ዲቮሽን ቁ. 215/07፤ ሰኞ፣ ሚያዚያ 5/07 ዓ/ም
(በማርታ ሲሳይነህ)
ሠልፉ የእግዚአብሔር ነው!
የጠበቀን፣ የመጣብንንም ወራሪ በእጃችን የጣለልን እግዚአብሔር ነው። 1ኛ ሳሙ 30፤23
ዳዊት ከሳኦል ሸሽቶ ወደ ፍልስጥኤም ሔደ፤ አንኩስንም መጠጊያ ሲለምነው፤ ጺቅላግን ሰጠው። ፍልስጥኤማውያን፣ እስራኤልን ለመውጋት ሲወጡ፣ አንኩስ ስለተማመነበት፣ ዳዊትንም ወደ ጦርነት ይዞት ሔደ። ሆኖም፣ የፍልስጥኤም ገዥዎች፣ ዳዊትን ስላላመኑት፣ ዳዊት፣ ሰዎቹን ይዞ ወደ ፍልስጥኤም ተመለሰ። በሦስተኛው ቀን ጺቅላግ ሲደርሱ ግን፣ እነ ዳዊትን የገጠማቸው አስደንጋጭ ነገር ነበር። አማሌቃውያን፣ ጺቅላግን ወረው፣ ወግተው፣ ከተማይቱ በእሳት ጋይታ፣ ሚስቶቻቸውና ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች ሁሉ ተማርከው፣ ጠበቃቸው።
በዚህ ጊዜ ዳዊት፣ እግዚአብሔርን ʻይሔንን ወራሪ ሠራዊት ልከተለውን? እደርስባቸዋለሁን?ʼ ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ʻትደርስባቸዋለህ፣ ምርኮውን ትመልሳለህ፣ ተከተላቸውʼ አለው። ሁለት መቶ ሠዎች ሲቀሩ፣ አራት መቶ ሠዎች ተከትለውት ሔዱ። በምድረበዳም፣ አንድ ግብጻዊ አገኙና፣ ወራሪው ሠራዊት ወዳለበት መርቶ አደረሳቸው። ዳዊትም አማሌቃውያን የወሰዱትን ሁሉ አስጣለ፤ ሁለቱንም ሚስቶቹን አስመለሰ፤ ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንዶችም ሆነ ሴቶች ልጆች፣ ምርኮም ሆነ ሌላ፣ አማሌቃውያን ከወሰዱት ነገር ምንም የጎደለ አልነበረም፤ ዳዊት ሁሉንም አስመለሰ። እንዲሁም፣ የበጉን፣ የላሙን፣ የፍየሉን መንጋ ሁሉ ወሰደ።
ከዚያም ዳዊት፣ እጅግ በመድከማቸው የተነሣ ሊከተሉት ወዳልቻሉት ወደ ሁለት መቶ ሰዎች መጣ። አብረውት ከተከተሉት መካከል አንዳንዶች፣ ʻአብረውን ስላልዘመቱ ካመጣነው ምርኮ አናካፍላቸውምʼ አሉ። ዳዊት ግን፣ ʻወንድሞቼ ሆይ፣ የጠበቀን፣ የመጣብንንም ወራሪ በእጃችን የጣለልን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በሰጠን ነገር ይህን ማድረግ አይገባችሁም፤ ሁሉም እኩል ይካፈላሉʼ አላቸው፤ አደረገውም።
ወገኖቼ ሆይ፣ አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ላይ በሚመጣ መከራ አብረውን የማይቆሙ ሰዎች ይኖራሉ፣ አልፎ ተርፎም ምናልባትም፣ ሊሳለቁብንና ሽንፈታችንን በጉጉት እየጠበቁ ከጎን ቆመው የሚያዩ ሰዎች ይኖራሉ፣ ቢሆንም ግን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከመሆኑ የተነሳ የማይታመኑ፣ ድንቆችንና ሁኔታወችን አመቻችቶልን፣ በመከራችን ላይ ድልን ባገኘን ግዜ፣ ያስቀየሙንን፣ ድል አታገኙም ብለው፣ የሳቁብንን፣ ያዋረዱንን፣ ያሙንን ሁሉ ልንባርካቸው እንጅ፣ የታባታቸው ብለን ልንበቀላቸው አይገባም።
በድህነታችን፣ በማጣታችን ግዜ፣ ወይም በሕመም እና በችግራችን ግዜ፣ ወይም በሕይወታችን ላይ ሰልፍ በበረታ ግዜ፣ ከዳር ቆመው ስንሞትና ስንዋረድ ለማየት እንዲሁም ለመሳቅ እና እሰይ ለማለት አሰፍስፍው የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፣ በጌታ ተዓምራት ሁሉን አልፈን ባዩን ግዜ ልናባርካቸው ይገባል።
የናቁን፣ ያንቋሸሹንን ሁሉ፣ በልዩ ልዩ፣ የጸጋ አገልግሎቶች በተገለጥን ግዜ፣ እግዚአብሔር ከሰጠን፣ የጸጋ አግልግሎት፣ የትንቢትም ሆነ፣ የፈውስ አግልግሎት በረከት በፍጹም ፍቅር ልናካፍላቸው ይገባል።
ውርደታችንን በክብር፣ ሐዘናችንን በደስታ እግዚአብሔር በለወጠልን ግዜ፣ ከዳር ቆመው ያሾፉብንን ሁሉ፣ በእኛ ላይ የሆነውን የጌታን ማዳን አይተው በሕይወት መዝገብ ላይ ከእኛ ጋር ስማቸው አብሮ እንዲጻፍ ልንረዳቸው ይገባል፤ ምክያቱም እኛም ሰው የሆንነው፣ በጌታ ጸጋ፣ እርዳታ፣ ምሕረትና፣ እገዛ በመሆኑ!!!!!!!
አብ አባት ሆይ! ሠልፉ ያንተ ነውና፣ አንተ ተዋግተህ ባሸነፍክልንና ድልን ባቀዳጀህን ቦታዎች እና በሮች ሁሉ፣ እኛም ትህትናን ካንተ ተምረን፤ ለናቁንና ለጠሉን ሁሉ የበረከት እና የፈውስ ምንጭ አድርገን፤ በቀል በኢየሱስ ስም ዛሬ ከእኛ ይራቅ! ሠምተህኛልና ተባረክ።
------------
ትምህርቱ ጠቅሞዎታል? እባክዎ እንግዲያውስ እባክዎ ላይክና ሼር ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!
No comments:
Post a Comment