Saturday, January 31, 2015

ቀዳሽና ፈዋሽ – ከቤታችን ሲገባ!

ዲቮሽን .143/07     ቅዳሜጥር 23/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)



ቀዳሽና ፈዋሽ – ከቤታችን ሲገባ!

በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ። እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ (ማቴ 8፡16-17)።

ኃጢአት–ሕመምና–የዘላለም ሞት የማይነጣጠሉ ሦስታ ጠላቶቻችን ናቸው! የኃጢአት ምንጩ አለመታዘዝ ሲሆን፣ ሕመምና ሞት ደግሞ ውጤቶቹ ናቸው! ኃጢአት–ሕመምና–ሞት የሰውን ልጅ ለማጥፋት በሰይጣን የተጠነሰሱ ናቸው! እነዚህን ሦስታ ጠላቶች ለመደምሰስ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስታ ፍቱን መድኃኒቶች ለሰው አዘጋጅቷል! እነርሱም ስርየት–ፈውስና–የዘላለም ሕይወት ናቸው!

ወገኖች ሆይ፣ ሰይጣን የኃጢአት ጠንሳሽ፣ የሰው ልጆች አሳች፣ ከሳሽና አውጋዥ ሲሆን፣ እግዚአብሔር ግን የሕዝቡ ቀዳሽና ፈዋሽ ነው! ሰዎች ንስሐ በመግባት የኃጢአት መንገዳቸውን ቢተዉ፣ የእግዚአብሔር ምሕረቱ ለዘለዓለም ነው!

ታውቃላችሁ፣ ይኼ የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ኃጢአታችን እንደ አለላ ቢቀላ፣ እንደ በረዶ ያነጣዋል! የእግዚአብሔር ይቅርታ እንደ ደም የቀላውን ኃጢአታችንን እንደ ባዜቶ ነጭ ያደርገዋል! የእግዚአብሔር ምሕረት የሰውን ልጆች ኃጢአት ሀጫ በረዶ ያደርገዋል!

ታውቃላችሁ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም የማያነጻው ኃጢአት የለምና፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ማናቸውም ኃጢአታችንን በልጁ ደም አጥቦ ሀጫ በረዶ ያደርገዋል! ኃጢአታችን የፈለገው ደረጃ ላይ ቢገኝ፣ በደላችን የተለቀ ቢሆን፣ ክፋታችን የተወሳሰበ ቢሆን፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም የማያነጻው ኃጢአት የለም!

ወገኖች ሆይ፣ ኃጢአት ተከትሎ ልዩ ልዩ ደዌ ከሰው ልጆች ድንኳን በርግዶ ይገባል! ከዚህም የተነሳ የሰው ልጆች ጤና እጅግ ይቃወሳል፡፡ ነገር ግን፣ የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ጌታችን ኢየሱስ ከቤታችን ደጃፍ ደርሶ ሲያንኳኳ፣ ከፍተን ስናስገባው የበሽታ ኮተት ጠራርጎ ያወጣል!

ታውቃላችሁ፣ ጌታችን ኢየሱስ ከሕይወታችን ሲገባ የመንፈስ የሥጋ የነፍስ  ችግራችን ተጠርጎ ይወጣል! የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀን ብንሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብናደርግ፥ ትእዛዙንም ብናደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ አጥብቀን ብንጠብቅ፥ የሕዝቡ ሐኪምና ፈዋሽ ፈውሳችንን ይዞ ከእኛ ቤት ይገባል!

ወገኖች ሆይ፣ ፈዋሻችን እግዚአብሔር ከቤታችን ሲገባ ካንሰር ሆነ አልሰር፣ ደም ግፊት ደም ማነስ፣ ባክቴሪያና ቫይረስ ተጠርጎ ይወጣል! ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤታችን ሲገባ መተቱ አስማቱ፣ ሰላቢ ገጣቢ–ጥንቆላ ድግምቱ፣ ተጠርጎ ይወጣል! ኢየሱስ ወደ ሕይወታችን ሲገባ ሰይጣን ከነጓዙ ጤናችንን ለቅቆ፣ ነፍሳችንን ለቅቆ፣ ሥጋችንን ለቅቆ፣ ቤታችንን ለቅቆ፣ ተባርሮ ይወጣል!

ወገኖች ሆይ፣ ቅዱስ ቃሉ፣ ‹‹…አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ›› እንደሚል፣ ኃጢአተኞች ሁሉ፣ በአጋንንት እስራት የምንገኝ ሁሉ፣ በልዩ ልዩ ሕመም እየተሰቃየን ያለን ሁሉ ወደ ኢየሱስ እንምጣ! ድካማችንን ሁሉ፣ ደዌያችንንም ሁሉ፣ ሸክማችንንም ሁሉ ወደ እርሱ እናምጣ!

ወገኖች ሆይ፣ በጎልጎታ ስለ እኛ በተሰቀለው፣ ስለ መተላለፋችን በቈሰለው፥ ስለ በደላችንም በደቀቀው፣ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእራሱ ላይ ባደረገው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ቍስል እኛ ተፈውሰናልና፣ ይኼ ምሕረት፣ ይኼ ፈውስ ትናንት፣ ዛሬም፣ ነገ እስከዘላለምም ይቀጥላልና ድካማችንን ሁሉ፣ ደዌያችንንም ሁሉ፣ ሸክማችንንም ሁሉ ወደ እርሱ እናምጣ!

ወገኖች ሆይ፣ ድካማችንን ሁሉ፣ ደዌያችንንም ሁሉ፣ ሸክማችንንም ሁሉ ወደ እርሱ ስናመጣ የሚከተለው ዝማሬ ከሕይወታችን ይፈልቃል፣ አንደበታችንም እንዲህ ይዘምራል!

ለአጭር፡ ጊዜ አይደለም ለረጅም ዘመናት
በድካም በትግል ላያሌ ዓመታት
በመውደቅ መነሳት በውጊያ በጭንቀት
እንደማያልፍ የለም አለፈ እሳት

ዞር ብዬ ሳየው ያሳለፍኩትን፣
አባጣ ጎርባጣ ጉድጓድ ገደሉን
ማመን ይሳነኛል ኃይልን ከዬት አገኘሁ
ለካስ ኤልሻዳዩ ደግፎኝ ቆሜያለሁ
ስሙን አከብራለሁ፡፡

መራራ አይታኘክ የመከራ እንጀራ
የብቸኝነት ቤት እኔው ከእኔ ጋራ
እንቅልፌን አጥቼ ብዙ ለሊት አልፏል
ዛሬ ግን ታሪክ ነው ተረት ነው ይወራል

የሕይወቴ ማብቂያ ዛሬ ነው ያልኩበት
ዓይኖቼን ጨፍኜ ሞትን ያሰብኩበት
ቀውጤው ሰዓት አልፎ ማየቴ ደንቆኛል
ለካ ጌታ ወዶኝ እጅ እግሬን ጠብቋል

የአብርሃም አምላክ በክንፉ ሸሸገኝ
ለካ መጐዳቴን ተጐሳቁዬ አየኝ
ያን ሁሉ ሻካራ ያን ሁሉ ጐርባጣ
ጌታ ብርታት ሆነኝ ችዬው እንድወጣ
(ዘማሪ ዶ/ር ደረጀ ከበደ)

-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

Friday, January 30, 2015

ተስፋ አትቁረጥ!

ዲቮሽን .142/07     አርብጥር 22/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


ተስፋ አትቁረጥ! 

እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ፥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው (ዕብ 11፡1)።

የሰው ልጆች ሁሉ ሥጋዊና መንፈሳዊ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ፍላጎቶች አሉን፡፡ እነዚህን ሥጋዊና መንፈሳዊ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ፍላጎቶች ለማሟላት፣ በሥራና በትምህርት እንዲሁም በልዩ ልዩ መንገዶች ለማሳካት ጥረት እናደርጋለን፡፡ አንዳንዴ እነዚህ ጥረቶቻችን እንደተመኘነው ሲሳኩልን፣ አንዳንዴም ሳይሳኩልን ይቀራሉ፡፡ እነዚህ ሥጋዊና መንፈሳዊ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ፍላጎቶች ‹‹ተስፋ›› ይባላሉ!

ታውቃላችሁ፣ ተስፋ የሕይወት ጣዕም ነው! ይህ ጣዕም ሲጠፋ ሕይወት ውሃ ውሃ ማለት ይጀምራል! ሕይወት ውሃ ውሃ ሲል ደግሞ መኖር ትርጉም ያጣል፡፡ መኖር ትርጉም ሲያጣ አለመኖር ይከተላል!

ወገኖች ሆይ፣ አማኞች ሥጋዊና መንፈሳዊ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ፍላጎቶቻቸውን  ለማሳካት፣ በሥራና በትምህርት ላይ ብቻ አይተማመኑም! የአማኞች ተስፋ ካስማው የተተከለው፣ የሕይወታቸው መልሂቅ በጥብቅ የታሰረው፣ ድርና ማጋቸው የተቆላለፈው፣ ዕጣና ፈንታቸው የተመሠረተው – በእምነት ላይ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ እምነት ምንድነው! እምነትም ማለት ገና ያላየነውን ነገር፣ ‹‹ይሆናል›› ብለን ተስፋ የምናደርግበትና ተስፋ ያደረግነውም ነገር እንደሚፈጸም የምንረዳበት ማረጋገጫ ነው! የእምነታችን ዋስትና እግዚአብሔር ራሱ ነው!

ታውቃላችሁ፣ እምነት ለተስፋችን መፈጸም ማረጋገጫ ነው! የመጽሐፍ ቅዱስ አባቶች የተመሰከረላቸው በዚሁ መንገድ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ተስፋ መቁረጥ የሕይወት ጸር ነው፣ ተስፋ መቁረጥ የሕይወት አደጋ ነው! ተስፋ መቁረጥ ሲኖር ብርሃን ይጨልማል፣ ተስፋ መቁረጥ ካለ ተራ ነገር እንኳ ውስብስብ ይሆናል! ስለሆነም ተስፋ መቁረጥ ይቅር!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

Thursday, January 29, 2015

ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ!

ዲቮሽን .141/07    ሐሙስ፣ ጥር 21/07 .. 
(
በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)



ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ!

እናንተ ደካሞች፥ ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ (ማቴ 1128)፡፡
አዋጅ፥ አዋጅ፥ አዋጅ! ዛሬ በልዩ ልዩ ሽክም ምክንያት እያለቀሱ ላሉ ሁሉ የሚሆን መልዕክት ነው የተቀበልኩት!
አዋጅ፥ አዋጅ፥ አዋጅ! በዛሬው ዕለት እንባቸው እየፈሰሰ ላለ፥ መንታ መንታ እንባዎች ፊታቸው ላይ እየጎረፈ ላለ፥ በእንባቸው ምክንያት ፊታቸው ለበለዘ፥ በእንባቸው ምክንያት አይናቸው ለፈዘዘ ሁሉ የሚሆን መልዕክት!
አዋጅ፥ አዋጅ፥ አዋጅ! ለሰው ሁሉ የሚሆን መልዕክት! አንገታቸውን ደፍተው፥ ፊታቸውን ቀብረው በሐፍረትና ጸጸት ለሚመላለሱ፥ ሸክም ከብዶባቸው ለሚንገዳገዱ ለእግዚአብሔር ልጆች የተላከ መልዕክት!

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ እናንተ ደካሞች፥ ሸክም የከበደባችሁ ሁሉ፥ ሽክማችሁን ስጡኝ! ሸክማችሁን ሁሉ፥ ወደ እኔ አምጡና በእግሬ ስር ጣሉ! ትልቅ ይሁን ትንሽ፥ ጥቂት ሆነ ብዙ፥ ጠባብ ሆነ ሰፊ፥ የስጋና የነፍስ ማናቸውንም ሸክም ለእኔ ስጡኝና እስኪ ላሳርፋችሁ!

Wednesday, January 28, 2015

ከ'እነዚህ' ይልቅ እንወደዋለን?

ዲቮሽን .140/07     ረቡዕጥር 20/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


'እነዚህ' ይልቅ እንወደዋለን?

… ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን … ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። … ደግሞ ሁለተኛ። … ትወደኛለህን? አለው። … ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። … (ዮሐ 21፡15-17)።

