኤል ልጆች መና አልመጣላቸውም፤ ነገር ግን በዚያው ዓመት የከነዓንን ምድር ፍሬ በሉ (ኢያ 5፡12)።
በዓለማዊው ሳይንስ ‹‹ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ ሦስቱ መሠረታዊ
ነገሮች፣ ‹‹ምግብ መጠሊያና ልብስ›› ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሠረታዊያን መካከል መካከል እግዚአብሔር የለበትም፡፡
ታውቃላችሁ፣ አሕዛብ እግዚአብሔርን አያውቁትምና፣ እርሱን መሠረታዊ
ፍላጎታቸውና ምርጫቸው አላደረጉትም፡፡ ይህም በመሆኑ፣ የእንጀራ ምንጫቸውን ከቀጣሪያቸውና፣ ከመሥሪያ ቤት አለቃቸው ያስተሳስሩታል፡፡
ይህም በመሆኑ፣ ዕለት ዕለት በስጋትና በፍርሃት፣ በጭንቀትና ውጥረት ይመላለሳሉ፡፡ እንጀራ ለማግኘት ክብራቸውን ጥለው፣ ለአሠሪዎቻቸው
ባሪያ ይሆናሉ፡፡
ወገኖች ሆይ፣ በእኛ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ጌታ እግዚአብሔር
የእስትንፋሳችን ምንጭ፣ የአካላችን ፈጣሪ፣ የሰውነታችን ሠሪ ነው፡፡ የእጀራችን ምንጩ
ከላይም ሆነ ከታች፣ ከሰሜን ሆነ ከደቡብ፣ ከምሥራቅም ሆነ ከምዕራብ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ታውቃላችሁ፣ የፍጥረት መጋቢ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ እህል ውሃ አቅራቢ፣ የጠዋትና ማታ
እንጀራ ጋጋሪ፣ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በሰው፣ በመሥሪያ ቤት፣ በቦታ የማይገደብ፣ በመዝራት በማጨድ በመውቃት የማይወሰን ሳያርሱ
የሚያዘራ፣ ሳይዘሩ ሚያሳጭድ፣ ሳይታጨድ አውድማ፣ ሳይወቃ ጎተራ፣ ሙልት የሚያደርግ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ዝናብ በሌለበት ከምድረበዳ መሀል፣ መናን እንደጤዛ በጠዋት የሚያወርድ እግዚአብሔር
ብቻ ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ እስራኤላዊያን በምድረበዳ ጉዞ መና እየወረደላቸው
ይመገቡ ነበር፡፡ የተስፋዪቱን ምድር ፍሬ ሲበሉ፣ መናው መውረድ ተወ፡፡
ታውቃላችሁ፣ መናው ሲቆም፣ እንጀራው ይቀጥላል፡፡ ከአንዱ አቅጣጫ የምናገኘው እንጀራ
ሲቋረጥ፣ የሌላ አቅጣጫው ይከተላል፡፡
ታውቃላችሁ፣ የእንጀራችን ምንጩ፣ ሥራ ቀጣሪያችን፣ የመሥሪያ ቤታችን፣ የሥራ አለቃችን፣
አይደለም፡፡ የእህል ውሃችን ምንጩ፣ ደመወዝ የሚሰጠን፣ ቀለብ የሚሰፍርልን፣ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ስለነፍሳችን እንበላለን፣
ምንስ እንጠጣለን፣ ምንስ አንለብሳለን ብለን አንጨነቅ! ምክንያቱም እህል ውሃችን ያለው በሰማዩ አምላካችን በእግዚአብሔር እጅ ነው!
ወገኖች ሆይ፣ የሰማዩ መጋቢያችን ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ጥቂቱን አዝመራ በፍሬ ሊያበዛ፣ በትንሹ ነገር
ጎተራ ሊሞላ፣ መናን ከላይ ሊያወርድ፣ ካልጠበቁት ቦታ፣ ካላሰቡት ስፍራ የማይመረመረውንና የማይታሰበውን ማድረግ ለእርሱ ይቻለዋል፡፡
እርሱ ጌታ ነውና፣ ለፍተን ከቀረነው፣ ተስፋ ከቆረጥነው ነገር፣ መረብ እስኪቀደድና ጀልባ እስኪሞላ መባረክ ይችላል!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ
እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡
ካዛንቺስ ኡራኤል መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን ዋና ጽ/ቤት እንዲገኙልኝና ይህንን
ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment