ዲቮሽን
ቁ.143/07 ቅዳሜ፣ ጥር 23/07 ዓ.ም.
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)
ቀዳሽና ፈዋሽ – ከቤታችን ሲገባ!
በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ። እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ (ማቴ 8፡16-17)።
ኃጢአት–ሕመምና–የዘላለም
ሞት የማይነጣጠሉ ሦስታ ጠላቶቻችን ናቸው! የኃጢአት ምንጩ አለመታዘዝ ሲሆን፣ ሕመምና ሞት ደግሞ ውጤቶቹ ናቸው! ኃጢአት–ሕመምና–ሞት
የሰውን ልጅ ለማጥፋት በሰይጣን የተጠነሰሱ ናቸው! እነዚህን ሦስታ ጠላቶች ለመደምሰስ ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስታ
ፍቱን መድኃኒቶች ለሰው አዘጋጅቷል! እነርሱም ስርየት–ፈውስና–የዘላለም
ሕይወት ናቸው!
ወገኖች ሆይ፣ ሰይጣን የኃጢአት ጠንሳሽ፣ የሰው ልጆች አሳች፣ ከሳሽና አውጋዥ
ሲሆን፣ እግዚአብሔር ግን የሕዝቡ ቀዳሽና ፈዋሽ ነው! ሰዎች ንስሐ በመግባት የኃጢአት መንገዳቸውን ቢተዉ፣ የእግዚአብሔር ምሕረቱ
ለዘለዓለም ነው!
ታውቃላችሁ፣ ይኼ የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ኃጢአታችን እንደ አለላ ቢቀላ፣
እንደ በረዶ ያነጣዋል! የእግዚአብሔር ይቅርታ እንደ ደም የቀላውን ኃጢአታችንን እንደ ባዜቶ ነጭ ያደርገዋል! የእግዚአብሔር ምሕረት
የሰውን ልጆች ኃጢአት ሀጫ በረዶ ያደርገዋል!
ታውቃላችሁ፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም የማያነጻው ኃጢአት የለምና፣ የእግዚአብሔር
ምሕረት ማናቸውም ኃጢአታችንን በልጁ ደም አጥቦ ሀጫ በረዶ ያደርገዋል! ኃጢአታችን የፈለገው ደረጃ ላይ ቢገኝ፣ በደላችን የተለቀ
ቢሆን፣ ክፋታችን የተወሳሰበ ቢሆን፣ የክርስቶስ ኢየሱስ ደም የማያነጻው ኃጢአት የለም!
ወገኖች ሆይ፣ ኃጢአት ተከትሎ ልዩ ልዩ ደዌ ከሰው ልጆች ድንኳን በርግዶ ይገባል! ከዚህም የተነሳ የሰው ልጆች
ጤና እጅግ ይቃወሳል፡፡ ነገር ግን፣ የተናቀ
ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ጌታችን ኢየሱስ ከቤታችን ደጃፍ ደርሶ ሲያንኳኳ፣ ከፍተን ስናስገባው የበሽታ ኮተት
ጠራርጎ ያወጣል!
ታውቃላችሁ፣ ጌታችን
ኢየሱስ ከሕይወታችን ሲገባ የመንፈስ የሥጋ የነፍስ ችግራችን ተጠርጎ
ይወጣል! የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀን ብንሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብናደርግ፥ ትእዛዙንም ብናደምጥ፥ ሥርዓቱንም
ሁሉ አጥብቀን ብንጠብቅ፥ የሕዝቡ ሐኪምና ፈዋሽ ፈውሳችንን ይዞ ከእኛ ቤት ይገባል!
ወገኖች ሆይ፣ ፈዋሻችን እግዚአብሔር ከቤታችን ሲገባ ካንሰር ሆነ አልሰር፣
ደም ግፊት ደም ማነስ፣ ባክቴሪያና ቫይረስ ተጠርጎ ይወጣል! ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤታችን ሲገባ መተቱ አስማቱ፣ ሰላቢ ገጣቢ–ጥንቆላ
ድግምቱ፣ ተጠርጎ ይወጣል! ኢየሱስ ወደ ሕይወታችን ሲገባ ሰይጣን ከነጓዙ ጤናችንን ለቅቆ፣ ነፍሳችንን ለቅቆ፣ ሥጋችንን ለቅቆ፣
ቤታችንን ለቅቆ፣ ተባርሮ ይወጣል!
ወገኖች ሆይ፣ ቅዱስ ቃሉ፣ ‹‹…አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ እርሱ ድካማችንን
ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ›› እንደሚል፣ ኃጢአተኞች
ሁሉ፣ በአጋንንት እስራት የምንገኝ ሁሉ፣ በልዩ ልዩ ሕመም እየተሰቃየን ያለን ሁሉ ወደ ኢየሱስ እንምጣ! ድካማችንን ሁሉ፣ ደዌያችንንም
ሁሉ፣ ሸክማችንንም ሁሉ ወደ እርሱ እናምጣ!
ወገኖች ሆይ፣ በጎልጎታ ስለ እኛ በተሰቀለው፣ ስለ መተላለፋችን በቈሰለው፥ ስለ በደላችንም በደቀቀው፣ የደኅንነታችንም
ተግሣጽ በእራሱ ላይ ባደረገው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ቍስል እኛ ተፈውሰናልና፣ ይኼ ምሕረት፣ ይኼ ፈውስ ትናንት፣ ዛሬም፣ ነገ እስከዘላለምም
ይቀጥላልና ድካማችንን ሁሉ፣ ደዌያችንንም ሁሉ፣ ሸክማችንንም ሁሉ ወደ እርሱ እናምጣ!
ወገኖች ሆይ፣
ድካማችንን ሁሉ፣ ደዌያችንንም ሁሉ፣ ሸክማችንንም ሁሉ ወደ እርሱ ስናመጣ የሚከተለው ዝማሬ ከሕይወታችን ይፈልቃል፣ አንደበታችንም
እንዲህ ይዘምራል!
ለአጭር፡ ጊዜ ፡ አይደለም ፡ ለረጅም ፡ ዘመናት
በድካም ፡ በትግል ፡ ላያሌ ፡ ዓመታት
በመውደቅ ፡ መነሳት ፡ በውጊያ ፡ በጭንቀት
እንደማያልፍ ፡ የለም ፡ አለፈ ፡ ያ ፡ እሳት
ዞር
ብዬ ሳየው ያሳለፍኩትን፣
አባጣ
ጎርባጣ ጉድጓድ ገደሉን
ማመን
ይሳነኛል ኃይልን ከዬት አገኘሁ
ለካስ
ኤልሻዳዩ ደግፎኝ ቆሜያለሁ
ስሙን
አከብራለሁ፡፡
መራራ ፡ አይታኘክ ፡ የመከራ ፡ እንጀራ
የብቸኝነት ፡ ቤት ፡ እኔው ፡ ከእኔ ፡ ጋራ
እንቅልፌን ፡ አጥቼ ፡ ብዙ ፡ ለሊት ፡ አልፏል
ዛሬ ፡ ግን ፡ ታሪክ ፡ ነው ፡ ተረት ፡ ነው ፡ ይወራል
የሕይወቴ ፡ ማብቂያ ፡ ዛሬ ፡ ነው ፡ ያልኩበት
ዓይኖቼን ፡ ጨፍኜ ፡ ሞትን ፡ ያሰብኩበት
ቀውጤው ፡ ሰዓት ፡ አልፎ ፡ ማየቴ ፡ ደንቆኛል
ለካ ፡ ጌታ ፡ ወዶኝ ፡ እጅ ፡ እግሬን ፡ ጠብቋል
የአብርሃም ፡ አምላክ ፡ በክንፉ ፡ ሸሸገኝ
ለካ ፡ መጐዳቴን ፡ ተጐሳቁዬ ፡ አየኝ
ያን ፡ ሁሉ ፡ ሻካራ ፡ ያን ፡ ሁሉ ፡ ጐርባጣ
ጌታ ፡ ብርታት ፡ ሆነኝ ፡ ችዬው ፡ እንድወጣ
መራራ ፡ አይታኘክ ፡ የመከራ ፡ እንጀራ
የብቸኝነት ፡ ቤት ፡ እኔው ፡ ከእኔ ፡ ጋራ
እንቅልፌን ፡ አጥቼ ፡ ብዙ ፡ ለሊት ፡ አልፏል
ዛሬ ፡ ግን ፡ ታሪክ ፡ ነው ፡ ተረት ፡ ነው ፡ ይወራል
የሕይወቴ ፡ ማብቂያ ፡ ዛሬ ፡ ነው ፡ ያልኩበት
ዓይኖቼን ፡ ጨፍኜ ፡ ሞትን ፡ ያሰብኩበት
ቀውጤው ፡ ሰዓት ፡ አልፎ ፡ ማየቴ ፡ ደንቆኛል
ለካ ፡ ጌታ ፡ ወዶኝ ፡ እጅ ፡ እግሬን ፡ ጠብቋል
የአብርሃም ፡ አምላክ ፡ በክንፉ ፡ ሸሸገኝ
ለካ ፡ መጐዳቴን ፡ ተጐሳቁዬ ፡ አየኝ
ያን ፡ ሁሉ ፡ ሻካራ ፡ ያን ፡ ሁሉ ፡ ጐርባጣ
ጌታ ፡ ብርታት ፡ ሆነኝ ፡ ችዬው ፡ እንድወጣ
(ዘማሪ ዶ/ር ደረጀ ፡ ከበደ)
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
--------------------------------
‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ
በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡
No comments:
Post a Comment