የሰው ልጆች የሚወዷቸው ነገሮች ብዙ አሉ! ከእነዚህ መካከል ባልና ሚስት፣ ወላጅና ልጅ፣ ዘመድና አዝማድ፣ እህልና ውሃ፣ መጠሊያና ልብስ፣ ገንዘብና ሀብት፣ ድሎትና ምቾት፣ ጓደኛና ወዳጅ፣ ክብርና ዝና ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ ‹‹ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?›› ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ከወዳጅ ዘመድዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ከቁርስ ከምሳዎ፣ ከመኝታ ሰዓትዎ፣ ከእረፍት ጊዜዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ ከሥራ ቦታዎ፣ ከንግድ ከትርፍዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? አሁን ጌታ መጥቶ፣ ከወር ደመወዝዎ፣ ከአሥራት ከመባዎ፣ ከጊፍት ከስጦታዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ከሚወዷቸው ሰዎች፣ ከሚቀርቧቸው ወዳጆች፣ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ እየደጋገመ ከምንም ከማንም እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ለተጠየቁበት በልበ ሙሉነት ‹‹አዎ፣ ጌታዬ ሆይ ካንተ ሌላ የለም፣ ሊኖርም አይችልም›› ብለው በመመለስ ያስደስቱት ይሆን? ‹‹አዎ፣ ጌታዬ ሆይ ካንተ ወዲያ ወዳጅ፣ ካንተ ወዲያ ዘመድ፣ ካንተ ወዲያ ላሳር›› ብለው በመመለስ ያስደስቱት ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ እየደጋገመ ከምንም ከማንም እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት፣ ‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ፣ እንደ አምላኬ ያለ፣ እገረማለሁ የትም ስለሌለ›› ብለው ይዘምሩለት ይሆን? ‹‹አምላኬን የሚስተካከለው ማነው? ጌታዬን የሚስተካከለው ማነው? ኦ፣ እገረማለሁ፣ እኔ እንደነቃለሁ!›› ብለው በመዘመር ያስደንቁት ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ እየደጋገመ ከምንም ከማንም እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት፣ ግራ ቀኙን አይተው፣ መደመር–መቀነስ–ማባዛት–ማካፈሉን ሁሉን አመዛዝነው፣ መምረጥ ተቸግረው፣ አንገት አቀርቅረው፣ እጅዎትን በአፍዎት ላይ በድርቡ ጭነው ያሳፍሩት ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ የኢየሱስን ፍቅር ያስቡ! ባንዲት ሌሊት ሦስቴ የካደውን፣ የዮናን ልጅ ስምዖን ጴጥሮስን በፍቅር ሲስበው! ከሶስት አመት በላይ አብሮት የነበረውን፣ አብሮት እየተራበ አብሮት የበላውን፣ አብሮት እየተጠማ አብሮት የጠጣውን፣ አብሮት እየወደቀ አብሮት የተነሳውን፣ ያንን ታላቅ ጌታ፣ ያንን ታላቅ አምላክ በአንዲት ገረድ ፊት፣ በአንዲት ቀን ለሊት ሶስቴ የካደውን፣ ቂም ሳይቆጥር፣ በደሉን ሳይቋጥር በፍቅር ሲስበው!

ወዳጄ ሆይ፣ እንዴት ያለ መውደድ – ምን ዓይነት ፍቅር ነው! ያን በመሰለ ከሀዲ፣ ያን በመሰለ ፈሪ፣ ያን በመሰለ ጥሎ ሯጭ፣ ያን በመሰለ ተለዋዋጭ እጅ ትልቅ እምነት ጥሎ፣ የመንጋው እረኛ፣ በጎች ጠባቂ አድርጎ ሲሾመው – እንዴት ያለ መውደድ፣ ምን ዓይነት ፍቅር ነው!
ወዳጄ ሆይ፣ የኢየሱስን ፍቅር ያስቡ! ከሀዲውን አምኖ፣ የመሪነት ሹመት ለስምዖን ሰጥቶ፣ ‹‹ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ ግልገሎቼን መግብ፣ በጎቼን ምራ›› በማለት ሲሾመው – እንዴት ያለ መውደድ፣ ምን ዓይነት ፍቅር ነው!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

Tuesday, January 27, 2015

አደገኛ 'ፋውል' – አደገኛ ውድቀት!

ዲቮሽን .139/07     ማክሰኞጥር 19/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


አደገኛ 'ፋውል'  – አደገኛ ውድቀት! 

ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ። ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም (1 ሳሙ 9፡6)።

ሳኦል ዕድለኛ መሪ ነበር፡፡ ሳኦል ብንያማዊ ሲሆን ብንያም ደግሞ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ የመጨረሻው ወይንም ታናሹ ነገድ ነው! ሳኦል፣ ከታናሽነት ሥፍራ ተነስቶ ለታላቅነት ሥፍራ የበቃ፣ ማለትም የመጨረሻው የእስራኤል ነገድ ሆኖ ነገር የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ የተቀባ ዕድለኛ መሪ ነበር!

ወገኖች ሆይ፣ ሳኦልን ብዙዎች ባያውቁትም፣ ያወቁ ቢንቁትም፣ በእግዚአብሔር ርስቱ ላይ አለቃ እንዲሆን ለመቀባት በቃ! ብዙዎች ባያውቁት፣ ያወቁ ቢንቁት፣ ሳኦልን እግዚአብሔር አወቀው፣ እግዚአብሔር ቀባው! የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት የተለየ መንፈስ፣ የተለወጠ ልብ፣ የተለወጠ ጆሮ ያስፈልጋልና፣ ይህ ሁሉ ሆነለት!

