Monday, March 30, 2015

In Memory of God's Mercy!



In Memory of God's Mercy!

12 months, 52 weeks, 365 days, 8,760 hours, 525,600 minutes, 31,536,000 seconds, (a year ago) – I had survived the deadly accident by the mercy of God! I shall not die, but live, and declare the works of the Lord (Psl 118:17-8).

ማስታወሻ – ለእግዚአብሔር!





ዲቮሽን . 201/07 ሰኞ፥ መጋቢት 21/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ማስታወሻ – ለእግዚአብሔር!

12 ወራት፣ 52 ሣምንታት፣ 365 ቀናት፣ 8,760 ሰዓታት፣ 525,600 ደቂቃዎች፣ 31,536,000 ሰኮንዶች – ድፍን አንድ ዓመት – በታላቅ ምሕረትህና በርኅራኄህ አለፉ! 

አምላኬ ሆይ፣ በወንዞች ውስጥ ባለፍሁ ጊዜ አላሰጠሙኝም! በእሳትም ውስጥ በሄድሁ ጊዜ አላቃጠሉኝም፥ ነበልባሉም አልፈጀኝም! ውኆች ሲናወጡ፣ ማዕበሉ ሲቆጣ፣ በወጀብ በአውሎንፋስ አልተለየኸኝምና አመሰግንሃለሁ!

12 ወራት፣ 52 ሣምንታት፣ 365 ቀናት፣ 8,760 ሰዓታት፣ 525,600 ደቂቃዎች፣ 31,536,000 ሰኮንዶች – ድፍን አንድ ዓመት – መገሰጹንስ እጅግ ብትገስጸኝም፣ ነገር ግን ለሞት አሳልፈህ አልሰጠኸኝምና በጨመርኽልኝ ዕድሜ አገለግልሃለሁ!

አምላኬ ሆይ፣ ተርፌ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤ የአንተንም ሥራ ገና እናገራለሁ! ከአዳኝ ወጥመድ፣ ከሚያስደነግጥ ነገር፣ ከአደጋ ከመቅሰፍት፣ ከሸማቂ ጠላት፣ ከድንገተኛ ጥፋት፣ አድነኸኛልና አመሰግንሃለሁ! 

አልሞትም በሕይወት እኖራለሁ እንጂ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እናገራለሁ። መገሠጽስ እግዚአብሔር ገሠጸኝ ለሞት ግን አልሰጠኝም (መዝ 118፡17-18)።







Sunday, March 29, 2015

የቀባኋቸውን አትዳስሱ – በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ!

ዲቮሽን . 200/07፣ እሁድ መጋቢት 20/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


የቀባኋቸውን አትዳስሱ – በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ!

የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ ብሎ፥ ሰው ግፍ ያደርግባቸው ዘንድ አልፈቀደም፤ ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ (1ዜና 16፡21-22፤ መዝ 105፡14-15)።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን፣ የተቀቡትን የዳሰሱ፣ በነቢያቱም ላይ ክፉ ያደረጉ ሰዎች በሕመም፣ በልዩ ልዩ መቅሰፍትና በሞት ተገስጸዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ወዳጅ ከሆነው ከአብርሃም ሚስቱን ሦራን የነጠቁ ነገሥታት በታላቅ መቅሰፍት ተመትተዋል፣ በታላቅ ግሳጼም ቅጣት ተቀብለዋል (ዘፍ 12፡17፤ 20፡3)፡፡

ወገኖች ሆይ፣ በያዕቆብ ላይ ግፍ የሠራው ላባ የሠራው ግፍ ሳያንስ ከሚሸሽበት መንገድ አሳድዶ ሊመታው ሲገሰግስ ሳለ ጌታ በሌሊት ሕልም መጥቶ፣ ያዕቆብን በክፉ ነገር እንዳይናገረው አስጠንቅቆታል(ዘፍ 12፡17፤ 20፡3)፡፡ ፡፡

