Wednesday, January 28, 2015

ከ'እነዚህ' ይልቅ እንወደዋለን?

ዲቮሽን .140/07     ረቡዕጥር 20/07 ..
(በመጋቢ ተስፋሁን ሐጢያ)


'እነዚህ' ይልቅ እንወደዋለን?

… ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን … ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። … ደግሞ ሁለተኛ። … ትወደኛለህን? አለው። … ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። … (ዮሐ 21፡15-17)።

የሰው ልጆች የሚወዷቸው ነገሮች ብዙ አሉ! ከእነዚህ መካከል ባልና ሚስት፣ ወላጅና ልጅ፣ ዘመድና አዝማድ፣ እህልና ውሃ፣ መጠሊያና ልብስ፣ ገንዘብና ሀብት፣ ድሎትና ምቾት፣ ጓደኛና ወዳጅ፣ ክብርና ዝና ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ ‹‹ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን?›› ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ከወዳጅ ዘመድዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ከቁርስ ከምሳዎ፣ ከመኝታ ሰዓትዎ፣ ከእረፍት ጊዜዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ ከሥራ ቦታዎ፣ ከንግድ ከትርፍዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? አሁን ጌታ መጥቶ፣ ከወር ደመወዝዎ፣ ከአሥራት ከመባዎ፣ ከጊፍት ከስጦታዎ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ከሚወዷቸው ሰዎች፣ ከሚቀርቧቸው ወዳጆች፣ እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ እየደጋገመ ከምንም ከማንም እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት መልስዎ ምን ይሆን? ለተጠየቁበት በልበ ሙሉነት ‹‹አዎ፣ ጌታዬ ሆይ ካንተ ሌላ የለም፣ ሊኖርም አይችልም›› ብለው በመመለስ ያስደስቱት ይሆን? ‹‹አዎ፣ ጌታዬ ሆይ ካንተ ወዲያ ወዳጅ፣ ካንተ ወዲያ ዘመድ፣ ካንተ ወዲያ ላሳር›› ብለው በመመለስ ያስደስቱት ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ እየደጋገመ ከምንም ከማንም እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት፣ ‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ፣ እንደ አምላኬ ያለ፣ እገረማለሁ የትም ስለሌለ›› ብለው ይዘምሩለት ይሆን? ‹‹አምላኬን የሚስተካከለው ማነው? ጌታዬን የሚስተካከለው ማነው? ኦ፣ እገረማለሁ፣ እኔ እንደነቃለሁ!›› ብለው በመዘመር ያስደንቁት ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ አሁን ጌታ መጥቶ፣ እየደጋገመ ከምንም ከማንም እኔን አስበልጠህ ትወደኛለህ ቢልዎት፣ ግራ ቀኙን አይተው፣ መደመር–መቀነስ–ማባዛት–ማካፈሉን ሁሉን አመዛዝነው፣ መምረጥ ተቸግረው፣ አንገት አቀርቅረው፣ እጅዎትን በአፍዎት ላይ በድርቡ ጭነው ያሳፍሩት ይሆን?

ወዳጄ ሆይ፣ የኢየሱስን ፍቅር ያስቡ! ባንዲት ሌሊት ሦስቴ የካደውን፣ የዮናን ልጅ ስምዖን ጴጥሮስን በፍቅር ሲስበው! ከሶስት አመት በላይ አብሮት የነበረውን፣ አብሮት እየተራበ አብሮት የበላውን፣ አብሮት እየተጠማ አብሮት የጠጣውን፣ አብሮት እየወደቀ አብሮት የተነሳውን፣ ያንን ታላቅ ጌታ፣ ያንን ታላቅ አምላክ በአንዲት ገረድ ፊት፣ በአንዲት ቀን ለሊት ሶስቴ የካደውን፣ ቂም ሳይቆጥር፣ በደሉን ሳይቋጥር በፍቅር ሲስበው!

ወዳጄ ሆይ፣ እንዴት ያለ መውደድ – ምን ዓይነት ፍቅር ነው! ያን በመሰለ ከሀዲ፣ ያን በመሰለ ፈሪ፣ ያን በመሰለ ጥሎ ሯጭ፣ ያን በመሰለ ተለዋዋጭ እጅ ትልቅ እምነት ጥሎ፣ የመንጋው እረኛ፣ በጎች ጠባቂ አድርጎ ሲሾመው – እንዴት ያለ መውደድ፣ ምን ዓይነት ፍቅር ነው!
ወዳጄ ሆይ፣ የኢየሱስን ፍቅር ያስቡ! ከሀዲውን አምኖ፣ የመሪነት ሹመት ለስምዖን ሰጥቶ፣ ‹‹ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ ግልገሎቼን መግብ፣ በጎቼን ምራ›› በማለት ሲሾመው – እንዴት ያለ መውደድ፣ ምን ዓይነት ፍቅር ነው!
-----
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!

--------------------------------

‹‹የወንጌላዊው እጮኛ›› አዲስ መጽሐፍ፣ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ በ0911 678158 ወይም 0911 813092 ይደውሉ፡፡

No comments:

Post a Comment