ዲቮሽን 250/07፥ ሰኞ፣ ግንቦት 10/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ምርጫ 2007 እና – ጴንጤዎቹ!
የፊታችን እሁድ፣ ግንቦት 16 ቀን
2007 ዓ.ም. 5ኛው ሀገር አቀፋዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ይደረጋል፡፡ በዚህ ምርጫ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን በአመራር የሚያገለግሉ
የሕዝብ እንደራሴዎች ይመረጣሉ፡፡ ይህ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሀገሪቱን ዜጎች ሁሉ የሚወክል በመሆኑና በዚህች ሀገር ውስጥ የሚገኘውን
እያንዳንዱን ኅብረተሰብ የሚነካ በመሆኑ፣ የዚህ ሣምንቱን ዲቮሽን በምርጫው ዙሪያና በአንዳንድ ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥቂት አስተያየቶች
ለመስጠት አስቤያለሁ፡፡
ማሳሰቢያ፣ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የማንም
የፖለቲካ ድርጅት አባል አይደለም፡፡ የሚቀርቡ አስተያየቶችም ሆኑ አቋሞች የግለሰቡ እንጂ የማንንም የእምነት ተቋም አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የአስተሳሰቦቹ ዋና ዓላማ፣ ለሀገር ሰላምና ልማት የሚጠቅሙ የጋራ እሴቶች እንዲጎለብቱ ለማበረታታት ብቻ ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ስለ ጴንጤዎች ማንነት በቂ ግንዛቤ የሌላቸው አንዳንድ ግለሰቦች፣
እኛ ጴንጤዎች ለአገራችን እንደማንቆረቆር ከማሰብም አልፈው እንደ ሁለተኛ ዜጎች አድርገው የመመልከት አባዜ ይጠናወታቸዋል፡፡ በእርግጥ
ዘላለማዊው፣ እውነተኛውና መንፈሳዊው ሀገራችን በሰማይ ነው! ቢሆንም፣ በዚህች ሀገር ውስጥ በአካለሥጋ እስካለን ድረስ፣ የሰላምና
የፍቅር እንዲሁም ለሀገር ልማት ከሌሎቹ ዜጎች የተሻለ እንደምንቆረቆርላት ሁሉም አካላት ማወቅ ይገባቸዋል፡፡
ከደርግ ውድቀት ወዲህ ስለ ጴንጤዎች ያለው አስተሳሰብ በደርግ ዘመነ መንግሥት ከነበረውና በንጉሠ ነገሥቱ ዘመነ መንግሥት
ከነበረው ጥቂት መሻሻሎች ያለው ቢሆንም፣ አሁንም በብዙዎች ዘንድ ስለ ጴንጤዎች ጤናማ አስተሳሰብ አለ ለማለት አያስችልም፡፡ ይህ
በሽታ የሚታየው በተራ ግለሰቦች ደረጃ ብቻም ሳይሆን፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የሀገር አመራር አካላት ዘንድም ጭምር ነው!
የዚህ አስተሳሰብ ዋናው ችግር ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የቆየው ጴንጤዎችን
እንደ ሀገሪቱ ዜጎች እኩል መብት ተጠቃሚ እንደሆኑ አድርጎ ያለመቁጠር፣ የማግለልና ሕገመንግሥቱ በግልጽ ያስቀመጣቸውን ሐይማኖታዊ
መብቶች እንዳይጠቀሙ ሆን ብሎ የመጨቆን ወይም የማስተጓጎል አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ችግር ግን ተቋማዊ ሳይሆን፣ ሥልጣናቸውን መከታ
በማድረግ የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ግለሰቦች የሚያራምዱት አስተሳሰብ ነው፡፡
ስለሆነም፣ ሁሉም ጴንጤዎች በዚህ ምርጫ
ላይ በበነቂስ በመውጣትና ለሀገር ሰላምና ልማት ቅድሚያ ትኩረት ያለውን ፓርቲ በመምረጥ፣ ለሀገር መሪዎች ምርጫ የምንሰጠው ትኩረት
የቤተክርስቲያን መሪዎችን ለመምረጥ ከምንሰጠው ትኩረት
ያላነሰ መሆኑን ማሳየት ይገባናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ጴንጤዎች ከዚህ ቀደም የምናሳየውን ገለልተኝነት በማስወገድ በዚህ ምርጫ
ላይ በበነቂስ ወጥተን ሰላማዊ ምርጫ ማድረጋችን የሚያስተላልፈው ሌላ መልዕክትም አለ – ‹‹ጴንጤዎቹም እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሁሉ ሕገመንግሥታዊ
መብታቸውን ለማስከበር መንቀሳቀስ ጀምረዋልና ተጠንቀቁ!›› የሚል፡፡
ዘላለማዊው ሀገራችን በሰማይ ቢሆንም፣ በዚህች ሀገር ውስጥ በአካለሥጋ እስካለን ድረስ፣ የሰላምና የፍቅር እንዲሁም ለሀገር
ልማት ከሌሎቹ ዜጎች የተሻለ እንደምንቆረቆርላት ለሁሉም አካላት ማሳየት ይገባናል፡፡ ስለሆነም፣ ይህ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ፣ ሁላችንም በጸሎትና በማናቸውም ሰላማዊና
ጤናማ መንገዶች በመንቀሳቀስ በሀገራችን ያገኘነውን የተረጋጋ ሰላምና የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ ድርሻችንን እንድንወጣ ጥሪዬን
አስተላልፋለሁ፡፡
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!
No comments:
Post a Comment