Saturday, May 16, 2015

ሸክማችሁ የከበደ ኑ

ዲቮሽን 246/07፣ ሐሙስ፣ ግንቦት 6/07
(በወንድም ጌታሁን ሓለፎም)

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ኑ ወደ እኔ እኔም አሳርፋችሁአለሁ (ማቴ 11፡-28)

ትዝ ይለኛል ከረጅም ዘመን በፊት ፤ ወደ ጓደኟዬ ሰፈር በሄድኩኝ ቁጥር መንደራቸው ውስጥ አንድ በተደጋጋሚ የሚያጋጥመኝ ትእይንት ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው አንዲት በ15 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ልጃገረድ በእጇ ገመድ አንጠልጥላ በከፍተኟ ፍጥነት ቁልቁለቱን ትሮጣለች ፡፡ ከኋላዋ ደግሞ በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች “ያዙዋት፤ ያዙዋት ያዙዋት” እያሉ እየተጯጯሁ ያባርሯታል፡፡ ልጃገረዲቷ ስትሮጥ ከሩቅ ለሚያት ሰው ቀሚሷን ነፋስ በአየር ላይ ብ…ን…ን …ሲያደርገው ሁኔታዋ ራሱን የቻለ ትርኢትን ይፈጥራል፡፡

የሩጫዋን ፍጥነት ላስተዋለው ሰው፤ ከኋላዋ የሆነ ሰው የሚያባርራት ይመስላል “ያዟት፤ ያዟት……አካባቢው ሁሉ ይታመሳል፡፡ ከግርግሩ መሃል በተሻለ ፍጥነት የሚሮጡ ወጠምሻ ጎረምሳወች ፈትለክ ብለው ይሮጡና ልጂቷ ዘንድ ደርሰው እንቅ ያረጉዋታል፡፡

እጆቿን ጥርቅም አድርገው የያዟትን ጎረምሶች ሲቃ እና እልህ በያዘው ድምጽ እምባ በተሞሉ አይኖቿ አይን አይናቸውን እያየች “ለምን፤ ለምን አትተውኝም” እያለች ትማጸናለች፡፡

እንደኔ ነገሩ ያልገባቸው አላፊ አግዳሚው ደግሞ የተፈጠረውን ግርግር መንስኤውን ለማወቅ እየጓጉ ወደሚተራመሰው ሰው ጠጋ ብለው “ምንድን ነው፤ ምንድን ነው ነገሩ ምንድን ነው” እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ ታዲያ የሚገርመው ነገር ሁል ጊዜ በዚህ ትእይንት መሃል “ምንድን ነው” እያለ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማወቅ ለሚጓጓ አላፊ አግዳሚ መግለጫ የሚሰጡ አንዲት ጠና ያሉ እናት አሉ“ እች ቤተሰብ አሰዳቢ እስቲ አሁን ምን ይባላል እናንተ ሆዬ ጎረምሳ ቤት ካልገባሁ ሞቼ እገኛለሁ ብሎ ድርቅ ማለት? እሱ እንደሆነ አልፈልግሽም ብሏል ሆቸው ጉድ ወላድ በድባብ ትሂድ እንጅ ሌላ አትፈልግም? አተወውም እንዴ? ሆሆሆ ቤተሰቦቿ እኮ ተቸገሩ በየቀኑ እሷን ማሯሯጥ! እግዚዮ፤ እግዚዮ አቤት ስምንተኛው ሺ” ይላሉ፡፡

ይህች ኮረዳ ከአቅሟ በላይ የሆነ የራሷ ሸክም ነበራት፡፡ ልትቆጣጠርው፤ ልትሸከመው ያልቻለችው የሽክሙ፤ የጭነቱ ልክ ይሉኝታ፤ ሰው ምን ይለኛል የማያስብል ቁዋጥኝ የሚያክል ነበር፡፡ በቃ አልቻለችም! ወጣቱን ካላገኘችው ጥፊ ጥፊ ይላታል እናም ወቅት ጠብቃ ሰው አየኝ አላየኝ ብላ ዛፍ ላይ ጥልጥል ልትል ድንገት ፈትለክ ትላለች፡፡

ከአዳም የተወለደ ሁሉ በዚህች ምድር ላይ ሲኖር እንደሁኔታው ይለያይ እንጅ የራሱ የሆነ ሸክም አለው፡፡

ያንዳንዱ ሰው ሸክሙ ትንባሆው መጠጡ እና ጫቱ ግልሙትናው ናላውን አዙሮት “እኔ ያንች ድውይ ያንች በሽተኛ ሲስሙኝ የምሳም ሲያቅፉኝ የምተኛ” የሚለው ዘፈን በየመንገዱ እየተገዳደረው እና ጠልፎ እየጣለው ከትዳሩ ከኑሮው ጎሎ ተቸግሮ ሊሆን ይችላል፡፡

ሃብታሙ ሰው ገንዘቡ አዱኛው ተትረፍርፎ እያለ አንድ በገንዘቡ ኃይል ሊያሸንፈው ያልቻለው እንቆቅልሽ፤ የከበደ የራሱየሆነ ሸክም፤ የራሱ የሆነ ችግር ቁዋጠሮ ሊኖረው ይችላል፡፡

የተማረው የተመራመረው እሱም ቢሆን የራሱ የሆነ ጥያቄ ምርምር ሸክም ቁዋጠሮ አለው ድሃው፤ ሴቱ፤ ወንዱ ……ሁሉም ባለ ቀንበር ነው፡፡ አንዳንዱ ሰው ሁሉ ተሳክቶለት ሁሉ ሞልቶት የጤናው ነገር ሰቀቀን ሆኖበታል፡፡

ሁሉም ታድያ ለሆነበት ነገር መፍትሔ ፍለጋ ይለፋል፥ ይደክማል፥ ይኳትናል፥ ሌላ ችግር ሌላ ሽክም !!! እንግዲህ ይህንን የሰው ልጅን ጭንቀት የሚያውቅው ጌታ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደኔ ኑ፤ አትልፉ ድካማችሁን ላቀል የምችል እኔ ብቻ ነኝ” እያለ ይጣራል፡፡

በነገራችን ላይ ይሄ ሁሉ ጴንጤ ቆስጤ ከዚህ ቃል ጋር ነገሩ ስለተገጣጠመ ነው ወደ ጌታ መጥቶ ሸክሙ የተቃለለለት እፎይ ያለው፡፡

ዛሬ በልዩ ልዩ ችግር እና ጭንቀት ጥያቄ እንዲሁም ሸክም ያላችሁ ይህ ጥሪ ይድረሳችሁ፡፡ ሸክሙ እንዳያጠፋችሁ እንዳያጎሳቁላችሁ ይህ ጥሪ ይድረሳችሁ፡፡ ሸክማችሁን ሊያራግፍ ለሚችልና ከሽክማችሁ ለሚያሳርፋችሁ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ሸክማችሁን ስጡት!

No comments:

Post a Comment