ዲቮሽን 248/07፥ ቅዳሜ፣ ግንቦት 8/07
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
(በዶ/ር በቀለ ብርሃኑ)
የእግዚአብሔርን ሥራ አናውቅም
“የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፣ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ሥራ አታውቅም”(መክብብ 11፡5)
የእግዚአብሔርን ሥራ አታውቅም እግዚአብሔር የሚሠራባቸው መንገዶች እጅግ ልዩ ልዩ ናቸው፡፡ እሱ እንዲህ ነው የሚሠራው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አሁን ያለንን ማንነት ለመሥራት የተጠቀመባቸው ብዙ ሁኔታዎችና ሰዎች ይኖራሉ፡፡ እንዳውም አንዳንዶቹ ሰዎች በምድር ላይ የሉም ይሆናል፡፡ ቢሆንም ሰዎቹ በኑሮ ጎዳናችን ላይ ለእኛ መሠራት ምክንያት ሆነው አልፈዋል፡፡ ጌታችን የቱንና ምኑን ለሥራው እንደሚጠቀም አናውቅምና፣ ጥበቡና አሠራሩ ከፍ ያለች ናትና፣ ነገሩ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ስናይ፣ ከማመስገንና ከመደነቅ በቀር ሌላ ቋንቋ አይኖረንም፡፡ አዎ፣ እሱ ነገሮችን እንዴት እንደሚያቀናጅ አናውቅም፡፡
ጌታችን በሕይወታችን ሞኝ የሚመስሉ፣ አእምሮን የማያሳምኑና ጥበብ የሌለባቸው የሚመስሉ ነገሮችን ይጠቀማል፡፡ ነገር ግን ሁኔታዎቹን አልፈን ወደ ኋላ ስናያቸው እጅግ ጥበብ የሞላቸው አሠራሮች እንደ ነበሩ እናስተውልና ከመደነቅ በቀር ሌላ አፍ አይኖረንም፡፡ ለሥራውና ላሰበው ዓላማ ሲፈልገን፣ አስቀድሞ ወደ ወኅኒ ቤት ለተወሰነ ጊዜ ሊወረውረን ይችላል፡፡ በመከራ ውስጥ እንድናልፍ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ውስብስብ ባሉ ነገሮች ውስጥ እንድንጓዝ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ በብዙዎች እንደተመሰከረው፣ አሠራሩ ብዙም አይገባምና፣ በእምነት መቆም ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል “የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፣ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ሥራ አታውቅም”(መክብብ 11፡5) ብሎ ይናገራል፡፡አዎ፣ ይህ እውነት የበራለት ሰው ከቃሉ ጋር በመስማማት “አላውቅም” ነው የሚለው እንጂ ሌላ ግርግር አይኖረውም፡፡ እስቲ የራሳችሁን ሕይወት እዩት፣ ኧረ ለመሆኑ ምንስ እናውቃለን? ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስበው በሕይወቴ ብዙ የምደነቅባቸው ነገሮች ሞልተዋል፡፡ ለምሳሌ ይችን ጽሑፍ እየጻፈ ያለው ሰው ከዛሬ 16 ዓመት በፊት ነጭ ዱርዬ የነበረ ሰው ነው፤ ይገርማል!
