Monday, December 29, 2014

የሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ! 1

ዲቮሽን .109/07     እሁድ ታህሳስ 19/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ሙሉጊዜ አገልጋዮች ክፍያ – በኢትዮጵያ!


ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። …የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ (ፊል 4፡10-15)

<<በሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ክፍያ ዙሪያ የሚገርሙም፣ የሚያስቁም የሚያስለቅሱም ምስክርነቶችን ሰብስቤያለሁ፡፡ ከመሐል ኢትዮጵያከአዲስ አበባ፣ ከምዕራብ ኢትዮጵያጅማ፣ ከምሥራቅ ኢትዮጵያድረዳዋ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያባህርዳር፣ ከደቡብ ኢትዮጵያሐዋሳ በመምረጥ ሰፊ ጥናት አድርጌያለሁ፡፡>>

<<ባደረግሁት ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ከሚገኙ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች መካከል በሚያገኙት የገቢ መጠን ቤተሰባቸውንና ራሳቸውን በመልካም ሁኔታ መደጎም የሚችሉትን ፈልጎ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡>>

<<ለምሳሌ እንውሰድ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቤተሰብ ይዞ የሚኖር አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለወርሃዊ ቀለቡ ከአጥቢያው የሚከፈለው 800 ብር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ለአሥራትና ለሌሎች ወጭዎች ተቆራርጦ ከእጁ የሚገባው 700ብር አካባቢ ነው፡፡ ሚስቱ ሥራ የላትም፡፡ ከተጋቡ ስድስት አመት ቢሆናቸውም ልጅ አልወለዱም፡፡ አገልጋዩ እንዳጫወተኝ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ራሱን ከሰጠ አስር አመቱ ነው፡፡>>

<<ጊዜውን ከመስጠቱ በፊት የእንጨት ሥራ ድርጅት ነበረው፡፡ በሥሩም ስድስት ሠራተኞችን ቀጥሮ ያስተዳድር ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጠርቶት፣ ሥራውን እርግፍ አድርጎ ሲወጣ፣ በሙሉ እምነት ስለነበር የዛሬው አይነት ችግር ይገጥመኛል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡ ጥሪ ሲደርሰው በወቅቱ በእጁ ደህና ገንዘብ ስለነበረው ስለገንዘብ የሚጨነቅ ልብም አልነበረውም፡፡>>

<<ሥራውን ጥሎ ወደ አገልግሎት ሲወጣ ለአገልግሎቱ ክብር ሲል ትዳር መያዝ እንዳለበት ይመከራል፡፡ የጋለ የአገልግሎት መንፈስ የነበረው ይኼው <<ፍሬሽ>> አገልጋይ የተነገረውን ምክር ባጭር ጊዜ ተግባራዊ በማድረግ በካዚናው የቋጠራትን ሳንቲም አራግፎ ሰርግ ደገሰበት፡፡ በሰርጉ ዕለት በርካታ አገልጋዮችንና በመቶ የሚቆጠሩ ወገኖችን በመጥራት ቡፌ ደርድሮ ጮማ አስቆረጠ፡፡>>

<<የኑሮን የችግር ቡፌ ለመጋፈጥ የተገደደው ግን ወዲያው ነበር፡፡ የወር ወጭዎቻቸውን ለመሸፈን ባለመቻላቸው የድርጅታቸውን ዕቃዎች እየሸጡ ለጥቂት ዓመታት ታገሉ፡፡ ዕቃዎቹ ካለቁ በኋላ ግን በተደራራቢ ችግሮች ውስጥ ለማለፍ ተገደዱ፡፡ ቤተክርስቲያኑ ለብዙ ጊዜያት ስታጠናው ቆይታ ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት በ600 ብር ደመወዝ ተቀበለችው፡፡ በዚህ ገቢ ለ2 አመት ሲያገለግል ቆይቶ ወደ 800 ብር አደገለት፡፡ በዚያም ብር እስከዛሬ እየኖረበት ነው፡፡>>

<<በአጥቢያው ውስጥ ስለደመወዝ ጭማሪ የሚያነሳ አገልጋይም ሆነ መሪ የለም፡፡ በዚህም ስቃያቸውን እያዩ ቆዩ፡፡ ልጅ ለመውለድ ደግሞ አቅማቸው ስላልፈቀደ ልጅ እንዳማራቸው ቀረ፡፡>>

<<በውድ ዋጋ ተከራይተው በሚኖሩበት ቤት የሚበላ ነገር በማጣት ብዙ ጊዜ በምግብ እጦት ተፈትነዋል፡፡ እዚህ ላይ <ጻድቅ ሲራብ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም> ብለሽ ትጠቅሺልኝ ይሆናል፡፡ በርግጥ ለጥቅስ ለጥቅሱማ እኛን ማን አህሎን! ነገሩ ወዲያ ሆነ እንጂ፡፡>>

<<በፊት በፊት፣ አልፎ አልፎ <ጌታ ተናግሮናል> የሚሉ ወገኖች አገልጋዮችን የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ያደርጉላቸው ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን በዚያ መንገድ ጌታ የሚናገራቸው ቀንሰዋል፡፡ ስለተቸገሩ አገልጋዮች የሚያሳስባቸው ሰዎች እየከሰሙ ነው፡፡ አገልጋይ የተንሻፈፈ ጫማ አድርጎ ሲሄድ ምዕመኑ ይጠቋቆምበታል፡፡>>

<<የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችም ሆኑ አገልግሎታቸው ትኩረት እያጣ ነው፡፡ በፊት ብዙ ወገኖች በቤታቸው እንድንጎበኛቸውና እንድንከታተላቸው ይፈልጉ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ይህ አይነቱ ፍላጎት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ብዙዎቹ ሰዎች በሥራና በትምህርት እያሳበቡ አገልጋዮች ከቤታቸው እንዲመጡባቸው አይፈልጉም፡፡ በዚህም ረገድ የራሴንና የበርካታ አገልጋዮችን ምስክርነት ለማሰባሰብ ሞክሬያለሁ፡፡ በየጊዜው ከማነጋግራቸው አገልጋዮች ዘንድ የምሰማው ምስክርነት ልብ የሚሰብር ነው፡፡>> … (ምንጭ፣ የወንጌላዊው እጮኛ፣ ገጽ 39-40 የተቀነጨበ)

--------------------------------
‹‹የወንጌላዊ እጮኛ›› በሺዎች የተደነቀ ልብ አንጠልጣይ መጽሐፍ ዛሬ፣ እሁድ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ በ9፡00 ይመረቃል፡፡ ካዛንቺስ መካነየሱስ አጠገብ በሚገኘው በፒቲሲ እንዲገኙልኝና ይህንን ታሪካዊ መጽሐፍ እንዲመርቁልኝ በአክብሮት ጋብዤዎታለሁ፡፡


No comments:

Post a Comment