ወገኖች ሆይ፣ ያዕቆብ ከላባ አምልጦ ወደ ትውልድ ቀዬው በመመለስ ሳለ ኤሣው በቂም በቀል 400 ሰዎች አስከትሎ ያዕቆብን ለመግደል እየመጣ ሳለ መላእክቱን በመላክ ተከላክሎለታል(ዘፍ 32-33)፡፡  ጠንቋዩ በለዓም እስራኤላዊያን ሊረግም ሲነሣ መልዐኩን በመላክ መንገዱን ዘግቶታል(ዘኁ 22)፡፡  

ወገኖች ሆይ፣ በመርዶክዮስ ላይ የስቅላት ሞትን የሸረበው ሐማ የሆነውን አስቡ! ነቢዩን ዳንኤል በሐሰት ከስሰውት በአንበሶች ጉድጓድ ያስጣሉትን ሰዎች ፍጻሜ አስቡ! ከአምላካቸው በቀር ማንም እንዳያመልኩ የወሰኑትን እነዚያን ወጣቶች በእቶን እሳት ውስጥ ያስጣሉትን ሰዎች እስኪ አስተውሉ!

ታውቃላችሁ፣ ስለአገልጋዮቹ ጌታ ይቆረቆራልና እርሱ የቀባቸውን በሚዳስሱት ላይ እጁን ይዘረጋል! በነቢያቱም ላይ ክፉ በሚያደርጉት ግሳጼውን ያወርዳል!

ወገኖች ሆይ፣ በእግዚአብሔር ነቢያት፣ በተቀቡ አገልጋዮቹ ላይ የምንሠራውን ነገር ደጋግመን መመርመር ደጋግመን መጠየቅ ደጋግመን መጠንቀቅ እጅግ ያስፈልጋል! ‹‹የቀባኋቸውን አትዳስሱ፥ በነቢያቴም ክፉ አታድርጉ›› ብሎ የተናገረው ጌታ ራሱ ነውና ይህን ማስጠንቀቂያ መጠንቀቅ ይገባል!


ታውቃላችሁ፣ ይኼ ማስጠንቀቂያ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው መኖሩን እያዩ፣ ከፍተው እያነበቡ፣ እየሰበኩና እያስተማሩ፣ ነገር ግን የተቀቡትን የሚዳስሱ፥ በነቢያቱም ላይ ክፉ የሚያደርጉ፣ መሪዎች ቢሆኑ አገልጋዮች ቢሆኑ – ከጠንቋዩ በለዓም፣ ከጨካኙ ፈርኦን፣ ከኤሣውና ላባ፣ ከአቤሜሌክ ይልቅ፣ ጌታን የመመልከት ብቃት የሌላቸው፣ ድምጹንም ለመስማት አቅም የሌላቸው – አይነ ስውሮችና ደንቆሮዎች ናቸው!

Saturday, March 28, 2015

ከእግዚአብሔር ጋር – መጣላት!

ዲቮሽን .199/07፣ ቅዳሜ መጋቢት 19/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


ከእግዚአብሔር ጋር – መጣላት!

ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል (ሮሜ 8፡7)፡፡

የእግዚአብሔር ጠላትነት ምሽጉ ያለው በሐሳባችን ወይንም በአእምሮአችን ውስጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጠላትነት ያለው ባልተለወጠ ሰው ሐሳብ ወይንም ዳግመኛ ባልተወለደ ሰው አእምሮ ውስጥ ነው፡፡

ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው አእምሮ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያለ ነውና ራሱን ለእግዚአብሔር ማስገዛት አይችልም፡፡ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያለ ሰው ለእግዚአብሔር መገዛት ቢፈልግ እንኳ የእግዚአብሔር መንፈስ ውስጡ የለምና ይህን ለማድረግ ፍጹም ይሳነዋል፡፡ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያሰ ሰው እግዚአብሔርን ማስደሰት በፍጹም አይችልም፡፡

ታውቃላችሁ፣ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና – ያልተለወጠ ሰው ሐሳብ የሞት መንትያ ነው! ይህም ማለት በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ያለ አእምሮ ወደ ሞት ይመራል ማለት ነው!

ታውቃላችሁ፣ ስለሥጋ ማሰብ ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ማለት ነው! ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉና በሥጋ አስተሳሰብ የሚመላለሱ ወደ ሞት ይወርዳሉ፡፡

ታውቃላችሁ፣ በየቤተክርስቲያኑ ብዙ መታለል አለ! ሰዎች እጃቸውን አንስተው ጌታን ሲቀበሉ፣ የደኅነት ትምህርት ተምረው ሲጨርሱ፣ የውሃ ጥምቀቱን ሲያጠናቅቁ በቃ በአባልነት መዝገብ ይመዘገባሉ! እነዚህ ወገኖች የደቀመዝሙርነት ትምህርት ተከታትለው ሲጨርሱ፣ ልዩ ልዩ አገልግሎት ይጀምራሉ፡፡ እዚህ ላይ ነው ችግሩ!

ወገኖች ሆይ፣ ነፍሳት ጌታን ሲቀበሉ በመንፈስ ቅዱስ እንዲጠመቁ ልንጸልይ ይገባል! በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ ሐሳባቸው ከኃጢአት ቁጥጥር ሥር አርነት ይወጣል! በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቀ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ዘንድ ይኖራል፡፡

ወገኖች ሆይ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ የሚኖር ሰው አስተሳሰቡ መንፈሳዊ ይሆናል፡፡ ስለመንፈስ ማሰብ ሕይወትና ሰላም አስከትሎ ይመጣል!

ታውቃላችሁ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሥጋ ሥራ እንጂ የመንፈስ ፍሬ የማይታይባቸው ብዙ አባላት አሉ፡፡ ከመዋደድ ይልቅ ጥልና ክርክር ጭቅጭቅ ንትርክ የሚወድዱ፣ በሕይወታቸው ውስጥ ደስታ የሌላቸው፣ ከሰላም የተጣሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡

ወዳጄ ሆይ፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይጣሉ ስለሥጋ አያስቡ!  ይደቅቃሉና ስለሥጋ አያስቡ! ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይሞታሉና በሥጋ አስተሳሰብ አይመላለሱ! በሥጋ አስተሳሰብ የሚመላለሱ ወደ ሞት ይወርዳሉና በሥጋ አስተሳሰብ አይመላለሱ!  

------------------------------------------

(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!) 

Friday, March 27, 2015

በጥቂቱ ታምነሃል – በብዙ እሾምሃለሁ!

ዲቮሽን .198/07፣ አርብ መጋቢት 18/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ!

መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ (ማቴ 25፡20-23)።

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ለመንግሥቱ ሥራ በኃይል ቀብቶ እንዲያስነሳን፣ በሙላት እንዲጠቀምብን እንፈልጋለንና በጾምና ጸሎት እንጠይቀዋለን፡፡ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምድር ላይ ለመገንባት በውስጣችን ፍላጎት ማደሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ተቀብቶ ለመውጣት መጾምና መጸለይም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡

ወገኖች ሆይ፣ እግዚአብሔር አምላካችን ለመንግሥቱ ሥራ አገልጋዮችን በኃይል ቀብቶ ማስነሳትና፣ በሙላትም መጠቀም የዕለት ተዕለት ፍላጎቱ ነው! ነገር ግን ይኼው አምላካችን እኛን በአገልግሎት ቅባት ቀብቶ ለማውጣት – የእኛን ታማኝነት ይመለከታል!

ወገኖች ሆይ፣ በብዙ ለመሾም በጥቂቱ መታመን መለኮታዊ ሕግ ነው! በመለኮታዊ አሠራር በጥቂት ነገር መታመን በብዙ ያሾማል! በተሰጠን በጥቂቱ ነገር ታምነን ያልተገኘን በብዙ ለመሾም የመጠበቅ ነገር የማይታሰብ ነው!

ወገኖች ሆይ፣ በተሰጠን በጥቂቱ ነገር ታማኞች ሳንሆን በብዙ ለመሾም መጾም መጸለዩ እንዲሁ ለድካም ነው! ታማኝነት ሳይኖር፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ጸሎት፣ እልፍ ጊዜ እልፍ ጾም የእግዚአብሔርን ቅባት ሊያመጣው አይችልም!

ታውቃላችሁ፣ ማናችንም ብንሆን ሀብት ንብረታችንን ለማንታመነው ሰው አደራ አንሰጥም! አመራር፣ አስተዳደር፣ ሹመት ሽልማት የሚመሠረተው በታማኝነት ነው!