ሌላ አንድ በቅርብ ያስደነቀኝን አሠራሩን ባጭሩ ልመስክርላችሁ፡፡ መሥሪያ ቤቴ ልደርስ ትንሽ ሲቀረኝ፣ የትራፊክ መብራት ጋ ቀስ እያልኩ መኪናዬን አብርጄ እያቆምኩ ሳለሁ፣ ከኋላ አንድ መኪና በኃይል ተንደርድሮ መኪናዬን በኃይል ገጫት፡፡ መኪናዬም በጌታ ምሕረት፣ ወደ ፊት ትንሽ ተንሸራታ ቆመች፡፡ የመኪናዬ ጩኸት ለጊዜውም ቢሆን እጅግ አስደንግጦኝ ነበር፣ ምንም እንኳ የደረሰብኝ ጉዳት ባይኖርም፡፡ ሰውየው ጥሩ የመኪና ኢንሹራንስ ነበረውና፣ መኪናዬ በሚገባ አንዲሠራልኝ ብሎ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሰዎች ጋር በስልክ አገናኘኝ፡፡
ባጋጣሚ መኪናዬ ሲመታ፣ አስቀድሞ ልል የነበረ ቦታ ላይ ስለተመታ ይመስለኛል (እንደዚያም እገምታለሁ፣ ምክንያቱም መኪናው አርጅቷልና)፣ የመኪናው ጭስ ማውጫ ሙሉ በሙሉ ዝርግፍ ብሎ ወደቀ፡፡ ከዚያ ይህ ኢንሹራንስ ካምፓኒ መኪናዬን ጥሩ ጋራጅ ወስዶ በጥሩ ሁኔታ ካሠራልኝ በኋላ፣ መኪናውን ለማሠራት ከተመደበው ብር የተረፈውን በርከት ያለ ብር ለሻይ ይሁንህ ብሎ ለግሶኝ፣ በብዙ ፈገግታ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡
እግረ መንገዴን የምነግራችሁ በዛው ሰሞን ያ ያገኘሁት ገንዘብ ለምፈልጋቸው አስቸኳይ ጉዳዮች እንደ ፈጥኖ ደራሽ ነበር የሆነልኝ፡፡ ያንን የላላ የመኪና ክፍል በግሌ ማሠራቴ አይቀርም ነበርና፣ ከብዙ ወጪ በመትረፌ አምላኬን ከፍ አድርጌ ነው ያመሰገንሁት፡፡ እስካሁን ክስተቱን ባሰብኩት ቁጥር ይገርመኛል፤ ያስደንቀኛልም! እስቲ እንደዚህ ዙሪያ ጥምጥም ከሚሄድ ለምን በቀጥታ የምፈልገውን ገንዘብ አይሰጠኝም ብዬም ማሰቤ አልቀረም፡፡ ለነገሩ በሱ ሥራ ምን አገባኝ!
ዮሴፍ ወደ ኋላ ያሳለፈውን ትልቁን ስዕል በመንፈስ አስተውሎ ለበደሉት፣ ጉድጓድ ውስጥ ለጣሉትና አውጥተውም ለሸጡት ወንድሞቹ እንዲህ ነበር ያላቸው፡- “አትፍሩ፤…..እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው” (ዘፍጥረት 50፡20)፡፡ የሚገርም የምሕረት ቋንቋ! ዮሴፍ እንዲህ እንዲል ያበቃው ምን መሰላችሁ? መለኮታዊ ንድፉ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ፣ በሚገባ ስላየውና ስለ ተረዳው ነው፡፡ መቼም ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ባለበት ሰዓትና ወኅኒ ቤት እያለ እንዲህ እንደማይል እገምታለሁ፡፡
ታዲያ ከኛ የሚጠበቀው ምንድን ነው? ሁሉን የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ሥራ አናውቅምና፣ ታማኝነቱን አምኖና ተደግፎ መቆም ብቻ ነው ከኛ የሚያስፈልገው! አዎ፣የኛ ኀላፊነትና ድርሻ፣ በእምነትና በትዕግስት በፊቱ መሆን ነው፡፡ በርጋታ እየተጠባበቁ፣ መድኃኒቱንና መፍትሔውን እየናፈቁና ተስፋ እያደረጉ ፊቱን መፈለግ ነው፡፡
በዚህ ጊዜ ሥፍራችንን ሳንለቅ፣ ሰዋዊ አካሄዶችን ሳናምታታና ሰከን ባለ መንገድ እሱን መጠበቅ አስተዋይነት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ባለ ማስተዋልና ባለ መረጋጋት ከፍ ያለችውን በረከቱንና ፍቃዱን ልናጣ እንችላለንና ነው፡፡ ቃሉ “ባንተ ታምናለችና ባንተ ለምትደገፍ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ” (ኢሳይያስ 26፡3) ይላልና ባይገባንም በመታመን ሳንናወጥ እንጠብቀው!
No comments:
Post a Comment