Tuesday, January 27, 2015

አደገኛ 'ፋውል' – አደገኛ ውድቀት!

ዲቮሽን .139/07     ማክሰኞጥር 19/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


አደገኛ 'ፋውል'  – አደገኛ ውድቀት! 

ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ። ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም (1 ሳሙ 9፡6)።

ሳኦል ዕድለኛ መሪ ነበር፡፡ ሳኦል ብንያማዊ ሲሆን ብንያም ደግሞ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ የመጨረሻው ወይንም ታናሹ ነገድ ነው! ሳኦል፣ ከታናሽነት ሥፍራ ተነስቶ ለታላቅነት ሥፍራ የበቃ፣ ማለትም የመጨረሻው የእስራኤል ነገድ ሆኖ ነገር የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ የተቀባ ዕድለኛ መሪ ነበር!

ወገኖች ሆይ፣ ሳኦልን ብዙዎች ባያውቁትም፣ ያወቁ ቢንቁትም፣ በእግዚአብሔር ርስቱ ላይ አለቃ እንዲሆን ለመቀባት በቃ! ብዙዎች ባያውቁት፣ ያወቁ ቢንቁት፣ ሳኦልን እግዚአብሔር አወቀው፣ እግዚአብሔር ቀባው! የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት የተለየ መንፈስ፣ የተለወጠ ልብ፣ የተለወጠ ጆሮ ያስፈልጋልና፣ ይህ ሁሉ ሆነለት!

ታውቃላችሁ፣ ታናሹ ሰውዬ ታላቁን ሹመት ለመቀበል ቻለ! በአናሳነቱ ምክንያት ሰዎች የማይሰጡትን ማዕረግና ክብር ሊንበሸበሽ ቻለ! ጽኑ ጦር ቢሰለፍ፣ ብርቱ ሰልፍ ቢነሳ፣ ጠላቱን ሳይፈራ ተዋግቶ ማሸነፍ መታወቂያው ሆነ!

ታውቃላችሁ፣ የኛ አናሳነት የእግዚአብሔርን ታላቅነት አይወስነውም! የእኛ ሰዋዊ ደረጃ፣ በሰው የተሰጠን ቦታ፣ በዙሪያችን ያለ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ቅባት ሊነፍገን አይችልም!

ታውቃላችሁ፣ ‹‹በአይኖችህ ከታየሁ ምን እፈልጋለሁ›› እንዲሉ፣ በአይኖቹ ከታየን የሚጎድለን የለም! የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ሥፍራ አይኖረውም!  በአይኖቹ ከታየን የእኛ ብቃት ማነስ፣ የእኛ ዕውቀት ማነስ፣ የእኛ አቅም ማነስ የእርሱን ችሎታ ሊገድብ አይችልም!

ወገኖች ሆይ፣ ብዙ ጊዜም ሳይቆይ፣ የብንያም ነገዱ ታናሹ ሰውዬ፣ የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንዲመራ የተሾመው ሳኦል፣ ከገባበት መስመር ወጣ ገባ ማለት፣ ከተሰጠው ሥራ ወለም ዘለም ለማለት ጀመረ! የተሰጠውን መንፈስ አውልቆና ጥሎ፣ የተገጠመለትን ኦሪጂናሌ ልብ በሰልባጅ ቀይሮ፣ ድምጹን እንዲሰማ ጆሮዎቹን ደፍኖ፣ ከአምድ ከፋንዲያ አንስቶ በቀባው በእግዚአብሔር አመጸ!

ታውቃላችሁ፣ ንጉሡ ሳኦል በሥልጣን ጨዋታው ብዙም ሳይቆይበት በአደገኛ ፋውል፣ በቀይ ተባረረ! የታዘዘውን ትቶ ያልታዘዘውን በማድረግ መመሪያውን ጣሰ! ከመሬት አንስቶ ለቀባው ለእግዚአብሔር አልታዘዝ አለ! ስለሆነም፣ ከአገልግሎታችን ይልቅ መታዘዛችንን የሚፈልግ ጌታ የሳኦልን ዙፋን አንኮታኩቶ ጣለ! ክብር ያልወደደለት የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ከመንበሩ ወርዶ ተንከራታች ሆነ! እየተንከራተተም በበረሃ ሞተ!

ታውቃላችሁ፣ ሳኦል ከእግዚአብሔር ጋራ ስምም በነበረ ጊዜ ጠላት የማይፈራ፣  ልቡም የማይሸበር የማይንቀጠቀጥ ጀግና ንጉሥ ነበር። ሳኦል ከእግዚአብሔር ጋራ ስምም በነበረ ጊዜ አምላኩን ሲጠይቅ ቶሎ መልስ የሚያገኝ የእግዚአብሔር ሰው ነበር! ከእግዚአብሔር ሲጣላ ጩኸቱና ጥሪው የማይደመጥ ሆነ! የጩኸቱ ምላሽ በሕልሙም በኡሪሙም ወይም በነቢያቱ የማይመለስ ሆነ!

ታውቃላችሁ፣ ከአመጻ መንገዳችን ካልተመለስን በስተቀር ጩኸታችን እሪ በከንቱ ነው! ከእግዚአብሔር ተጣልተን፣ ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ገደል ማሚቱ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ሳኦል ፋውል ሠራ ከእግዚአብሔር ተጣላ! ከእግዚአብሔር ሲጣላ ጠላት የሚፈራ፣ በሆነ ባልሆነው የሚደነግጥና የሚሸበር ሆነ! ከእግዚአብሔር ተጣልቶ እምነቱ ድፍረቱ ብቃቱና ኃይሉ ተለይቶታልና – ጭፍራ ባየ ጊዜ መደንበር ጀመረ!

ወገኖች ሆይ፣ ከእግዚአብሔር ተጣልቶ ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ከንቱ ድካም ነውና ከእርሱ እንዳንጣላ ጥንቃቄ እናድርግ! ከእግዚአብሔር መጣላት ትልቅ አደጋ ነውና፣ አደገኛ 'ፋውል' ነውና ከእርሱ እንዳንጣላ ጥንቃቄ እናድርግ! አደገኛ 'ፋውል' – አደገኛ ውድቀት ያስከትላልና ጥንቃቄ እናድርግ! 
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment