ዲቮሽን 217/07፥ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 7/07 ዓ/ም
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
(በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)
ወርቃማው ሕግ!
…ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ
እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና (ማቴ 7፡12)።
‹‹ወርቃማው ሕግ›› በመባል የሚታወቀው
ይኼ የሕይወት መርህ፣ የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከመጻፋቸው ከብዙ ጊዜ በፊትም ጀምሮ በአይሁዶችና በዙሪያው በሚኖሩ አሕዛቦች ሁሉ
ዘንድ የታወቀ መርህ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በሚያውቁም ሆነ በማያውቁ ሰዎች ዘንድ ይህ መርህ የታወቀና የተወደደ
ነው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ይህን በሁሉም የሰው ልጆች ዘንድ የታወቀውንና የተወደደውን የሕይወት መርህ፣ ለደቀመዛሙርቱ ሲሰጥ ከመርህነት ባለፈ በሕግ ደረጃ
ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን በዘሌዋውያን 19፡18 ላይ ‹‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ›› ሲል ያዝዛል፡፡ ይህን ስንመለከት ጉዳዩ ከመርህነት
ያለፈ፣ ሕግ ወይንም ትዕዛዝ መሆኑን ልብ ይሏል!
ታውቃላችሁ፣ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን
መውደድ በሕግም ሆነ በነቢያት የሕይወት መርህ ሳይሆን መለኮታዊ ትዕዛዝ ነው! ይህን ትዕዛዝ አለመፈጸም ትልቅ አደጋ አለው!
ወገኖች ሆይ፣ ሌሎች በእኛ ላይ እንዲያደርጉ
የምንፈልገውን ለሌሎች እናድርግ! ሌሎች በእኛ ላይ እንዲያደርጉ የማንፈልገውን ደግሞ በሌሎች ላይ አናድርግ!
ወገኖች ሆይ፣ ሌሎች በእኛ ላይ ክፉ እንዲያደርጉ
አንፈልግምና፣ በሌሎችም ላይ ክፉ አናድርግባቸው! ሌሎች እንዲሰድቡን፣ እንዲጎዱንና እንዲያዋርዱን አንፈልግምና፣ በሌሎችም ላይ ስድብ
ጉዳትና ውርደት እናድርግባቸው፡፡
ወገኖች ሆይ፣ በሌሎች መጠላት፣ በሌሎች
መከዳት፣ በሌሎች መከፋት አንወድምና፣ እኛም በሌሎች ላይ ጥላቻና ክህደት ክፋት አንፈጽም፡፡
ወገኖች ሆይ፣ በሌሎች መዘለፍ፣ በሌሎች
መነቀፍ፣ በሌሎች መሰየፍ አንፈልግምና እኛ በሌሎች ላይ ዘለፋና ነቀፋ፣ እንዲሁም ሰይፍ መዘዛ እናቁም፡፡
ታውቃላችሁ፣ ሌሎች እንዲሰርቁን፣ እንዲመነትፉን፣
እንዲያታልሉንና እንዲያጭበረብሩን ፈጽሞ አንመርጥምና፣ እኛም በሌሎች ላይ ይህንን አናድርግ! ሌሎች እንዲገፍፉን፣ እንዲዘርፉን፣
እንዲበረብሩንና እንዲመዘብሩን አንወድምና፣ እኛም በሌሎች ላይ ይህንን
አናድርግ!
ወገኖች ሆይ፣ ሌሎች እንዲጨቁኑን፣ እንዲፈጩንና
እንዲጨፈልቁን አንፈልግምና፣ እኛም በሌሎች ላይ ይህንን አናድርግ! ሌሎች እንዲጨቀጭቁን፣ እንዲነዘንዙን፣ እንዲለበልቡንና እንዲያንገበግቡን
አንሻምና፣ እኛም በሌሎች ላይ ይህንን አናድርግ!
ወገኖች ሆይ፣ ሌሎች እንዲወጉን፣ ሌሎች
እንዲያቆስሉን፣ እንዲያደሙንና ደግሞም እንዲገድሉን አንፈልግምና፣ እኛም በሌሎች ላይ ይህንን አናድርግ!
ወገኖች ሆይ፣ ሌሎች እንዲነድፉን፣ ሌሎች
እንዲገርፉን፣ ሌሎች እንዲገፉን፣ ሌሎች እንዲጠልፉን፣ እንዲያደናቅፉንና
እንዲያጨናግፉን አንፈልግምና፣ እኛም በሌሎች ላይ ይህንን አናድርግ!
ወገኖች ሆይ፣ ሌሎች እንዲያደርጉልን የምንወድደውን
ሁሉ እኛም ደግሞ እንዲሁ አናድርግ፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና!
---------
ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፡፡ ጌታ ይባርክዎ!
No comments:
Post a Comment