ዲቮሽን 247/07፣ አርብ፣ ግንቦት 7/07
(በወንድም አበባዬ ቢተው)
(በወንድም አበባዬ ቢተው)
ሕይወት እንዲበዛልን
"ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።" (ዮሐ 10:10)
የእግዚአብሄር ዓላማ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ እና ይህም ሕይወት እንዲበዛልን ነው። ከእግዚአብሄር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ኖሮን ወደ ተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት እና ሰላም እንድንገባ ጭምር ነው። በክርስቶስ ሞት ከእርሱ ጋር ታርቀንና በትንሳኤው አዲስ ሕይወት ተቀብለን እንድንመላለስ ነው። (ሮሜ 5፥10) የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምክንያት ይህ ነው።
ወገኖቼ ከዚህ ዉጭ የሆነ ነገር ሁሉ ሌባ ነው። ከእግዚአብሄር ሳይሆን ከሌላ ነው።
ክርስቶስን እና የተቀበልነውን የዘላለም ሕይወት የማያጎላ ሁሉ ሊሰርቀን የሚመጣ ሌባ ነው። ክርስቶስን ማዕከላዊ ያላደረገ ሁሉ ወደ ሕይወት ዕድገት የማያመጣ የጥፋት መስመር ነው። ዓይናችንን ከመስቀሉ እና ከትንሳኤው ዘወር እንድናደርግ የሚያደርግ ነገር ሁሉ ከሕይወት በረከት ሊያጎድለን የመጣ መቅሰፍት ነው። እናስተውል።
ስለዚህ ወገኖቼ ዙሪያችንን እንይ። የምንማረውን የሚያስተምሩንን እና የምናስተምረውን እናስተውል። የምንሰማውን እና የምናሰማውን እንፈትሽ። ክርስቶስን ያገለለ ከሆነ ዉሎ እያደረ ሕይወታችን መዳከው አይቀርም። ወደ ጥፋት መቃረባችን እና ከተትረፈረፈ ሕይወት መጉደላችን ፈፅሞ አይቀርም። በሕይወታችን ክሳት እና ፍሬ አልባነት መምጣቱ አይቀርም።
ኢየሱስ ዋና ነው። በእርሱ የተትረፈረፈ ሕይወት አለ። ስለዚህ የሁሉ ነገራችንን ማዕከላዊ ስፍራ ሊይዝ ይገባል። ያኔ ሕይወታችን በበረከት ይሞላል፥ በማያቋርጥ እድገት ውስጥም ያልፋል።
"ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤" (ሮሜ 5:10)
ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋል ይሰጠን!
No comments:
Post a Comment