Thursday, May 21, 2015

የጴንጤ ፖለቲካ = ፊሊያ + ኮይኖኒያ !



ዲቮሽን 253/07 ሐሙስ፣ ግንቦት 13/07
(
በፓ/ ተስፋሁን ሐጢያ)


የጴንጤ ፖለቲካ = ፊሊያ + ኮይኖኒያ !

ስለፖለቲካ ያለን መረዳት የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ወንጌል ሰባኪ እንጂ የፖለቲካ ሰውም አይደለሁም፡፡ ስለሆነም፣ በዚህ ነጥብ ላይ መከራከር አልፈልግም፡፡ ነገር ግን በግሪኮቹ ፈላስፎች በፕሌቶም ሆነ አርስቶትል ትርጉሞች፣ እንዲሁም በዛሬውም ዘመን በመላው ዓለም እየተሠራበት ያለውን ስለ ‹‹ፖለቲካ›› የተሰጠው ቀላልና ግልጽ ትርጉም፣ ‹‹መልካም ኑሮ›› ማለት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይህ ‹‹መልካም ኑሮ›› መገለጫው ደግሞ በሰዎች መካከል ያለ የእርስ በርስ ወዳጅነት (ፊሊያ) ሲሆን፣ የወዳጅነት መለኪያው ደግሞ በሰላምና በመቻቻል አብሮ መኖር (ኮይኖኒያ) ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የአንድ ሀገር ፖለቲካ ‹‹መልካምነቱ›› ወይም ‹‹ኢ-መልካምነቱ›› የሚፈተሸው የምንወድደው ፓርቲ ስለሆነና ስላልሆነ ሳይሆን፣ በአንድ ሀገር ዜጎች መካከል እኩልነትና ወዳጅነት እንዲሁም በሰላምና በመቻቻል አብሮ ለመኖር በሚያደርገው ጥረት ይመስለኛል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥም ጉሮሮአችን እስኪሰነጠቅ በየጊዜው እየጮኽን የምንሰብከው እውነት ቃል በቃል ማለት ይቻላል ይኸው ነው!

ወገኖች ሆይ፣ በሰዎች መካከል የወዳጅነት መንፈስ ከጠፋ በሀገሪቱ ውስጥ ጤናማ ፖለቲካ ሊኖር አይችልም፡፡ ጤናማ ፖለቲካ በሌለበት ሀገር ደግሞ ‹‹መልካም ኑሮ›› ማየት ዘበት ይሆናል፡፡ በቤተከርስቲያን ውስጥ ያለውም ይኸው ነው! በሰዎች መካከል የወዳጅነት መንፈስ ከጠፋ ቤተክርስቲያንም አብራ ትፈርሳለች፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ አይተናል፡፡

ወዳጆቼ ሆይ፣ ይህን አስተሳሰቤን ላለመቀበል ‹‹ቤተክርስቲያንን የገሀነም ደጆች አይችሏትም›› ተብሎ ተጽፏልና ቤተክርስቲያን አትፈርስም በማለት አትከራከሩኝ፡፡ በአውሮፓ ሀገሮች ለምዕተ ዓመታት ገናና የነበሩ በርካታ የፈራረሱ ቤተክርስቲያኖችን በሥጋ ዓይኖቼ ተመልክቻለሁና ሌላ ምስክር አልሻም!

ወገኖች ሆይ፣ በመጀመሪያዎቹ ምዕተ ዓመታት በሰሜን አፍሪካና በእስያ በርካታ አብያተክርስቲያናት ነበሩ፡፡ እነዚያ አብያተክርስቲያናት ዛሬ መታሰቢያቸውም ደብዛቸውም ጠፍቷል፡፡ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም ሁለቱን ብቻ መጥቀስ ይበቃል፡፡ አንደኛው፣ በቤተክርስቲያን ምዕመናን መካከል በልዩ ልዩ አስተምህሮች ምክንያት አለመግባባትና አንዱ ሌላውን ማሳደድ ሲሆን፣ ሁለተኛው፣ የእስልምና እምነት መስፋፋትና ክርስትና እምነትን ከምድር ገጽ የማጥፋት ዋነኛ ተልዕኮ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በብዙዎች ዘንድ ‹‹የክርስትና እምነት በስደት ውስጥ ይጠነክራል›› የሚለው አስተሳሰብ ሥር የሰደደ ነው፡፡ ይህን አስተሳሰብ መቃወም አልፈልግም፡፡ ነገር ግን፣ የክርስትና እምነት እንቅስቃሴ ሰላማዊና የተረጋጋ ፖለቲካዊ አስተዳደር ቢያገኝ የተሻለ ለመስፋፋት ዕድል የማግኘቱ ነገር ደግሞ ክርክር የማያሻው ነው፡፡ ለዚህም ማሳያው እንደ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ያሉ አካባቢዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ወንጌልን ከዳር እስከዳር ለማድረስ ከ30 ዓመት በላይ አልፈጀም፡፡

በተቃራኒው ደግሞ፣ ወንጌል ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል የደረሰው ከአውሮፓውያኑ የተሐድሶ እንቅስቃሴ እኩል በተመሣሣይ ጊዜ ሲሆን፣ ክፍለዘመኑ ሁሉ በየጊዜው ይካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት በኅብረሰተሰቡ ዘንድ የተረጋጋና ሰላማዊ ለወንጌል ሥራ እንቅስቃሴ ምቹ ምህዳር ሳይፈጠር ቀርቷል፡፡ እንደ ፒተር ሐይሊንግ፣ እነ ሳሙኤል ጉባትና ሌሎቹም በርካታ አውሮፓዊያን የአውሮፓውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ እንደወረደ ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ ቢመጡም በወቅቱ በነበረው ምህዳር የተነሣ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ዛሬም ቢሆን በኢትዮጵያ ክልሎች ለምሳሌ በአፋር፣ በሶማሌ፣ በአርሲ ባሌና በሰሜኑ አካባቢዎች የወንጌል እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሲሠራ የማይስተዋልበት በጣም ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ የተጠናከረ የወንጌል እንቅስቃሴ እንዲኖር የተረጋጋ ሰላምና የፖለቲካ አስተዳደር ያስፈልጋል ብዬ የምከራከርበት ምክንያቱ ይኼ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በእኔ አተያይ፣ ያለፉት የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓቶች፣ አንዱን የኅብረተሰብ ክፍል አለቅጥ ጠቅመው፣ ሌላኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ አለቅጥ የመጉዳት አካሄድ ነበራቸው፡፡ ይህን እውነታ ለኢትዮጵያዊያን ለማስረዳት የታሪክ ሰነዶችን ማጣቀስ ፌዝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እኛ በሀገራችን የነበረውን ሁኔታ ስለምናውቀው አስረጅ አያሻንምና ነው፡፡ ሐሳቤን ለማብራራት ግን ምሣሌ መጥቀስ ይበቃል፡፡

ያለፉት የሀገራችን የፖለቲካ ሥርዓቶች፣ በኢትዮጵያ የነበሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሐይማኖቶች፣ እርስ በእሳቸው እንዲቀባበሉና እንዲከባበሩ ሲደረግ አልነበረም፡፡ አንዱን ተቀብሎ ሌላውን የመግፋት፣ አንዱን የመንግሥት ሌላውን የጫካ አድርጎ የመውሰድ ነገሮ ነበሩ፡፡ ከዚህም የተነሳ በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የእርስ በእርስ ጥላቻና አለመቀባበል ነበር፡፡ በሐይማኖት ተቋማት ዘንድም መንግሥታዊ ተቀባይነት ያለው በሌለው ላይ ጡንቻውን ሲያሳርፍ፣ ሲያሳድድና ሲያንገላትታ ነበር፡፡

እንደ ሐይማኖት መሪ፣ ሐሳቤ ተቀባይነት አገኘም አላገኘ እውነታውን በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርብኛል፡፡ በሐገራችን የሐይማኖት እኩልነት የተረጋገረጠው፣ የብሔረሰቦች እኩልነት በይፋ የታወጀው በአሁኑ ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን እውነት አለመቀበል የሚያመለክተው የአስተሳሰብ ልዩነት መኖሩን ሳይሆን የአስተሳሰብ ችግር መኖሩን ይሆናል፡፡ የአስተሳሰብ ልዩነት ጤናማ ሲሆን፣ የአስተሳሰብ ችግር ግን ጤነኛ አይደለም፡፡

እውቀት እየጨመረ ይሄዳል ብዬ ባምንም፣ ማንም ሰው ስለፖለቲካ ያለው ግንዛቤ ከፖለቲካ ፈጣሪዎቹ ከፕሌቶና አርስቶትል ልቆ መሄድ ችሏል ብዬ ለማመን ይቸግረኛል፡፡ ካለም ይቅረብና እንስማው፡፡ ‹‹ሪፐብሊክ››ን በደንብ ያነበበ ሰው በእውነት ፖለቲካን ከሐይማኖት ለያይቶ ለማስቀመጥ ይቸግረዋል፡፡ የዚህም ምክንያቱ የእውነተኛ ፖለቲካ ዋና ዓላማ በሰዎች መካከል የወዳጅነት፣ የወንድማማችነትና የእኩልነት መብት በማስፈንና ፍትሐዊ ሥርዓቶችን በማስፈን ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ኑሮ እውን ማድረግ ስለሆነ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ይህ  አስተሳሰብ ከመንፈሳዊ አስተምህሮአችን ጋራ በቀጥታ ይያያዛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም ነው፣ ድምጼን ማሰማት ግዴታ ሲሆንና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ስንደርስ፣ ዛሬ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት ለፖለቲካ አስተዳደሪዎቹም ሆነ ለአብያተክርስቲያናት መሪዎች መልዕክቴን በድፍረት ከማስተላለፍ የማልቆጠበው!

ከዚህም በፊት ያሰማኋቸውን የወሳኝ ወቅት ድምጾቼን ለማስታወስ ያህል፣ (1ኛ) በምርጫ 97 ወቅት ‹‹አይናማዎች እንዳይገጩን›› በሚል ርዕስ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ (2ኛ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ መፈለጋቸውን በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ባደረጉ ጊዜና በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ውይይት በሆነ ወቅትም ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸውን  ቢለቅቁ እንጠቀማለን?›› በሚል ርዕስ በሜታኖያ መጽሔት ላይ፣ ድምጼን አሰምቻለሁ፡፡

መካነኢየሱስ ከኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት ኅብረት ለመልቀቅ በተንቀሳቀሰች ጊዜም ‹‹ቄሶቹ መንታ መንገድ ላይ››፣ በሚል ርዕስ በሜታኖያ መጽሔት ላይ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስቲያናት በነቢያት አገልግሎት ላይ ክርክር በሆነ ጊዜም ሚዛናዊ ያልሆነ አቋም እንዳይወሰድ በተደረጉ ጉባኤዎች ሁሉ ላይ በአካል ተገኝቼ ድምጼን ከማሰማትም አልፎ፣ በዚህ ዲቮሽን መስከረም 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ላይም ‹‹ነቢያትን እንውገር፣ አንግደል!›› በሚል ርዕስ ድምጼን አሰምቻለሁ፡፡ ሌሎችም ለወንጌል አገልግሎት በተዘዋወርኩባቸው ክልሎች ሁሉ የተመለከትኳቸውን ነገሮች ልዩ ልዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም በጽሁፍና በንግግር ወደ ሕዝብ እንዲደርሱ ከማድረግ ተቆጥቤ አላውቅም፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ለእኔ መጋቢነት ማለት በር ዘግቶ መጯጯኽ ብቻ አይደለም፡፡ መጋቢነት የአጥቢያውንና የመላ ሀገሪቱን ሁለንተናዊ ጥቅም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነኩ ነገሮች ሲያጋጥሙም ሆነ ከማጋጠማቸውም በፊት ድምጹን ማሰማት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይም እንደእኔ መንፈሳዊ ጸጋው ነቢይነት የሆነና ጸሐፊ የሆነ መጋቢ፣ የሰው ትችት ፈርቶ አፉን በፕላስተር ቢያስርም የሚሳካለት አይመስለኝም (ደግሞም፣ ራሱን ነቢይ ነኝ አለ ብላችሁ አትውገሩኝ:: አንዳንዶቻችሁ ፓ/ር ሆኖ ፖለቲካ ነክቷልና ፓስተርነቱ ይቅርበት ‹አቶ› ይበቃዋል፣ ያላችሁም እግዜር ይስጥልኝ! እርሱንም አትንፈጉኝ እንጂ ‹አቶ› ለእኔ መቼ አነሰኝ፡፡ ከምንም ከምንም በላይ ‹ወንድም› ብትሉኝ በመካከላችን የተሻለ መቀራረብ እንዲኖር ይረዳናል)፡፡

ከዓመታት በፊት በአንድ የወረዳ ከተማ ውስጥ በተዘጋጀው ኮንፍራንስ ላይ በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተሳትፈው ነበር፡፡ ስለዚህ ግን ምንም ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ በስብከት አገልግሎቴ መሀል ላይ የትንቢት ቃል መጣ፡፡ ‹‹በዚህ ከተማ የሚገኙ በሥልጣናቸው በመባለግ ሕዝብን ያስመረሩ ሙሰኞችን ቢሮዎችና ቤቶች በቅርቡ ባዶ አደርጋለሁ›› የሚል፡፡ ይህንን መልዕክት በድፍረት አስተላለፍኩ፡፡ አስደንጋጭ ሁኔታ ነበር፡፡ ግን ጌያ ተናግሯልና፣ ወዲያውም የበላይ የመንግሥት አካል የወረዳውን ባለሥልጣናት ሁሉ በመገምገም በርካቶቹን ከሥልጣናቸው እንዳባረረ ሰምቻለሁ፡፡ ነቢይነት ማለት እንደ ውሻ በበሉበት መጮኽ ሳይሆን እውነትን በድፍረት መናገር ነው!

የ2007 ምርጫ እንዳይረሳ! ሁሉም ክርስቲያኖች በበነቂስ ወጥተው ለሐይማኖት ብዝሃነትና ነጻነት፣ ለሕዝቦች እኩልነትና ወንድማማችነት እንዲሁም ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጠውን አቅም ያለውን አካል በጸሎት ለይተን በመምረጥ ሕገመንግሥታዊ መብታችንን፣ በተለይም ግራ ጉንጯን ሲመቷት ሌላኛውን ለምታዞረው፣ ሰይፍ ሲያነሱባት፣ ፍቅር ለምትሰጠው፣ ሰያርዷትና ሲሰቅሏት ‹‹የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው›› ለምትለዋና ከሰላምና ፍቅር እንዲሁም ሕጋዊ መስመር ሌላ ምንም አማራጭ የሌላትን ቤተክርስቲያን ለመጠበቅና ለመንከባከብ አቅም ያለውን አካል በጸሎት ለይተን እንምረጥ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

No comments:

Post a Comment