ዲቮሽን 251/07፥ ማክሰኞ፣ ግንቦት 11/07
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ምርጫ 2007 - ለሰላም !
ጴንጤዎች ከአጼው ሥርአተ መንግሥት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ሌሎቹ የሐይማኖት ተቋማት እኩል መብት ሲነፈጉ፥ የአምልኮ ቦታዎቻችን ሲቃጠሉ፥ አማኞቻችን ሲደበደቡ፥ ሲገደሉ፥ በሕጋዊ የአምልኮ ቦታዎቻችን ላይ እንኳ የማምለኪያ አዳራሾች እንዳንሰራ ስንከለከል - ከሰላምና ከሕጋዊ መንገድ ሌላ ምላሽ ሰጥተን አናውቅም! ሌሎች ይህን እንደ ቅሽምና ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ ግን አይደለም፡፡ እኛ ቀሽሞች ሆነን ሳይሆን ሰላም የሕልውናችንና የማንነታችን መገለጫ ስለሆነ ነው!
ወገኖች ሆይ፥ የጴንጤዎቹ ሞዴል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወቱ ከሰላም በተቃራኒ መንገድ ሄዶ አያውቅም፡፡ እኛም ይህንኑ እንከተላለን! እርሱ ስሰላማችን ነውና ሰላምን ብቻ እንከተላልለን!
ታሪክ ቢመረመር፥ አንዳንድ አካላት ሕዝብን ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት ታሳቢ አድርገው ሆን ብለው በየወረዳውና በየክልሉ ቢሮዎች ውስጥ በሚያደርሱብን ግፎች እንኳ ተቋቁመው፥ ጴንጤዎቹ ከሕጋዊ መስመር ውጭ ሕገመንግሥታዊ መብታቸውን በኃይልና በአመጽ ለማስከበር ተንቀሳቅሰው አያውቁም!
ጴንጤ የሰላም ዜጋ ነው! ጴንጤነትና ሰላም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው! ይህ እውነታ ምርምርና ጥናት የማያስፈገው ለሁሉም የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ አካላት የታወቀና በመላው ዓለምም ሁሉ የተመሰረከለት ነው! ጴንጤነት ሰላማዊነት ነው!
በተቃራኒው ደግሞ፥ የአክራሪነትና ጽንፈኝነት መገለጫው የዜጎችን የሐይማኖትና የእምነት ነጻነት በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ (ሕገመንግስት አንቀጽ 27 ለመናድ) እንዲሁም የሐይማኖት እኩልነትን በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ (ሕገ/መንግሥት አንቀጽ 25 ለመናድ) መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም፥ በዚህ ምርጫ ላይ ከምንም ከምንም ነገር ይልቅ፥ ሰላም የሚያስጠብቅልንን፥ ስለሰላም ጮኾ የሚሰብከውንና በተግባርም የሚያሳየንን አካል መምረጥ ይኖርብናል፡፡
በርግጥ የሀገራችን ሰላም በአስተማማኝነት የሚጠብቅልን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው! ነገር ግን ይህ ጌታ ከእርሱ በታች ሀገርን እንዲጠብቁ መሪዎችን አስነስቶ ይጠቀምባቸዋል፡፡ ጠንክረን ከጸለይን ጠንካራ መሪዎች እናገኛለን፥ ደካማ ጸሎት ካደረግን ግን ደካማ መሪዎች ይነሳሉ፡፡ ስለሆነም፥ በእነዚህ በቀሩት ጥቂት ቀናት ለሰላም ቅድሚያ የሚሰጠውን አካል በጸሎት አስተውለን እንድንመርጥ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ!
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ!
No comments:
Post a Comment