ዲቮሽን 252/07፥ ረቡዕ፣ ግንቦት 12/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
የጴንጤዎች ዕድገት - በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት!
ዛሬም የሞኝ ለቅሶዬን ላልቅስ ፍቀዱልኝ - የቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ጥቅም ተቆርቋሪ እንጂ፥ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፥ የጽሁፌ መልዕክትም የማንንም የእምነት ተቋም የሚወክል አይደለም፡፡
ጴንጤዎች በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ያገኘነውን ያህል ጥቅም በየትኛውም የኢትዮጵያ ሥርዐተ ማኅበር አግኝተን አናውቅም! በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ1987 ዓ.ም ከወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፥ የሐይማኖትና የመንግሥት መለያየት (አንቀጽ 11)፥ የሐይማኖት እኩልነት (አንቀጽ 25)፥ የሐይማኖት፥ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት (አንቀጽ 27)፥ የሐይማኖት ተቋማት የመደራጀት መብት (አንቀጽ 31)፥ እና ሌሎቹም ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው ድንጋጌዎች በግልጽ አስቀምጧል፡፡
እነዚህ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ጥቅም ላይ ውለዋል ብለን ባናምንም፥ ነገር ግን ከዚህ በፊት በሀገራችን ይወጡ ከነበሩ "የይስሙላ" ሕገመንግሥቶች ሁሉ ማለት ይቻላል፥ ይህኛው ሕገመንግሥት ለጴንጤዎች ወርቃማ ዕድሎች ማጎናጸፍ የቻለ ሕገመንግሥት ነው!
ይህም ከመሆኑየተነሣ፥ በዝርዝር ለማስቀመጥ የሚበዙ ጥቅሞች አግኝተናል፡፡ ካገኘናቸው ከብዙ ጥቅሞች መካከል ቢያንስ አንዱን ለመጥቀስ ያህል፡- በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት የታየውን የጴንጤዎቹን ዕድገት መጥቀስ ይበቃል፡፡
እኤአ በ1994 እና በ2007 የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ እኤአ በ1994 ቆጠራ ወቅት ከሀገሪቱ የሕዝብ ቁጥር 10.1% የነበረው የጴንጤዎች ቁጥር በ2007 ቆጠራ ወቅት ወደ 18.6% ደርሶአል፡፡ ይህ ዕድገት በፐርሰንት ሲሰላ 8.5% ነው፡፡ ይህም ማለት በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ሐይማኖቶች ሁሉ ዕድገት ከስምንት እጥፍ የበለጠ ዕድገት ነው!
ወገኖች ሆይ፥ ጴንጤዎች በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ በመቻላቸው ምክንያት እኤአ በ1994 የሕዝብ ቆጠራ ወቅት 61.6% በነበረው የሀገሪቱ የክርስትና ተከታዮች የጋራ ቁጥር ላይ የ1.2% ዕድገት በመጨመር በ2007 ላይ 62.8% እንዲደርስ አስችለዋል፡፡ በዚህም ጴንጤዎች ለሀገሪቱ የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉ ታሪካዊ ውለታ አድርገዋል፡፡ ከእዚህም በላይ በርካታ ትንታኔዎች መስጠት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን በዚሁ መተዉ መልካም ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፥ ባብዛኛው ጴንጤዎች ስንባል ፖለቲካዊ ገለልተኝነት በእጅጉ የሚያጠቃን የኅብረተሰብ ክፍሎች ነን፡፡ በርካታ ወገኖች የፖለቲካ ነገርን ከዓለማዊነት ጋራ በቀጥታ ያያይዙታል፡፡ የኢትዮጰያ ጴንጤዎች ፖለቲካዊ ፎቢያ(መደንግጽ) አለባቸው! በከፍተኛ የፖለቲካ ማዕረግ ላይ ቢሆኑም፥ ፖለቲከኝነታቸው ለእግዚአብሔር ሕዝብ ከፍተኛ ጥበቃና ከለላ ከመስጠት ያልከለከላቸውን ትንቢተ ዳንኤልን ቢያነብቡም፥ መጽሐፈ አስቴርን ቢያነብቡም፥ መጽሐፈ ነህምያን ቢያነቡም የኢትዮጰያ ጴንጤዎች የፖለቲካ ፎቢያ(መደንግጽ) አለባቸው፡፡