ወገኖች ሆይ፣ ከጌታ ለተሰጠን ለጥቂቱ ነገር ታማኞች እንሁን! ይኼ ታማኝነታችን በእግዚአብሔር ፊት ብድራት ያገኛል! ስለሆነም፣ ለተሰጠን ለጥቂቱ ነገር ታማኞች እንሁን!

ታውቃላችሁ፣ በጥቂት መታመን፥ ለብዙ ሹመት በር ይከፍታል፤ ይህ በር ሲከፈት ወደ ጌታ ደስታ መግባት ያስከትላል! ሃሌሉያ!

------------------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!) 

(1) ዕለታዊ ዲቮሽኖቹን በፌስቡክ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡ https://www.facebook.com/tesfahun.hatia

(2) ዲቮሽኖቹን በብሎግ ለመከታተል የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡፡ https://draft.blogger.com/blogger.g?blogID=7832170107481561272#allposts

(3) ኤግል የሬዲዮ አገልግሎት በአማርኛ ቋንቋ መጀመሬን በደስታ አሳውቃለሁ፡፡ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ አማርኛ አድማጮች http://zenoradio.com/en/listeners/ET/Eagle+Amharic+Radio/ በመጫን ሊያዳምጡ ይችላሉ፡፡ Listeners in Canada and America can call free at (605) 562 4274 and enjoy some of my live sermons.

Thursday, March 26, 2015

በረከትና መርገም – ከከተማ እስከ ገጠር!



ዲቮሽን .197/07፣ ሐሙስ መጋቢት 17/07 ..
(
በፓ/ር ተስፋሁን ሐጢያ)


 በረከትና መርገም – ከከተማ እስከ ገጠር!

የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል። በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ። …ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል። በከተማ ርጉም ትሆናለህ፥ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ (ዘዳ 28)።

ዘዳግም ምዕራፍ 28 መልዕክቶች ሁሉ አቢይ መልዕክት ሆኖ ይገኛል – በረከት ወይም መርገም፡፡ ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ያሉ ስድሳ ስድስቱ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የመልዕክታቸው ዋና ጭብጥ በዘዳግም 28 ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው – በረከት ወይም መርገም!

ወገኖች ሆይ፣ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል መስማት፣ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ መጠበቅና ማድረግ የእግዚአብሔርን በረከቶች ሁሉ የሚያመጣ ሲሆን፣ ቃሉን አለመስማት፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ አለመጠበቅ አለማድረግም፥ መርገሞችን ሁሉ የሚያስከትል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

ታውቃላችሁ፣ በረከትና መርገም እንደ 'ራዳር' ናቸው! በረከትና መርገም እንደ 'ራዳር' የገባንበት ገብተው የወጣንበት ወጥተው ፈልገው ያገኙናል፣ ካለንበት ቦታ ተከትለው ይመጡልናል አሊያም ይመጡብናል! 

ታውቃላችሁ፣ በረከትና መርገም እንደ 'ራዳር' ናቸውና አናመልጣቸውም! ቃሉን ስንታዘዝ የእግዚአብሔር በረከቶች የገባንበት ገብተው ፈልገው ያገኙናል፣ የወጣንበት ወጥተው ይገናኙናል! ቃሉን ካልታዘዝን መርገሞቹ ሁሉ የገባንበት ገብተው ፈልገው ያገኙናል፣ የወጣንበት ወጥተው ይገናኙናል!

ታውቃላችሁ፣ በረከትና መርገም እንደ 'ራዳር' ናቸውና ከተማም ብንገባ፣ ገጠርም ብንሄድ አናመልጣቸውም! ነጋዴም ብንሆን፣ ገበሬም ብንሆን፣ መሐይምም ብንሆን ምሁርም ብንሆን፣ ድሃና ሀብታምም፣ ትልቅም ትንሽም ከእግዚአብሔር ራዳር ልናመልጥ አንችልም!

------------------------------------------
(ትምህርቱ ጠቅምዎታል? እንግዲያውስ ላይክ ያድርጉ፣ ጌታ ይባርክዎ!)