Friday, April 17, 2015

ንብ ወይስ ቢራቢሮ!



ዲቮሽን 219/07 አርብ፣ ሚያዝያ 9/07 /
(በወንድም አበባዬ ቢተው)


ንብ ወይስ ቢራቢሮ!

" ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።
ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው። በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው፤ በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና። (መዝሙረ ዳዊት 133:1-3)


የክርስትናን ሕይወት የምንቀበለውና የምንገባዉ በግል ቢሆንም የምንኖረው ግን በህብረት ነው። ምርጫ እና ውሳኔ የምናደርገው በግል ቢሆንም ኑሮው እና በረከቱ ግን በጋራ ነው፡፡
በጌታ ስናምን የተቀበልነው ሕይወት አብረን የምንካፈለው ሕይወት እንጂ ድርሻችንን አንስተን ዘወር የምንልበት አይደለም። የጠጣነው አንዱ መንፈስ(1ቆሮ 1213) አቆራኝቶናል።

  የምንካፈለው ስጋ ወደሙ አንዱን ክርስቶስን በአንድነት ሆነን እንደምናመልክ ያሳያል።
በእኛ በአማኞች መካከል ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት ከስጋ ዝምድና ሁሉ የላቀ ነው። ለስራ ጉዳይ ከተወዳጁ ወገኖች ግንኙነት ሁሉ የላቀ ነው። መንፈሳዊ ነውና። በሕይወታችንንም ትክ የሌለው አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።


እግዚያብሄርም ለዚህ ድንቅ ህብረት በረከትን አዝዟል። የጸጋ ስጦታዎችን አትረፍርፎ ልቅቋል። ይህን ድንቅ ህብረትም ሁልግዜ ይመግበዋል፡ይንከባከበዋል።


ስለዚህ ወገኖቼ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ የቅዱሳንን ሕብረት አጥብቀን ልንፈልግ ይገባል። በሰበብ አስባቡ ከሕብረት በመራቅ እና በመለዬት ሕይወታችንን አደጋ ላይ ልንጥል ፈጽሞ አይገባም። ቀስ በቀስ ከጸሎት ህብረቶች፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች፡ የአዳር ጸሎት ፐሮግራሞች፡ የኮሚቴ ሃላፊነቶች፡ የሰፈር እና መደበኛ የጋራ ጊዜያት እየተዉን ስንመጣ ህይወታችን እየደከመ ብሎም እየሞተ ይሄዳል። የበረከት ምንጫችን ተቋርጧልና።


ወገኖቼ በሕብረት በመሆን ማገልገልና መገልገልን የሕይወታችን ቋሚ ልማድ ልናደርገው ይገባል። በግል ያቃተን ነገር በህብረት ጸሎት ይፈታል። በግል ጥናት ያልተረዳነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በጋራ ጥናት ይመለሳል። ምክርና ተግሳጽ እርዳታ እና ማበረታቻ የምናገኘው በሕብረት ነው።


በአጠቃላይ የክርስትና ሕይወት እንደ ቢራቢሮ ከዚህም ከዚያም እየተቅበዘብን በቃረምነው የግል ቃርሚያ ብቻ የምንኖረው ሳይሆን እንደ ንብ በጋራ ተያይዘን የምንኖረው የበረከት ሕይወት ነው " በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።"
(ወደ ዕብራውያን 10:25)


ጌታ ሆይ እርስ በእርሳችን እንድንያያዝ እርዳን! በአንድ ሃሳብ በአንድነት ሆነን የአንተን በረከት እንድንካፈል አግዘን! ከመንከራተት እና ከመቅበዝበዝ መልሰን! ክፉ አውሬ ብቻችንን አግኝቶ እንዳይሰበረን ጠብቀን! በረከትህ ወደ ሚፈስበት ንጹህ ሕብረት አጣብቀን! አሜን! ሃሌሉያ።
----------
ወገኖች ሆይ፣ መልዕክቱን ከወደዳችሁለት ወንድማችን አበባየሁ በየሳምንቱ አርብ በዲቮሽናችን ላይ ሊያገለግለን ይችላልና እስኪ ፍቅራችሁን ግለጹለት፡፡ መልዕክቱን ላይክና ሼር አድርጉ፡፡

No comments:

Post a Comment