ታውቃላችሁ፣ ታናሹ ሰውዬ ታላቁን ሹመት ለመቀበል ቻለ! በአናሳነቱ ምክንያት ሰዎች የማይሰጡትን ማዕረግና ክብር ሊንበሸበሽ ቻለ! ጽኑ ጦር ቢሰለፍ፣ ብርቱ ሰልፍ ቢነሳ፣ ጠላቱን ሳይፈራ ተዋግቶ ማሸነፍ መታወቂያው ሆነ!

ታውቃላችሁ፣ የኛ አናሳነት የእግዚአብሔርን ታላቅነት አይወስነውም! የእኛ ሰዋዊ ደረጃ፣ በሰው የተሰጠን ቦታ፣ በዙሪያችን ያለ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ቅባት ሊነፍገን አይችልም!

ታውቃላችሁ፣ ‹‹በአይኖችህ ከታየሁ ምን እፈልጋለሁ›› እንዲሉ፣ በአይኖቹ ከታየን የሚጎድለን የለም! የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ሥፍራ አይኖረውም!  በአይኖቹ ከታየን የእኛ ብቃት ማነስ፣ የእኛ ዕውቀት ማነስ፣ የእኛ አቅም ማነስ የእርሱን ችሎታ ሊገድብ አይችልም!

ወገኖች ሆይ፣ ብዙ ጊዜም ሳይቆይ፣ የብንያም ነገዱ ታናሹ ሰውዬ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንዲመራ የተሾመው ሳኦል፣ ከገባበት መስመር ወጣ ገባ ማለት፣ ከተሰጠው ሥራ ወለም ዘለም ለማለት ጀመረ! የተሰጠውን መንፈስ አውልቆና ጥሎ፣ የተገጠመለትን ኦሪጂናሌ ልብ በሰልባጅ ቀይሮ፣ ድምጹን እንዲሰማ ጆሮዎቹን ደፍኖ፣ ከአምድ ከፋንዲያ አንስቶ በቀባው በእግዚአብሔር አመጸ!

ታውቃላችሁ፣ ንጉሡ ሳኦል በሥልጣን ጨዋታው ብዙም ሳይቆይበት በአደገኛ ፋውል፣ በቀይ ተባረረ! የታዘዘውን ትቶ ያልታዘዘውን በማድረግ መመሪያውን ጣሰ! ከመሬት አንስቶ ለቀባው ለእግዚአብሔር አልታዘዝ አለ! ስለሆነም፣ ከአገልግሎታችን ይልቅ መታዘዛችንን የሚፈልግ ጌታ የሳኦልን ዙፋን አንኮታኩቶ ጣለ! ክብር ያልወደደለት የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ከመንበሩ ወርዶ ተንከራታች ሆነ! እየተንከራተተም በበረሃ ሞተ!

ታውቃላችሁ፣ ሳኦል ከእግዚአብሔር ጋራ ስምም በነበረ ጊዜ ጠላት የማይፈራ፣  ልቡም የማይሸበር የማይንቀጠቀጥ ጀግና ንጉሥ ነበር። ሳኦል ከእግዚአብሔር ጋራ ስምም በነበረ ጊዜ አምላኩን ሲጠይቅ ቶሎ መልስ የሚያገኝ የእግዚአብሔር ሰው ነበር! ከእግዚአብሔር ሲጣላ ጩኸቱና ጥሪው የማይደመጥ ሆነ! የጩኸቱ ምላሽ በሕልሙም በኡሪሙም ወይም በነቢያቱ የማይመለስ ሆነ!

ታውቃላችሁ፣ ከአመጻ መንገዳችን ካልተመለስን በስተቀር ጩኸታችን እሪ በከንቱ ነው! ከእግዚአብሔር ተጣልተን፣ ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ገደል ማሚቱ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ሳኦል ፋውል ሠራ ከእግዚአብሔር ተጣላ! ከእግዚአብሔር ሲጣላ ጠላት የሚፈራ፣ በሆነ ባልሆነው የሚደነግጥና የሚሸበር ሆነ! ከእግዚአብሔር ተጣልቶ እምነቱ ድፍረቱ ብቃቱና ኃይሉ ተለይቶታልና – ጭፍራ ባየ ጊዜ መደንበር ጀመረ!

ወገኖች ሆይ፣ ከእግዚአብሔር ተጣልቶ ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ከንቱ ድካም ነውና ከእርሱ እንዳንጣላ ጥንቃቄ እናድርግ! ከእግዚአብሔር መጣላት ትልቅ አደጋ ነውና፣ አደገኛ 'ፋውል' ነውና ከእርሱ እንዳንጣላ ጥንቃቄ እናድርግ! አደገኛ 'ፋውል' – አደገኛ ውድቀት ያስከትላልና ጥንቃቄ እናድርግ! 
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