Saturday, July 11, 2015

ታሪክ ባይኖርህ – ቃል ይኑርህ!



ዲቮሽን 304/07 ቅዳሜ፥ ሐምሌ 4/07 /
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)

ታሪክ ባይኖርህቃል ይኑርህ!

በገለዓድ ቴስቢ የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን፦ በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም አለው(1 ነገ 17፡1)።


ወገኖች ሆይ፣ ከዚህ ምዕራፍ በፊት ስለ ኤልያስ ማንነት ምንም የሚታወቅ ታሪክ የለም! መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኤልያስ ሲነግረን ከገለዓድ ቀበሌዎች አንዱ ከሆነው ቴስቢ የመጣ ቴስብያዊው ከመሆኑ ሌላ ምንም የሚነገረን መረጃ አይነግረንም፡፡ ቃሉ ስለ ኤልያስ ሲነግረን ‹‹ማን ቢወልድ ማን›› የሚል የዘርና የሐረግ መዘርዝር አይሰጠንም! 


ወገኖች ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ታሪኩ ማንነት ባይነግረንም፣ የዘር ሐረጉን ቤትና ግንዱን ባይዘረዝርልንም፣ የት እንደተማረና ስንት ዲግሪ እንደጫነ ባይተነትንልንም፣ ምን ታሪክ እንዳለው አንዳች ባይነግረንም፣ ነገር ግን ኤልያስ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም፣ በአፉ ቃል ያለው፣ ሰማያትን መዝጋት መክፈትም የሚችል ታላቅ ሥልጣን ያለው ሰው መሆኑን ይመሰክራል!


ታውቃላችሁ፣ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም አቅም ይኑረን እንጂ፣ በአፋችንም ውስጥ ቃሉ ይኑር እንጂ – ተማርን አልተማርን፣ ታሪክ ኖረን አልኖረን ጉዳያችን አይደለም!
ታውቃላችሁ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ ወዳጆች የመሆን አቅም ይኑረን እንጂ፣ ዘመድ ኖረን አልኖረን፣ ከሚነገርለት ሐረግና ዘር መጣንም አልመጣን፣ ሀብታም ሆንን ድሃ – ጉዳያችን አይደለም!


ታውቃላችሁ፣ ለእግዚአብሔር ሰው ዋናው ጉዳይ ታሪክ ይዞ መገኘት ሳይሆን ቃል ይዞ መገኘት ነው! ወገኖች ሆይ፣ ቃል ያለው እግዚአብሔር ሰው፣ ሰማያትን ዘግቶ ሰማይን ለመክፈት ሥልጣን ይኖረዋል! ቃል ያለው ሰው ደመናትን አዝዞ ዝናብ ሊያዘንብ ሊያቆም፣ ሥልጣን ይኖረዋል! ቃል ያለው ሰው – በወሳኝ ወቅት ላይ፣ ቃል ያለው ሰው – በወሳኝ ሰዓት ላይ፣ ሊገለጥ ይችላል፡፡ 


ታውቃላችሁ፣ ቃል ያለው ሰው ታሪክ ባይኖረውም፣ በወሳኝ ወቅት ላይ፣ በወሳኝ ሰዓት ላይ በድንገት ሲነሣ ያልተጠበቀ ታሪክ መሥራት ብቻ ሳይሆን – ያልተጠበቀ ተአምር ሊሠራ ይችላል! ስለሆነም ታሪክ ባይኖረም ቃል ግን ይኑረን! 


-------------------
ዕለታዊ ዲቮሽኑ ጳጉሜ 6 ቀን 2007 ላይ ይጠናቀቃል፡፡ አሁን 62 ብቻ ቀርተዋል፡፡

በዚህ ዓመት ብቻ ዲቮሽኑን የሚከታተሉ 15000 በላይ ሰዎች ከመላው ዓለም ማፍራት ተችሏል፡፡ ዲቮሽኖቹ፣ ሰዎች ወደጌታ እንዲመጡ፣ በርካታዎቹም ከውድቀታቸው እንዲነሱና ከስብራታቸው እንዲጠገኑ፣ በርካታዎቹም እንዲታነጹምክንያት ሆነዋል፡፡ ክብሩን ሁሉ ጌታ ይውሰድ፡፡

እነዚህን ዲቮሽኖች ሰብስቦ በአንድ መጽሐፍ ላይ ለማሳተምና መስከረም 2008 .. ላይ ለአንባቢዎች ለማድረስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በሀገራችን ታሪክ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውንና አንድም ቀን ሳይቋረጥ ዓመቱን ሙሉ ለአንባቢዎች ይቀርብ የነበረውንና በርካታ ነጻ አስተያየቶች ሲሰጡበትና በርካታ ቅዱሳን ሲጸልዩለት ቆይተዋል፡፡

ይህን ታሪካዊ መጽሐፍ፣ የማሳተሚያ ወጭ በገንዘብ ለመደገፍ የምትፈልጉ፣ ወይም ገፆች በመግዛት በመጽሐፉ ላይ የድርጅታችሁንና የአገልግሎታችሁን ዓላማዎች ለአንባቢያን ማስተዋወቅ የምትፈልጉ፣ ምርቶቻችሁንና ማናቸውንም አገልግሎታችሁን በማስታወቂያ ማስተላለፍ የምትፈልጉ በሀገር ውስጥና ውጭ የምትገኙ ወገኖች ሁሉ ባሉን ውስን ገጾች ውስጥ አስቀድሞ በመያዝ ራዕዩን መደገፍ ትችላላችሁ፡፡ ለተጨማሪ መረጃ፣ በሞባይል 911-678-158 መደወል ይቻላል፡፡

ዓመቱን ሙሉ አብራችሁን ለነበራችሁ ወገኖች ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በዲቮሽኑ መቆም ልባችሁ ለሚያዝንብን ወገኖች ደግሞ ከፍ ያለ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ፡፡ / ተስፋሁን ሐጢያ

No comments:

Post a Comment