በርግጥ ለዚህ ፖለቲካዊ መደንግጽ ሕዝባችንን ያጋለጡት ባለፉት ዘመናት ሀገሪቱን ያስተዳድሩ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን በወረዳና በክልሎች ቢሮዎች ውስጥ የሚገኙ የግል ጥቅም ፈላጊዎች እኩልነታችንን አምነው ለመቀበልና ለመናገር ይተናነቃቸዋል፡፡ ጴንጤዎች ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸው እየታወቀ ማግለልና መድልዎ ይደረግባቸዋል፡፡ ቢሆንም፥ በርካታ ተከታዮቻችን እምነታቸውን ሳይጥሉ፥ ፖለቲካን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ገብተው ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን በማገልገል ላይ መሆናቸውን ግን ማወቅ ይገባናል፡፡
እነዚህ ወገኖቻችን በሀገሪቱ እያበረከቱ ያሉት አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፥ የጴንጤዎቹ ሰላማዊና ሕገመንግሥታዊ ኑሮ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል፥ የወንጌል ሥራና ልዩ ልዩ ሰላማዊ የእምነት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዕድል ልንሰጥ ይገባል፡፡ አለበለዚያ፥ የሚፈልጉትን ሀይማኖታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ለመመሥረት ያለ እንቅልፍ ሲሰሩ የቆዩ ሀይማኖታዊ ፖለቲከኞች ዕድል ያገኛሉ፡፡
አንዳንዶች፥ የሀገሪቱን ሥልጣን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ "ብቻ" እንዲረዳቸው ፖለቲካዊ አጀንዳ አንግበውና ፖለቲካዊ ጭንብል አጥልቀው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ የኛ ቸልተኝነት በዚህ መሰል ዓላማ እየተንቀሳቀሱ ላሉ ኃይሎች ማሸነፍና፥ ከድሉም ማግሥት ጀምሮ ወዲያውም ሕገመንግሥቱን የመለወጥ፥ ቀጥሎም ሐይማኖታዊ መንግሥት መመሥረት፥ ወዲያውም ተከትሎ አገሪቱ በሐይማኖታዊ አክራሪዎችና አሸባሪዎች እጅ የመውደቅ አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል!
ስለሆነም መጻኢ ዕድላችን ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ በዚህ ምርጫ ላይ በበነቂስ ወጥተን ሐይማኖታዊ ነጻነታችንን ቢቻል የበለጠ የሚያቆይልንን፥ ካልተቻለም ባለበት ሊያስከብርን የሚችለውን፥ አቅም ያለውን፥ አካል በጸሎት አስበን እንምረጥ!
በየክፍለ ከተሞቹና በየወረዳዎቹ የሚገኙ የመሬት አስተዳደር ቢሮዎችና ኃላፊዎች በጴንጤዎች ላይ በተለይ ሲያደርሱብን በነበሩ የመልካም አስተዳደር እጦት በደሎች ምክንያት ቂም በመያዝ፥ "አያ በሬ ሆይ፥ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ" እንደተባለው፥ እነዚህን በምርጫ ካርድ ለመቅጣት በማሰብ፥ ጊዜያዊ ችግርን ለማስወገድ አስበን ዘላቂ ችግር በራሳችን ላይ እንዳናመጣ፥ ዋናው የክርስትና እምነት እንቅስቃሴያችንና ሕልውናችን ላይ አደጋ እንዳንጋብዝ አደራ እላለሁ!
"በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፥ ነገር ግን አይዟችሁ፥ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁና"(ዮሐ 16፡33) ያለንን ጌታ በማሰብ፥ የመልካም አስተዳደር እጦት በዚህ ምድር ላይ እስካለን ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊወገድ የማይቻል ጉዳይ መሆኑን በማወቅና፥ ለወደፊቱም ሕጋዊ በሆነ መልኩ መብታችንን ለማስከበር የሚያስችል ዕድል መኖሩን በማሰብ የሚሻለንን መምረጥ ይኖርብናል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
No comments:
Post a Comment