ዲቮሽን 306/07፥ ሰኞ፥ ሐምሌ 6/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ከፊትህ – አትጣለኝ!
ከፊትህ አትጣለኝ፥ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ (መዝ 51:11)፡፡
ወገኖች ሆይ፥ ከተጠቀምናቸው በኋላ በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ የምንጥላቸው ልዩ ልዩ ዓይነት ቆሻሻዎች፥ ከተጣሉበት ገንዳ ውስጥ ተለቅመው ወጥተው ወደ ሌላ መልክ ተቀይረው (ሪሳይክል ተደርገው) ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡
ታውቃላችሁ፥ ሰው የጣለው ቆሻሻ ዋጋ ያለው ሲሆን፥ ጌታ የጣለው ሰው ምንም ዋጋ የለውም! የሰው ልጅ የጣለው በሰው ልጅ ሲነሳ ጌታ የጣለው ሰው በሰው አይነሳም!
ወገኖች ሆይ፥ መዝሙረኛው፥ "ከፊትህ አትጣለኝ" እያለ የሚማጸነው - ከጌታ ፊት መጣል የሚያስከትለውን አደጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው!
ወገኖች ሆይ፥ መዝሙረኛው ሲጸልይ (መዝ 27፡4)፥ "እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ…" እያለ የሚማጸነውም ከዚህ እውቀቱ ነው!
ወገኖች ሆይ፥ መዝሙረኛው ሲጸልይ፥ "ከፊትህ አትጣለኝ" ብሎ ብቻ አያቆምም - "ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ" ብሎም ነው እንጂ!
ታውቃላችሁ፥ ከእግዚአብሔር ፊት አለመጣላችንን የምናረጋግጠው ውስጣችን በሚኖረው በቅዱስ መንፈሱ ነው፡፡ ይኼ ቅዱስ መንፈስ በውስጣችን እንዲኖር ጌታ ያደረገው ልጆቹ "አባ አባት" ብለው መጥራት እንዲችሉ፥ እርሱም "እነሆኝ ልጄ" ብሎ ይመልስ ዘንድ ነው፡፡
ታውቃላችሁ፥ ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ከሌለ፥ የአባትና የልጅ ግንኙነት ተበጠሰ ማለት ነው! ቅዱስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኛ ውስጥ ከሌለ፥ ከእግዚአብሔር ፊት ተተፋን፥ ተጣልን ማለት ነው! ከእግዚአብሔር የተጣለ ሰው አለቀለት ማለት ነው! ያለቀለት ሰው ደግሞ፥ ወደ ሲዖል ገባ፥ ለዘላለም ጠፋ ማለትም ጭምር ነው!
------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 60 ቀን ቀርቶታል፡፡
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6/07 ዓ/ም ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 60 ቀን ቀርቶታል፡፡
No comments:
Post a Comment