Monday, July 13, 2015

የአሕዛብ – አማልክት!

ዲቮሽን 305/07፥ እሁድ፥ ሐምሌ 5/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


የአሕዛብ – አማልክት!


የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ (መዝ 95፡6፤1 ዜና 16፡26) ።
ከ20 ዓመታት በፊት ጎረቤቶቼ ጸበል ቅመስ እያሉ በሚጋብዙኝ ሐይማኖታዊ በዓላት ምንም ሳይመስለኝ እሄድ ነበር፡፡ ከአልኮሆል መጠጦች በስተቀር የሚቀርብልኝን ሁሉንም ዓይነት ምግብ ተመግቤ ተጫውቼ ወደቤቴ እመለስ ነበር፡፡ በዚም ሁኔታዬ ጎረቤቶቼ ‹‹የማያካብድ ጴንጤ›› የሚል ቅጽል ሰጥተውኝ እነደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ በእኔ ቤት እነዚህ አጋጣሚዎች የበለጠ ከአሕዛብ ጋር ለመቀራረብና ወንጌልን ለማካፈል ዕድል ይሰጣል በሚል ነው፡፡ እስከማስታውሰው ድረስ ግን በእንዲህ መልኩ ልቡ ተለውጦ ጌታን የተቀበለ ሰው ትዝ አይለኝም፡፡


አንድ ጊዜ በሕልሜ ዝንጀሮ ጸበል ቅመስ ብላኝ ከቤቷ ሄድኩ፡፡ ቤቷ ስገባ በየቦታው በስብሰውና ለማየት እንኳ የሚቀፍፉ እጅግ አስቀያሚ የሆነ ጠረን ያላቸው እዳሪዎች እዚህና እዚያ ወዳድቀው ይታያሉ፡፡ የቤቱ ጠረን ሳንባ መተንፈሻ እስኪያቅተው ድረስ የታፈነ ነው፡፡ ይሁንና በይሉኝታ ተይዤ ወደቤቱ ዘልቄ ገባሁና በተዘጋጀልኝ መቀመጫ ላይ ተሸማቅቄ ተቀመጥሁ፡፡ ዙሪያዬ ሁሉ በእዳሪ የተከበበና የተጨማለቀ ስለሆነ እንደልቤ መንቀሳቀስ አልችልም ነበር፡፡


ዝንጀሮዋ እጇ በእዳሪ ቆሻሻ ተበክሎ ሳለ ነገር ግን ምንም ሳይመስላት ምግብ እየተመገበች ለእኔ ደግሞ ቡና ልታፈላልኝ ቡና ትወቅጥ ነበር፡፡ ከደቂቃዎች ቆይታ በኋላ በዓይኖቼ የማየውንና በአፍንጫዬ የማሸትተውን ነገር መቋቋም ስላልቻልኩ ውስጤ ይገለባበጥና ወደላይ ወደላይም ይለኝ ጀመር፡፡ በዚህ የጭንቅ ቅጽበት ከእንልቅፌ ነቃሁ፡፡ ተነስቼ እንኳ በውስጤ የነበረው መረበሽ የእውነትም ይረብሸኝ ቀጠለ፡፡ ከእንቅልፌ ነቅቼ እንኳ ወደዓእምሮዬ እስከምመለስ ድረስ ትንፋሽ አጥሮኝ በኃይል እተነፍስ ነበር፡፡ ላብ በላብም ሆኛለሁ፡፡


ታዲያ ከእንቅልፌ በደንብ ነቅቼ የሆነውን ሁሉ ሳስተውል ያቺ በእውኗ ዓለም ‹‹ጸበል ቅመስ›› የምትባለዋ ነገር፣ በሕልሜ ካየሁት የዝንጀሮ ግብዣ ጋር ተመሣሣይ እንደሆነችና አጋንንታዊ አምልኮ እንዳላት ጌታ አስተማረኝ፡፡ ተዚያች ዕለት ጀምሮ አስተዛሬ ድረስ የትም ዘመድ ቤት፥ የትም ቦታ ቢሆን ‹‹ጸበል ቅመስ›› ግብዣ ድርሽ ብዬ አላውቅም፡፡


ወገኖች ሆይ፣ በዓለማችን ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የአሕዛብ አማልክት አሉ፡፡ በሰማይ አካላት የተመሰሉ፣ በፀሐይ በጨረቃ የተመሰሉ፣ በቅዱሳን መላዕክትም ጭምር የተመሰሉ ብዙ የአሕዛብ አማልክት አሉ፡፡ እነዚህን አማልክት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓለማችን አሕዛብ ያመልኳቸዋል፡፡


ወገኖች ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል – የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸው! በምድር ላይ ይሁን፣ ከምድር በታች፣ ወይም በየትኛውም ስፍራ እንዲሁም በሰማይ አካላት ዘንድ የሚገኙ ማናቸውም የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸው!


ወገኖች ሆይ፣ በርካታ ሰዎች የክርስትና ስም ይዘው የአምልኮ መልክ ይዘው ነገር ግን አጋንንትን ማምለክ እስካሁን ስላልተዉ፣ ጣዖታትን ማምለክ ዛሬም ሳልተዉ፣ ደግሞም መንፈሳዊ ዕውቀት ስላልበራላቸው በአጋንንት አምልኮ የተጠመዱ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡


ወገኖች ሆይ፣ የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና እኛ አናመልካቸውም፡፡ ልናመልከው የሚገባው በሰማይና በምድር የሚኖሩትንና የሚንቀሳቀሱትን እንዲሁም የማይንቀሳቀሱትንም ሁሉ የፈጠረውን የሠራዊቱን ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን ብቻ ነው!


-----------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ላይ ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 61 ቀናትብቻ ቀርተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment