Wednesday, May 13, 2015

የቅዱሳንን ልብ – ማሳረፍ!



ዲቮሽን 245/07፣ ረቡዕ ግንቦት 5/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)

የቅዱሳንን ልብ – ማሳረፍ! 

የቅዱሳን ልብ በአንተ ስራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ፥ በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና (ፊልሞና 1፡7)።

አንዳንዴ የወገኖች ልብ በወገኖች ሲቆስልና ሲደማ ይታያል! አንዱ ሌላውን ሲያስለቅስ፣ ሲያስነክስና ሲያስነካክስ ይታያል! ወገኖች ወገኖችን ሲጎዱ፣ ሲያሳድዱና ሲያዋርዱም ይስተዋላል! አንዱ ሌላውን ሲሰብር፣ ሲበድልና ሲሰቅል፣ ሲወጋ፣ ሲገድልና ሲቀብርም ይታያል!

ወገኖች ሆይ፣ ከፊልሞና እንማር! ፊልሞና በሚሠራው ስራ የቅዱሳንን ልብ ያሳረፈ ሰው ነበር፡፡ በሚሠራው ስራ የቅዱሳንን ልብ ማሳረፍ በመቻሉና ለቅዱሳን በሚለግሰው ፍቅር ለብዙዎች ብዙ ደስታንና መጽናናትን ለመስጠት የቻለ ጻድቅ ሰው ነበር፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ በሚሠሩት ሥራ የቅዱሳን ልብ እያሳረፉ ነው ወይስ እረፍት እየነሱ? በሚሠሩት ሥራ ለብዙዎች ብዙ ደስታንና መጽናናትን እየሰጡ ወይስ ደስታንና መጽናናትን እየነፈጉ?

ወዳጄ ሆይ፣ በአገልግሎትዎ የቅዱሳንን ልብ እያሳረፉ ነው ወይስ እረፍት እየነሱ? በአገልግሎትዎ ለብዙዎች ብዙ ደስታንና መጽናናትን እየሰጡ ወይስ ደስታንና መጽናናትን እየነፈጉ?

ወዳጄ ሆይ፣ ከፊልሞና ይማሩ! በሚሠሩት ስራ የቅዱሳንን ልብ ማሳረፍ እንዲችሉ ከሁሉ አስቀድመው ራስዎትን ለጌታ ያቅርቡ! ራሳቸውን አስቀድመው ለጌታ ከሰጡ፣ በሚሠሩት ሥራ የቅዱሳንን ልብ ከማሳረፍም አልፈው፣ ለብዙዎች ብዙ ደስታንና መጽናናትን ለመስጠት ጸጋና አቅምን ይቀበላሉ!

No comments:

Post a Comment